ፈልግ

ለዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም አገልግሎት ለዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም አገልግሎት 

ለዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም አገልግሎት

የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ አገልጋዮች ቅዱስ ኤሬኔዎስ ‹‹የእግዚአብሔር ክብሩ ሙሉ በሙሉ ሕያው የሆነ ሰው ነው›› በማለት እንደተናገረው፣ ወደፊት የምትራመድ፣ ደስተኛና ሕያው የሆነች አፍሪካ፣ የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥ ታደርጋለች፡፡ ቅዱስ ኤሬኔዎስ በመቀጠል እንዳለው “የሰው ልጅ ሕይወት ግብ እግዚአብሔርን መግለጽ ነው፡” ዛሬም ቢሆን፣ የቤተክርስቲያን ዋና ተግባር የወንጌልን መልእክት ለአፍሪካ ህብረተሰብ ማዳረስ እና ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያዩ መምራት ነው፡፡ ጨው ምግብን እንደሚያጣፍጥ፣ ይህ የወንጌል መልእክትም በቃሉ መሠረት የሚኖሩትን እውነተኛ ምስክሮች ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ የሚጓዙ ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይታረቃሉ፡፡ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው የብርሃን ምንጭ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ፣ እኛም ከሲኖዶስ አባቶች ጋር ሆነን “የአፍሪካ ቤተክርስቲያን የዕርቅ፣ የፍትህና የሰላም አገልጋይ፣ “የምድር ጨው” እና “የዓለም ብርሃን” እንድትሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን። ይኸውም የቤተክርስቲያን ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆንሽ የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ሆይ፣ የሰማዩ አባት ጠርቶሻልና ተነሺ ለሚለው ጥሪ ምላሽ እንድትሰጥ ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሁለተኛው የአፍሪካ ሲኖዶስ በቤተክርስቲያን ሕይወትና ተልእኮ ውስጥ ለእግዚአብሔር ቃል ስለመገዛት ጥሪ ከሚያደርገው ሲኖዶስ ቀጥሎ መካሄዱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ያ ሲኖዶስ እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር በቃሉ የሚጠራን ክርስቶስን የመረዳት አስፈላጊነት አውስቷል፡፡ በቃሉ አማካይነት እኛ ምእመናን ክርስቶስን መስማትንና የሁሉንም ነገር ትርጉም በሚገልጽልን መንፈስ ቅዱስ (ንጽ. ዩሐ. 16፡13) መመራትን እንማራለን፡፡ በመሠረቱ፣ “የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ማስተንተን በይበልጥ በክርስቶስ እንድንጸናና አገልግሎታችንን እንደ ዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም አገልጋዩች ሆነን እንድንመራ ያደርገናል”። ሲኖዶሱ እንደሚያስታውሰን “የክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ለመሆን፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በተግባር እንደሚያውሉት” (ሉቃ. 8፡21) መሆን አለብን፡፡ በእውነት መስማት ማለት መታዘዝና ማድረግ ነው፡፡ ፍትህና ፍቅር በሕይወት ውስጥ እንዲያብብ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ነቢያት ጥሪ በሕይወትና በህብረተሰብ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ከሕይወት፣ ከእምነትና ታማኝነት፣ ከአምልኮና ማህበራዊ ዝግጁነት ጋር በቀጣይነት የሚያጣምር ምስክርነት መስጠት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥና ማስተንተን ከእግዚአብሔር ጋር እንታረቅ ዘንድ ቃሉ በሕይወታችን ውስጥ ሰርጾ እንዲገባና እንዲለውጠን መፍቀድ ነው፤ እግዚአብሔር ከሰው ሁሉ ጋር እንድንታረቅ እንዲመራን መፍቀድ ነው፤ ይህም የግለሰቦችና የሕዝቦችን አንድነት ለመገንባት አስፈላጊ መንገድ ነው። በፊታችንና በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል በእውነትም ሥጋ ይልበስ!

ክርስቶስ የአፍሪካ ሕይወት ማዕከል፡ የዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም ምንጭ

ለሲኖዶሱ የተመረጡ ሶስት ዐበይት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም ዕርቅ፣ ፍትህና ሰላም ሲኖዶሱ ያለበትን “ነገረ መለኮታዊና ማህበራዊ ኃላፊነት” አሳይተዋል፤ እንዲሁም በቤተክርሰቲያን ሕዝባዊ ሚናና ዛሬ በአፍሪካ ስላላት ስፍራ እንዲያሰላስል አድርገውታል። “ዕርቅና ፍትህ የሰላም ሁለቱ ዋና መሠረቶች ስለሆኑ በተወሰነ ደረጃ የሰላምን ባህርይ ይወስናሉ ይባል ይሆናል”። ለራሳችን እያቀድን ያለው ሥራ ቀላል አይደለም፤ ይህም ሥራ ከቤተክርስቲያን ቀጥተኛ ኃላፊነት ወጣ ባለ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍና ከተጨባጭ ታሪካዊ ኃላፊነት ለማምለጥ በሚያስችል ነገረ መለኮታዊና መንፈሳዊ ግምት ውስጥ በመቀጠል ወደኋላ በማፈግፈግ ወይም በመሸሽ መካከል ያለ ይመስላል፡፡

“ሰላሜን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ይላል ጌታ፡፡ በመቀጠልም “እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ ዓይነት አይደለም” (ዩሐ.14፡27) ብሏል፡፡ ፍትህ የሌለበት የሰው ሰላም ከእውነት የራቀና ሀላፊ ጠፊ ነው፡፡ “እውነት በፍቅር” (ኤፌ. 4፡15) የሆነ የዕርቅ ፍሬ የሌለው የሰው ፍትህ ፍጹምና እውነተኛ ፍትህ አይደለም፡፡ በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር በታረቀ “በሰው ልጅ ቤተሰብ፣ በሰላም ማህበረሰብ” ውስጥ ወንድማማችነትን እንደገና ለመመሥረት ከተፈለገ የሰው ፍትህ ሁሉ መከተል የሚገባው መንገድ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ወደ እርሱ የሚመራንን “ሙሉ እውነት” መውደድ ነው (ንጽ.ዩሐ.16፡13)፡፡ ፍትህ ከቶውንም ምውት ወይም ከእውነት የራቀ ነገር አይደለም፡፡ ፍትህ በጽኑ የሰው ልጅ ውሳኔዎች ውስጥ ጸንቶ የሚገኝ መሆን አለበት፡፡ ፍትህንና የሁሉንም ሰው መብቶች የማያከብር በጎ ሥራ ሐሰት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ክርስቲያኖች በፍትህና በጽድቅ ሥራ መስክ መልካም ምሳሌ እንዲሆኑ አደራ እንላለን (ማቴ.5፡19-20)፡፡

ምንጭ፡ የአፍሪካ ታማኝነት በሚል አርእስት የቀድሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ “የአፍሪካ ታማኝነት” በሚል ርዕስ ያስተላለፉት የድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር፣ ከአንቀጽ 15-18 ላይ የተወሰደ።

14 January 2021, 13:03