ፈልግ

ዓለም አቀፍ የሰላም ጸሎት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የሰላም ጸሎት ጉባኤ 

ቅድስት መንበር በጋራ መግባባት እና እምነት ለክርስቲያኖች ውህደት እንደምትሰራ አስታወቀች

አስቸጋሪ በሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ቢሆን ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን ኅብረት የሚያጠናክሩ የአንድነት እና የቸርነት ሥራዎች በጽሕፈት ቤታቸው በኩል እየተከናወነ መሆኑን፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል “ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ” ለተባለ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ኩርት በመግለጫቸው፣ ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በግልም ሆነ በጋራ ሕይወት ላይ ያስከተለው ለውጥ ለረጅም ጊዜ ሲታወስ ይኖራል ብለዋል። ለውጡ በማኅበራዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴ ላይ የጤና አገልግሎት መቃወስን በማስከተል የራሱን ሚና ተጫውቷል። ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማስወገድ ያላቸውን መልካም ፍላጎት በመግለጽ፣ የግል ግንኙነቶችን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አሳይተዋል። በክርስቲያኖች በመካከላቸው አንድነት ሊመጣ እና ሊያድግ የሚችለው የጋራ መግባባት እና መተማመን ሲኖር ነው።  በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ሊካሄድ የታቀዱ በርካታ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች፣ ስብሰባዎች እና የጋራ ውይይቶች ሊሰረዙ ወይም ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፉ ተደርገዋል። በቴክኖሎጂዎች አማካይነት የሚደረጉ የሃሳብ፣ የእምነት እና የውስጥ ተነሳሽነት ልውውጥ የተፈለገውን ያህል ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል ባይባልም፣ በርካታ ስብሰባዎች በቪዲዮ ኮንፌረንስ አማካይነት እንዲካሄዱ ተደርገዋል። ይህ ቢሆንም

በዚህ አስጨናቂ ዓመት ውስጥ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች ቀጥለው መልካም እድገትን በማሳየት ላይ ይገኛል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ 1960 ዓ. ም. የተመሠረተው፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የቆመለትን ዓላማ እና እምነት አጥብቆ በመያዝ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል የሚታየውን የክርስቲያኖች አንድነት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነቶች ማሳደግ የምትችልባቸውን መንገዶች በማሳየት ብርታትን እየሰጠ ይገኛል። እነዚህ ሁለት የሥራ ድርሻዎች በቅርቡ የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባሳተመው እና ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባርከው ይፋ ባደረጉት ሰነድ ላይ በደንብ ተብራርተዋል። ሰነዱ በምክር ቤቱ ባለሙያዎች እና በሮማ የቅድስት መንበር መማክርት ብቃት ባላቸው መምሪያዎች ጸድቆ ተዘጋጅቷል። በቅርቡ የተከናወኑ ተግባራትን ስናስታውስ፣ የጳጳሳትን ብቻ ሳይሆን የመላው ቤተክርስቲያንን መሠረታዊ የክርስቲያኖች ውህደት የሚያንፀባርቁ የምክር ቤቱን ሰነድ አወቃቀር እንደገና መመልከት እንችላለን።

ቀዳሚ የሥራ ድርሻ የሚሆነው፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጠናከር የምታካሂዳቸውን ተግባራት በቀጣይነት ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንድትቀጥልበት ማድረግ ሲሆን፣ ይህን ለማድረግ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት፣ ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ማዘጋጀት እና ውስጣዊ ፍላጎትን ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪም የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጠናከር የሚያግዙ የተለያዩ ስብሰባዎችን መሳተፍ፣ የተለያዩ ሕትመቶችን ማግኘት፣ ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ዘላቂ ግንኙነትን መመስረት፣ ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ወደ ቫቲካን ማድረግ የሚሉ ይገኙባቸዋል። ከዚህም በላይ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የክርስቲያኖችን የውህደት ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛሉ ያሏቸውን የሚከተሉ አዳዲስ መንገዶች አስቀምጧል። ከሁሉም አስቀድሞ ቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን ውህደት ለማጠናከር የሚያግዙ፣ ሁለተኛውን የቫቲካን ሰነድ ጨምሮ በርካታ ጥንታዊ የቤተክርስቲያን ሰነዶች ያሉበት (www.christianunity.va) የተሰኘ ድረ ገጽ፣ ሁሉም ሰው ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ይፋ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ከሃምሳ ዓመታት በላይ ሲያሳትም የቆየውን «Acta Œcumenica» የተባለ መጽሔት ከሙሉ መረጃዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል። እንደዚሁም «Ut unum sint» የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ተከታታይ መጽሔት ካቫቲካን አሳታሚ ድርጅት ጋር በመተባበር ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል። ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ማዘጋጀት በተመለከተ ሮም ከተማ የሚገኘው “አንጄሊኩም” የተባለ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ፣ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያግዙ ኮርሶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። የክርስቲያኖችን ውህደት ለማፋጠን ከሚረዱ መንገዶች መካከል ሁለተኛው፥ መንፈሳዊ የክርስቲያኖች ውህደት እንቅስቃሴ፣ ቸርነትን ለማሳደግ የሚደረግ የጋራ ውይይት፣ እውነትን ለማግኘት የሚደረግ የጋራ ውይይት እና ሕይወትን ለማግኘት የሚደረጉ የጋራ ውይይቶች ናቸው።

የክርስቲያኖችን ውህደት ለማምጣት በሚደረግ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ከአብያተ ክርስቲያናት የውህደት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በየዓመቱ የጸሎት ሳምንትን በማስተባበር ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያሳድጉ ሌሎች ተግባራት፣ ለምሳሌ ቅዱሳት አጽሞችን ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወደ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በጊዜያዊነት ማዛወርን ይመለከታል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2017 ዓ. ም. የቅዱስ ኒኮላ አጽምን ከጣሊያን የባሪ ከተማ ካቶሊካዊ ቁምስና ወደ ሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በጊዜያዊነት ማዛወሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ምዕመናን መንፈሳዊ ጉዞ እንዲያደርጉ ማበረታታቱ ይታወሳል። እንደዚሁም ተመሳሳይ መንገድ ወደ ግሪክ እና ቡልጋሪያ በጊዜያዊነት የተደረጉ የቅዱስ አጽም ዝውውር፣ በርካታ ምዕመናን ለአንድነት ያላቸውን ምኞት ማነቃቃቱ ይታወሳል። በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘንድ ለቅዱሳን እና ለሰማዕታት ቅዱስ አጽም የሚሰጥ ክብር ሕያው በመሆኑ ከምዕመናን ዘንድ የሚቀርብ ጥያቄ ብዙ ነው።

በክርስቲያኖች መካከል ቸርነትን ለማሳደግ የሚደረግ የጋራ ውይይት በተመለከተ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የስብሰባ መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ክርስቲያናዊ ተቋማት መሪዎችን ማሳተፉ ይታወሳል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመግባቱ በፊት ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወይም ከክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር ቢያንስ በሳምንት ውስጥ ከአንድ የቤተክርስቲያናት ተወካይ ወይም መሪ ጋር ውይይት ሳይደረግ ያለፈበት ዕለት የለም። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶችም የክርስቲያን አንድነትን ለማጠናከር የታለሙ ነበሩ። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ዱስነታቸው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ በአልባንያ፣ በጆርጂያ፣ በአርሜኒያ፣ በስዊድን፣ በቡልጋሪያ፣ በሰሜን መቄዶኒያ፣ በሮማኒያ፣ በባልቲክ አገሮች እና እ.አ.አ 2018 ዓ. ም. በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ  ወደ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወይም መንፈሳዊ ጉዞ የሚጠቀስ ነው። ይህ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በአብያተ ክርስቲያናት በተለይም በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት ዘንድ መልካም ውጤትን አስገኝቷል። ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጨረሻዎቹ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል የሚጠቀሰው እ.አ.አ. በ 2016 ዓ. ም. ወደ ሩሲያ ያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በሮም በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ እና በሩሲያ ሞስኮ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ ጋር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሐዋርያዊ ግንኙነት ነበር።       

በክርስቲያኖች መካከል እውነትን ለማግኘት የሚደረግ የጋራ ውይይት በተመለከተ፣ በርካታ ሥነ መለኮታዊ ውይይቶች መካሄዳቸው ሲታወስ፣ በአሁኑ ወቅት አስራ አምስት የሁለትዮሽ እና የተለያዩ ሁለገብ ርዕሦች ላይ ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። በእርግጥ ሁሉም ውይይቶች ተመሳሳይ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ይዘት ያላቸው አይደሉም፤ ተመሳሳይ ውጤትም የላቸውም። እያንዳንዱ ርዕሠ ጉዳይ በተወሰነ ሥነ-መለኮታዊ / ቤተ-ክርስቲያን መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማሳትረፍ ይፈልጋል። የውይይቱ ተሳታፊ ሰው ቁጥር ይለያያል። ለምሳሌ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል በሚደረግ ውይይት የሚሳተፍ ሰው ቁጥር 28 ሲሆን በሌሎች ውይይቶች እስከ ስድስት ወይም ሰባት ሊደርስ ይችላል። በአጠቃላይ እነዚህ አባላት በዓመት አንድ ጊዜ ፣ ​​ለአንድ ሳምንት ፣ በተለያዩ ሀገሮች ይሰበሰባሉ። የውይይት ምክር ቤቱም ለአምስት ወይም ለስድስት ዓመታት ያህል የሚሠራ ሲሆን ከዚያ በላይም የጋራ መግባባት ላይ እስኪደርስ ድረስ ሊቆይ ይችላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጋራ ውይይቱ ጉልህ የሆኑ ሰነዶች ሊዘጋጁ በቅተዋል። እ.አ.አ በ 2015 ዓ. ም. በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በጴንጤቆስታል ቤተክርስቲያን መካከል “የመንፈስ ቅዱስን ሥራ አታዳፍኑ” (1ኛ ተሰሎ. 5:19) በሚል ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት መደረጉ፣ እ.አ.አ በ 2016 ዓ. ም. በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል “በመጀመሪያው ሚሊኒየም ውስጥ ሲኖዶሳዊነት እና የቤተክርስቲያን ቀዳሚ መሪነት” በሚል ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት መደረጉ፣ ከወንጌላዊያን ኅብረት ጋር “ቅዱሳት መጻሕፍት እና ትውፊቶች እና ቤተክርስቲያን በደኅንነት ጎዳና ውስጥ” በሚል ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት መደረጉ፣ ከሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ጋር “የቅድስና ጥሪ፣ ከክብር ወደ ክብር”፣ እ.አ.አ በ 2017 ዓ. ም. ከምሥራቅ የአሦር ቤተክርስቲያን ጋር “የቅዱስ ቁርባን ሕይወት” በሚል ርዕሥ ላይ ወደ ጋራ ስምምነት መደረሱ፣ እ.አ.አ በ 2018 ዓ. ም. ከአዲሶቹ የተሃድሶ እንቅስቃሴ አብያተ ክርስቲያናት ጋር “የአዲሶቹ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አብያተ ክርስቲያናት ባህሪዎች” የሚል ርዕሥ በተሰጠው ሰነድ ላይ በተናጠል ጥናት መደረጉ ታውቋል። ከአንግሊካን ቤተክርስቲያን ኅብረት ጋር “በአንድነት ጎዳና በጋራ እንራመድ” በሚል ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት መደረጉ፣ እ.አ.አ በ 2020 ዓ. ም. በሦስት አብያተ ክርስቲያናት (ሉተራን-ሜኖናዊ እና ካቶሊክ) መካከል “ጥምቀት እና በክርስቶስ አካል ውህደት ፣ ቤተክርስቲያን” በሚል ርዕሥ ላይ የጋራ ውይይት ከተደረገ በኋላ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ ለእምነት እና ህገ-መንግሥት ምክር ቤት “ቤተክርስቲያን ወደ አንድ የጋራ ራዕይ” በሚል ርዕሥ ተዘጋጅቶ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ከታየ በኋላ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነተ አንቀጽ አስተምህሮ ጽ/ቤት ጸድቆ ምላሽ የተሰጠበት ሰነድ መዘጋጀቱ ይታወሳል።  

ሕይወትን ለማግኘት የሚደረጉ የጋራ ውይይቶችን በተመለከተ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በዚህ የውይይት ዘርፍ የክርስቲያኖችን ውህደት ለማገዝ ባዋቀረው ኮሚቴ በኩል ከምሥራቃዊ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና ከሌሎች የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኩል ለሚመጡት ተማሪዎች በጳጳሳዊ ዩኒቨርስቲዎች ነጻ የትምህርት ዕድልን ሲያመቻች መቆየቱ ይታወሳል። በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ለአርባ ተማሪዎች በጳጳሳዊ ዩኒቨርስቲዎች ነጻ የትምህርት ዕድል እና በካቶሊካዊ ኮሌጆች የመኖሪያ ሥፍራዎችን ማመቻቸቱ ይታወሳል። ይህም ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚመጡ ተማሪዎች ስለ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቂ ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማገዝ ተሞክሯል። የምዕመናን አስተያየት ሊያድግ የሚችለው በአንዳንድ ትላልቅ በዓላት እና መድረኮች መሆኑ ሲታወቅ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው እ.አ.አ. በ2016 ዓ. ም. በግሪክ ሌስቦ ከተማ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከክርስቲያኖች ውህደት ደጋፊ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቤርቶሎሜዎስ ጋር እና ከአቴን ከተማ ሊቀ ጳጳሳ፣ ከብጹዕ ኢሮኒሞስ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል። እንደዚሁም እ.አ.አ. በ2018 ዓ. ም. በጣሊያን፣ ባሪ ከተማ የልዩ ልዩ ሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሰላም የጋራ ጸሎት እና አስተንትኖ ማድረጋቸው ይታወሳል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያጠናክሩ ተግባራት እንዳይካሄዱ እንቅፋት ሆኖ ቢቆይም፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ከፍተኛ የመረዳዳት እና የአንድነት መንፈስ እንዲያድግ ማድረጉ ይታወቃል። በዓለማች ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው መከራ እና ስቃይ እንዲያበቃ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመላው ዓለም ምዕመናንን “በአባታችን ሆይ!” ጸሎት ማስተባበራቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሁል ጊዜ የሚያደርጉት ድጋፍ የክርስቲያኖችን ውህደት ለማጠናከር ብቻ ሳይሆን፣ በቫቲካን በሚገኙ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል ተሃድሶ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ያበረታታል።      

20 January 2021, 17:09