ፈልግ

በጀርመን የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምርምር ማዕከል በጀርመን የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምርምር ማዕከል 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ለጋራ ጥቅም ሲባል ለሁሉም ማድረስ ያስፈልጋል ተባለ።

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፣ ጸረ ኮቪድ-19 ወረሽኝ መከላከያ ክትባት ገደብ ሳይደርግባት ወደ ሁሉም አገራት እንዲደርስ አሳሰበ። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚሰጥ ክትባት ማንንም ወደ ጎን ሳይል ሕክምናውን የማግኘት ዕድሉን መነፈግ የለበትም ብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው በማሳሰቢያ ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒቱን በማምረት እና ማከፋፈል ሂደት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እየታየ መሆኑን ገልጾ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽ  ዘዴ እና ኅብረት በባለ ድርሻ አካላት መካከል በአስቸኳይ እንዲፈጠር አሳስቧል። አካዳሚው በመግለጫው አክሎም፣ በወረርሽኙ መከላከያ መድኃኒት አምራች አገሮች መካከል ፉክክር መኖሩን ገልጾ፣ ይህ ፉክክር ተመልሶ ከባድ የፍትህ መጓደል አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በአካዳሚው ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ እና በቻንስለሩ ብጹዕ አቡነ ሬንዞ ፔጎራራ በጋራ ተፈርሞ ይፋ የሆነው መግለጫ እንዳመልከተው ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ አቆጣጠር ታኅሳስ ወር 2020 ዓ. ም. የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ለሮም ከተማ እና ለዓለም በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት፣   የመንግሥት መሪዎች ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ወደ ሁሉም አገሮች ለማድረስ፣ በተለይም ለወረርሽኙ ይበልጥ የተጋለጡ አቅመ ደካሞችን ፈጥኖ ለመርዳት ሁሉም ሰው እንዲተባበር በማለት መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ የቅዱስነታቸው መልዕክት ሃላፊነት በሚሰማቸው እና መልካም ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ተደማጭነትን እንዲያገኝ አሳስበዋል።

ልዩ ሰነድ

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፣ ከቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር እ.አ.አ ታኅሳስ 29/2020 ዓ. ም. ያወጡትን ሰነድ በማስታወስ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒት መገኘቱ እና መድኃኒቱን ለሁሉ ሰው እንዲደርስ ማድረጉ ለጋራ ጥቅም አስፈላጊ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። የጋራ ሰነዱ በተጨማሪም የወረርሽኙን መከላከያ መድኃኒት በአገር በመገደብ፣ ለተወሰኑት ዜጎች ብቻ በቅድሚያ እንዲቀርብላቸው ለማድረግ የሚወሰደው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል። የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ በማከልም፣ የመድኃኒት ምርቱ ለሁሉ ሰው ተደራሽ እንዲሆን ለማመቻቸት እና በባለቤትነት መብቶች ላይ ስምምነት በማድረግ፣ ወደ ንግድ የሚያዘነብሉ አዝማሚያዎችን ለማስቀረት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲደረጉ እና ሁሉን ሰው ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በመድኃኒቱ ዋጋ ላይ ቁጥርር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቆ በመድኃኒት ምርት ሂደት ላይ የአገሮች፣ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች እና ሌሎች ድርጅቶች በመተባበር፣ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ተመሳሳይ አገልግሎት ተግባራዊ እንዲሆን አሳስቧል።

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ መግለጫውን ሲያጠቃልል፣ ከላይ የተጠቀሱ፣ የወረርሽኙን መከላከያ መድኃኒት አቅርቦት ዘዴን መከተል ወደ ፊትም ፍሬያማ ውጤትን ለማምጣት እንደሚያገለግል ገልጾ፣ በጋራ ስምምነቶች ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ዘዴዎችም ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተደረገ “ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መሆኑን አስረድቷል።  

23 January 2021, 15:07