ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ 

ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ፣ አይሁዳዊያን ወንድሞቻችንን ከአደጋ ለማትረፍ ብዙ ጥረት ማድረጋቸው ተነገረ

የቫቲካን መዝገብ ቤት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ በርካታ ሰነዶችን በያዘው “ፒዮስ 12ኛ እና አይሁዶች” በተሰኘው መጽሐፋቸው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ከጽሕፈት ቤታቸው ጋር በመተባበር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ አይሁዳዊያንን ከሞት አደጋ ማትረፋቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን አገር የታተመው እና የረጅም ጊዜ ጥናታዊ ምርምር ውጤት የሆነው የአቶ ዮሓን ኢኪስ መጽሐፍ በውስጡ የያዟቸው ሰነዶች የቫቲካን መዝገብ ቤት ታድሶ ለጥናታዊ ምርምር ሥራ ክፍት ከሆነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረጉትን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ሰነዶች የያዘ መሆኑ ታውቋል። በቫቲካን መዝገብ ቤት ውስጥ ቅድስት መንበር ከተለያዩ መንግሥታት ጋር የምታደርጋቸውን ግንኙነቶች የያዘ ሰነድ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሓን ኢክስ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ከረዳቶቻቸው ጋር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳዊያንን ከሞት አደጋ ለማትረፍ ያደረጓቸውን ጥረቶች የሚገልጹ ወደ አሥር የሚጠጉ ሰነዶችን በመጽሐፋቸው ውስጥ ማካተታቸው ታውቋል። መጽሐፉ ወደ አራት መቶ ያህል ገጾች ያሉት ሲሆን ጭብጡም ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ እ.አ.አ. ከ1938-1944 ዓ. ም. ድረስ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በኩል በየዕለቱ የሚቀርቡላቸውን የዕርዳታ ጥያቄዎች ለመመለስ ያደረጉትን ጥረቶች የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል። የታሪክ ምሁር እና የሥነ-መዝገብ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ ከቫቲካን ሬዲዮ ጣሊያንኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለማካሄድ እና የደራሲ ጆቫኒ ቦካቾ መንገድን ለመከተል ለምን እንደወሰኑ አስረድተዋል።

ስለ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሚናገሩ፣ በቁጥር ከ 800 ሺህ በላይ ሰነዶች በቫቲካን መዝገብ ቤት መኖሩን የተናገሩት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ አራት መቶ ገጾች ብቻ ባሉት መጽሐፋቸው ሁሉንም መግለጽ እና ማብራራት የማይቻል መሆኑን ተናግረው፣ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን በመምረጥ በአንድ ርዕሠ ጉዳዩ ላይ ከአንባቢያን እና ጓደኞቻቸው ጋር መወያየቱ መልዕክቱን በቀላሉ ማስተላለፊያ መንገድ ሆኖ እንደረዳቸው ገልጸዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ እና ግፍ በዝምታ ተመልክተዋል የሚለው አባባል ትክክል እንዳልሆነ ያብራሩት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ በማንኛውም ቤተ መዛግብት ውስጥ የማይገኙ እና እውነትን የሚገልጹ ሰነዶች በቫቲካን ቤተ መዛግብት ውስጥ መኖራቸው ተናግረው እነዚህ ሰነዶች ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ከአሥራ አንድ ረዳቶቻቸው እና በልዩ ልዩ አገራት ከሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች ጋር በመተባበር በየዕለቱ፣ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ በአውሮፓ ውስጥ የሚፈጸሙ ስቃዮችን ለማስወገድ እና የሚቀርቡላቸውን የዕርዳታ ጥያቄዎችን በቸርነት ሲመልሱ መቆየታቸውን የሚያስረዱ መሆኑን አብራርተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በወቅቱ ያከናውኑትን ሐዋርያዊ ተግባራት የሚተነትኑ አስደናቂ ሰነዶች በመጽሐፋቸው ውስጥ መጠቃለሉን የገለጹት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ በጣሊያን ሚላኖ ከተማ፣ በፕራግ ወይም በቡዳፔስት በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች የእርዳታ ጥያቄአቸውን በሮም ለሚገኙት ር. ሊ. ጳ. ያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም መሠረት በተለይ አይሁዳዊያንም በግልጽ እንደሚረዱት ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ የዕርዳታ ጥያቄአቸውን በቸርነት በመመለስ፣ ከሞት አደጋም በመታደግ ከጎናቸው መቆማቸውን በማያሻማ መንገድ ይረዱታል ብለዋል።

ቫቲካን የአይሁዳዊያንን እና የበርካታ ክርስቲያኖችን ጉዳይ በቅርብ ስትከታተል መቆየቷን ያስታወሱት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ ይህ ተግባሯ በስፋት የማይነገርላት መሆኑን አስታውሰው፣ የቅድስት መንበር የዕርዳታ ተግባሯን በማስመልከት ገለጻን የሚሰጡ በርካታ ሰነዶች በቫቲካን ቤተ መዛግብት ውስጥ መኖራቸውን አስረድተዋል። በወቅቱ ለሕዝቦች ስቃይ ሐይማኖት እና ዘር እንደ ዋና ምክንያት የሚወሰድ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ እ.አ.አ. በ1943 ዓ. ም. በሮም ከተማ በናዚዎች በኩል ጥቃት የደረሰባት አንዲት የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሴት፣ እናቷ የአይሁድ ዝርያ ያላት መሆኑን አስረድተው፣ የነፍስ አድን እርዳታን ለመጠየቅ ወደ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ መምጣቷን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ይህች እናት የነፍስ አድን እርዳታን ታግኝ አታግኝ ሰነዶች ባይገልጹም ነገር ግን ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ይህችን እናት በአንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ ተደብቃ ሕይወቷ እንዲተርፍ ማድረጋቸው የሚያስመሰግን መሆኑን እና ሌሎችም ተመሳሳይ እርዳታዎች ይደረጉ እንደነበር የሚያብራሩ በርካታ ሰነዶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ያዋቀሩት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ጦርነት ከሚካሄድባቸው እና የሕዝቦች ስቃይ ከበረታባቸው አካባቢዎች በቂ መረጃን ካለማግኘቱ የተነሳ ጭንቀት ውስጥ መውደቁን ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ አስታውሰዋል። እንግሊዞች፣ አሜሪካኖች እና ቅድስት መንበር መረጃዎችን መለዋወጥ መቻላቸው በመጽሐፋቸው መገለጹን የተናገሩት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ፣ የሕዝብ ሰቆቃ በሚታይባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ዲፕሎማቶች መካከል ፍሬያማ ትብብር የነበረ ሲሆን በማጎሪያ ካምፖቹ ውስጥ ስለሚከናወኑ አሰቃቂ ተግባራት ዜና ይደርሳቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ለምሳሌ በዋርሶ ከሚገኝ የቫቲካን ወኪሎች ወይም አንዳንድ ምስክሮች በኩል መረጃዎች የሚደርሱ ሲሆን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የሚደርሱ ብዙ መረጃዎችን ግን ማጣራትን የሚጠይቅ መሆኑን ዶ/ር ዮሓን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ከብሪታንያ፣ ከአሜሪካ፣ ከሶቪዬት ኅብረት ወይም ከሌሎች አገራት ጋር አለመወገናቸው የውግዘት ሰነድን እንዳያሳትሙ አድርጓቸዋል ያሉት ዶ/ር ዮሓን፣ ሶቪዬቶች በመጀመሪያ አካባቢ ጦርነቱን ከአሜሪካ እና ከብሪታንያ ጋር በመተባበር ማካሄዳቸው መረሳት እንደሌለበት አስረድተው፣ በጊዜው ቅድስት መንበር ከሶቪዬቶች ጋር በመተባበር በአገሮች ዘንድ ያላትን መልካም ስም ማጉደፍ አለመፈለጓን ገልጸው በዚህ አቋሟ በጦርነቱ ምክንያት ስቃይ እና መከራ የደረሰበትን የማንኛውንም አገር ሕዝብ ያለ ልዩነት ለመርዳት መቆሟን አስረድተዋል።

ለአስርተ ዓመታት የተወሰኑ ፕሮፖጋንዳዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛን የሂትለር ደጋፊ አድርገው ማቅረባቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ዮሓን፣ እነዚህ ፕሮፓጋንዳዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን አስረድተው ሌሎችም ወገኖች በተመሳሳይ መልኩ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ሮዝቬልት ከር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ማሰባቸውን አስታውሰው፣ ይህም በቫቲካን የዲፕሎማቲሲ ሥርዓት ውስጥ የማይታሰብ እና ከተለመዱት ፕሮቶኮሎች የተለየ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

አሜሪካዊያን አይሁዶች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በተጀመረው የዘር ስደት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ፣ አቋም እንዲወስዱ ቫቲካንን መጠየቃቸውን የገለጹት ዶ/ር ዮሓን፣ በጊዜው የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ጋስፓሪ የጽሑፍ መልስ እንዲሰጣቸው ማዘዛቸውን ገልጸው፣ አሜሪካዊያን አይሁዶች በበኩላቸው በካርዲናሉ መልስ የረኩ መሆናቸውን በመጽሔቶቻቸው በኩል ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል። አይሁዳዊያን እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ መብታቸውም እንዲጠበቅ ቅድስት መንበር ላደረገችው እገዛ “የእኛ ወንድሞች” በማለት መግለጻቸውን ዶ/ር ዮሓን ገልጸው፣

ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ፣ በኋላ ላይ ኤውጄኒዮ ፓቼሊ የተባሉት፣ በውጭ መንግሥታት ግንኙነት ክፍል ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት “አይሁዳዊን እንደ ማንኛውም ሌሎች ሕዝቦች ወንድሞቻችን ናቸው” ማለታቸውን ዶ/ር ዮሓን አስታውሰው፣ ሰነዱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በቅድስት መንበር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑን አስረድተዋል። ይህ መልዕክት ከዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1965 ዓ. ም. “Nostra Aetate” ወይም “የእኛ ዘመን” በመባል በሚታወቀው ሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ መጠቀሱንም አስታውሰዋል። በዚህ መሠረት ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ በመጀመሪያ የናዚ አስከፊ ሥርዓትን፣ ከዚያም ቀጥሎ የኮሚኒዝም ትልቅ ተግዳሮቶችን በር. ሊ. ጵጵስና ዓመታት መጋፈጣቸውን ዶ/ር ዮሓን አመልክተዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውሮፓ የነበረው የማኅበራዊ መገናኛ ፍጥነት ዝቅተኛ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ዮሓን፣ የባለሞያ ቁጥር እጅግ አነስተኛ እና በጊዜው የነበሩት የናዚ ጸጥታ ኃይሎች መረጃ እንዳይተላለፍ መከልከላቸውን ቅድስት መንበር እርዳታዋን ለተጎዱት በአግባቡ እንዳታደርስ ያደርግ እንደ ነበር እና ይህም ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛን እጅግ ያሳዘናቸው መሆኑን አስታውሰዋል። በግልጽ እንደሚታየው ብጹዕ አቡነ ባርቤታ ወይም ብጹዕ አቡነ ዴልአኳ እና ሌሎች የቅድስት መንበር ዕርዳታ አስተባባሪዎች በካርዲናል ማሊዮኔ እና በታርዲኒ የተመሩት ሌሎች ሰራተኞችም ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ በመሄድ በችግር ውስጥ የወደቁ ሕዝቦችን ለመርዳት 24 ሰዓት ሙሉ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ዘግይተው በመድረሳቸው ምክንያት ጥረታቸው ከንቱ መቅረቱን የቫቲካን መዝገብ ቤት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮሓን ኢኪስ አስረድተዋል።             

27 January 2021, 19:17