ካርዲናል ጋላገር ከኒውክለር የጦር መሳሪያዎች ነፃ የሆነ ዓለም መገንባት ያስፈልጋል አሉ!
ቫቲካን ከሌሎች አገራት ጋር የምታደገውን ግንኙነቶች በበላይነት የሚቆጣጥረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ካርዲናል ጋላገር እ.ኤ.አ. በጥር 22/2021 ዓ.ም ሥራ ላይ የሚውለውን የኒውከለር የጦር መሳሪያ እቀባ የተመለከተ ሕግ የቅድስት መንበር ያላትን ቁርጠኝነት በተመለከተ ከቫቲካን ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ ገለጹት “ዓለም አቀፍ ሰላምና ፀጥታ በጋራ የመጥፋት ስጋት ላይ የተመሠረተ ሊሆን አይችልም” ማለታቸው ተገልጿል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለብዙ አመታት ያሕል የኒውክለር የጦር መሳርያ እንዲወገድ ጥረት እያደረገች እንደ ሆነ ካርዲናል ጋላገር አክለው የገለጹ ሲሆን ቅድስት መንበር “የኒውክለር የጦር መሳሪያ መስፋፋት የምያግደው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን” አንደ ምትፈልግ ካርዲናል ጋላገር እክለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ እና በራሻ መካከል በአዲስ መልክ አገርሽቶ ሁሉቱን የዓለማችን ኃያላን የሚባሉ ሀገራት የኒውክለር የጦር መሳሪያ በአዲስ መልክ ለመታጠቅ የምደርጉት ሩጫ ሁለቱንም ሀገራት ፍጥጫ ውስጥ እንደ ከተታቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ ፍጥጫ ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር የዓለማችንን ሕዝቦች ለስጋት የዳረገ ክስተት እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1960ዎቹ በተከሰተው የቀዝቃዛው ጦርነት ሳቢያ ሁለቱም የዓለማችን ኃያላን ሀገራት የኒውክለር የጦር መሳሪያን በከፍተኛ ሁኔታ መታጠቅ መጀመራቸው የሚታወቅ ሲሆን በወቅቱ ይህንን ጅምላ ጨራሽ የሆነ መሳሪያ ለመታጠቅ የሚደርገው እሽቅድድም ለዓለማችን ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ የተነሳ መወገድ የሚገባው ፍጥጫ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቋሟን መገልጿ ይታወሳል።
በወቅቱ በመከናወን ላይ በነበረው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ መካከል ላይ ይህ ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሰባቸው በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ 23ኛ ይህንን በአሜሪካ እና በራሻ መካከል በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን የኒውክለር የጦር መሳሪያ ፍጥጫ ለማርገብ በማሰብ በላቲን ቋንቋ “Pacem in Terris” በአማርኛው “ሰላም በምድር ላይ ይሁን!” በሚል አርእስት ሐዋርያዊ መልእክት ለንባብ ማብቃታቸው የምታወስ ሲሆን በዚሁ ሐዋርያዊ መልእክት በእውነት፣ በፍትህ፣ በፍቅር እና በነጻነት ላይ የተመሰረተ ዓለማቀፍ ይዘት ያለው ሰላም መገንባት እንደ ሚገባ ጠንካራ የሆነ መልእክት ለመላው የክርስቲያን ማኅበርሰብ እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል በአዲስ መልክ የኒውክለር የጦር መሳሪያን በተመለከተ ቀድም ሲል ይህንን የጦር መሳሪያ በዓይነት እና በይዘት ለመቀነስ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1987 ዓ.ም ሁለቱም ሀገራት የገቡትን ስምምነት በተለይም አሜርካ የቀድሞ ፕሬዚዳን ዶናልድ ትራንፕ ውድቅ አድርገው የነበረ ሲሆን አሜርካ በአዲስ መልክ የኒውክለር የጦር መሳሪያን ለመታጠቅ የወሰነችው ውሳኔ ዓለማችንን ስጋት ውስጥ እየከተተ የመጣ ወቅታዊ እና አሳሳቢ ጉዳይ እንደ ሆነ በእየ ጊዜው ከምንሰማው ዘገባ ለመረዳት ይቻላል። ይህ አሜሪካ በተናጥል የወሰነችው ውሳኔ ሁለቱም ሀገራት የዛሬ 31 አመት ገደማ የፈረሙትን ስምምነት የሚሽር በመሆኑ ራሻ የሚያሳስባት ጉዳይ እንደ ሆነ በይፋ ማሳወቋ ይታወሳል።
ዓለማቀፍ ዘገባዎች እንደ ሚያመለክቱት በሁለቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት መካከል በአዲስ መልክ የቀዝቃዛው ጦርነት መከሰት መጀመሩን እየዘገቡ መሆናቸውን በስጋት በመግለጽ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ስጋቱ እንዲጨምር የሚያደረገው ክስተት ደግሞ ይህ ፍጥጫ ከሁለቱ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት ባሻገ በመሄድ የኒውከለር የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሌሎች ሀገራትን ሳይቀር በተለይም ቻይናን ጭምሮ ያለተገባ ውዝግብ ውስጥ ሊከታቸው እንደ ሚችል ከወዲሁ ግምት ተሰቶታል።
የአቶሚክ የጦር መሳሪያዎችን አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ለመጠቀም የሚደርገው ሽርጉድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስጨንቃት እና የሚያሳስባት ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጿ የሚታወስ ሲሆን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የኒውክለር የጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደርገው ሩጫ መጨረሻው አስከፊ የሆነ ጦርነት በመሆኑ በጥብቅ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ እንደ ሆነ አቋማቸውን በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ ላይ እንደ ሚገኙ ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለይም ደግሞ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ላይ (በ1945 ዓ.ም ማለት ነው) በጃፓን ሄሮሽማ እና በነጋሳኪ ላይ የተጣሉት አቶሚክ ቦንቦች በወቅቱ ያደረሱትን ከፍተኛ ጉዳት በማስታወስ ይህ አስከፊ የሆነ ጥቃት በድጋሚ በምድራችን ላይ መፈጸም እንደ ሌለበት በተደጋጋሚ መገለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ይህ በቀቡ የአሜርካው ፕረዝዳንት ዶንል ትራንፕ የኒውክለር የጦር መሳሪያን በዓይነት እና በይዘት የማስፋፋት እቀባን የተመለከተ ስምምነት በተናጥል ለማፍረስ መሞከራቸው ተገቢ እንዳልሆነ እና በተቃራኒው የዓለማችንን ሕዝቦች ለስጋት ያጋለጠ ጅምላ ጨራሽ የሆነ መሳሪያ በመሆኑ የተነሳ ይህንን የተናጥል ውሳኔ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትቃወመው ብቻ ሳይሆን የምታወግዘው ተግባር መሆኑን ከቅድስት መነበር የደርሰን ዜና ያመለክታል።
የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው!
ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል የሚያደርጉትን 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በኅዳር 09/2012 ዓ.ም አመሻሹ ላይ መጀመራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው ከኅዳር 09-12/2012 ዓ.ም በታይላንድ ቆያታ ካደረጉ በኋላ በመቀጠል “ሕይወትን ከጉዳት እና ከሞት አደጋ እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 12-16/2012 ዓ.ም ድረሰ የ32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ መዳረሻ አገር ወደ ሆነችው ጃፓን ማቅናታቸው ተገልጹዋል።
ቅዱስነታቸው በእዚህ በጃፓን በሚኖራቸው የአራት ቀን ቆያት የጃፓን ዋና ከተማ የሆነችውን ቶክዮን ጨምሮ፣ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት በኒውክለር የጦር መሣርያ ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን እና እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የሰው ልጆች ሕይወት የተቀጠፈበት አደጋ ተከስቶ የነበረባቸውን ኔጋሳኪ እና ሂሮስሺማን መጎብኘታቸው ከእዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጃፓን በእዚያው “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” በመባል በሚታወቀው የመታሰቢያ ስፍራ ለተገኙ ሕዝቦች በወቅቱ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት “የአቶሚክ ኃይልን ለጦርነት መጠቀምና ይህንን መሣሪያ ማከማቸት ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት በአጽኖት መግለጻቸው ይታወሳል።በጃፓን በነበራቸው የመጀመሪያው ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራን በጎበኙበት ወቅት ይህ “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ስፍራ ሞትና ሕይወት ፣ ኪሳራ እና ዳግም ልደት ፣ ሥቃይና ርህራሄ የተገናኙበት ስፍራ እንደሆነ” ገልፀዋል። ለጦርነት ዓላማ አቶሚክ ኃይል መጠቀምና ማከማቸት በራሱ ሥነ-ምግባር የጎደለው ተግባር መሆኑን ከታሪክ መማር እንደ ሚቻል ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።
እ.አ.አ በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም 8፡15 ደቂቃ ላይ በሂሮሺማ ከተማ ላይ በተጣለው የመጀመሪያው አቶሚክ ቦንብ ወቅት ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ማድርጉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚህም ጋር በተያያዘ መልኩ በእዚህ አቶሚክ ቦንብ አማካይነት በቅጽበት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል ደግሞ የአቶሚክ ቦንቡ ባደርሰው የጨረር አደጋ ቀስ በቀስ የ 70 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።
ከእዚህ ከተጣለው የአቶሚክ ቦንብ መሣርያ ፍንዳታ የተረፈው ብቸኛው ሕንፃ የጄንባኩ ዶም በመባል የሚታወቀው የፈረሰ ሕንጻ ሲሆን ይህ ሕንጻ በሰው ልጆች ላይ እና በአጠቃላይ በሰብዓዊነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ውድመት ያስከተለ እጅግ አስከፊ የሆነ አደጋ መሆኑን ለማስታወስ፣ ይህ ስፍራ ዛሬ በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ እምብርት ላይ ቆሞ ይታያል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትላንት እሑድ ኅዳር 14/2012 ዓ.ም ይህንን የሰላም መታሰቢያ ሥፍራ ለመጎብኘት ወደ እዚያው ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን በሂሮሽማ በሚገኘው የጄንባኩ ዶም በመባል የሚታወቀው የፈረሰ ሕንጻ ሥር ሆነው ባደረጉት ንግግር ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ይህንን በአቶሚክ ቦንብ መሣሪያ አማካይነት የተቃጣው አደጋ በተመለከተ ሲገልጹ “በእዚህ ነጎድጓድ መብርቅ በመሰለ ከፍተኛ ጥቃት እና የእሳት ፍንዳታ፣ ብዙ ወንዶች እና ሴቶች ፣ ብዙ ህልሞች እና ተስፋዎች ጠፍተዋል፣ ጥለውት ያለፉት ጥላ እና ዝምታ ብቻ፣ በቅጽበት ሁሉም ነገር በሞት ጥላ ተውጦ ነበር” ብለዋል።
የጥቃቱ ሰለባዎች እና ከአደጋው የተረፉ ሰዎች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ እዚያው ሥፍራ ያቀኑት በእዚህ አሳዛኝ አደጋ ተጎጅ ለሆኑ ሰዎች ያላቸውን ክብር ለመግለጽ እና እነርሱ በወቅቱ የነበራቸውን ጥንካሬ ምንጭ ለመገንዘብ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን “አሁን በሕይወት ለሌሉ እና የእዚህ አደጋ ሰላብ የሆኑ ሰዎችን ጩኸት እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ማሰማታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። የእዚህ የአቶሚክ ቦንብ ጥቃት ሰለባ የነበሩ ሰዎች “ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ፣ የተለያዩ ስሞች የነበሯቸው፣ የተወሰኑት ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገሩ እንደ ነበረ፣ ሆኖም ሁሉም በዚህች ክፉ እጣ ፈንታ በአንድነት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል ፣ በዚህች ሀገር ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሳይቀር እስከ መጨረሻው ድረስ ለዘለቄታዊነት ያለው ምልክት ጥሎ ያለፈ ክስተት ነው” ብለዋል።
የኑክሌር ጦርነት ሥነ ምግባር የጎደለው ነው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን በቀጠሉበት ወቅት በድጋሚ እንደ ተናገሩት “ለጦርነት ዓላማ የአቶሚክ ኃይልን ተጠቅሞ ጦርነት ማካሄድ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ በሰው ልጆች ክብር ላይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የጋራ መኖርያ ቤታችን በሆነች በምድራችን ላይ የሚፈጸም በደል ነው፣ የአቶሚክ ኃይል ለጦርነት መጠቀም ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር እንደመሆኑ መጠን፣ የአቶሚክ የጦር መሥርያ አምርቶ ማከማቸት በራሱ ሥነ ምግባር የጎደለው ተግባር ነው” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው “ስለሰላም ብቻ በማውራት ሰላምን ግን በተጨባጭ በምድር ላይ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ለማምጣት ባለመቻላችን ምጪው ትውልድ በእኛ ላይ እንደ ሚፈርድ” ገልጸው፣ አክለውም “ሰላም በእውነት ላይ የተመሠረተ ፣ በፍትህ የተገነባ ፣ በልግስና የተሟላ እና ነጻነትን የሚያስገኝ መሆን አለበት” ብለዋል።
በእጆቻችን ላይ የሚገኙ የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን እናስወግድ
“ይበልጡኑ ፍትሃዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ መገንባት ከፈለግን በእጆቻችን ላይ የሚገኙትን የኒውክለር የጦር መሣሪያዎችን ማስወገድ ይኖርብናል” በማለት በንግግራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው “ግጭቶችን ለመፍታት እና ለግጭቶች መፍትሄ ለመስጠት የኑውክሌር ጦርነት መሳሪያ ይህንን ስጋት ለመቀረፍ የሚያስችል ሕጋዊ የሆነ መስመር ነው ብለን በማሰብ የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን ለማጋበስ በምናደርገው ሩጫ የተነሳ እንዴት ሰላምን ማረጋገጥ እንችላለን?” በማለት ቅዱስነታቸው ጥያቄ አንስተዋል። “እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው የጦር መሳሪያዎችን በማስወገድ ብቻ አይደለም ፣ ምክንያቱም ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ማለት ስላልሆነ! በአንጻሩ ሰላም ማለት ከታሪክ እንደ ተማርነው እና እንደ ተረዳነው የፍትህ፣ የልማት፣ የአንድነት፣ የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን” ማለት በመሆኑ የተነሳ ጭምር ነው ብለዋል።
አስታውሱ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን በቀጠሉበት ወቅት ሦስት ሥነ ምግባራዊ እሳቤዎችን ማስታወስ እንደ ሚገባ በገለጹበት ወቅት እንደ ተናገሩት “ማስታወስ ፣ አብሮ መጓዝ ፣ መንከባከብ” የሚሉትን ሥነ ምግባራዊ እሳቤዎችን ያመላከቱ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተጨማሪም አጽኖት ሰጥተው እንደ ተናገሩት “የአሁኑ እና የወደፊቱ ትውልድ በእዚህ ስፍራ ምን እንደ ተካሄደ እንዳያስታወሱ ማደረግ አንችልም” በማለት አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል። “ይበልጡኑ ፍትሐዊ እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ መጻይ ጊዜ መገንባትን የሚያረጋግጥ እና የሚያበረታታ ያለፉ ክስተቶች ትውስታ አስፈላጊ ነው፣ የወንዶችና የሴቶች ንቃተ ሂሊና በተለይም በአገራት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሁሉ የሚያነሳሳ ሰፊ የሆነ የባለፉ ጊዜያትን ሁኔታ የማስታወስ ችሎታ አስፈላጊ ነው፣ ይህንን ለሁሉም ትውልዶች መናገር እና ማስተላለፍ የሚገባን ሕያው ትውስታ ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፣ መጪው ትውልድ እንደነዚህ ያሉ ክስተቶች በጭራሽ እንዳይከሰቱ ያለፈውን ዘግናኝ ክስተት ማሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።
በጋራ ወደ ፊት መጓዝ
“እኛ በመግባባት መንፈስ እና በይቅርታ እይታ በመታገዝ አብረን በጋራ ወደ ፊት መጓዛችንን እንቀጥል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በመቀጠል “ዛሬ የተስፋን አድማስ ለማስፋት እና በጨለማ በተሞላው ሰማይ ውስጥ ማብራት የሚችል የብርሃን ነጸብራቅ እንዲፈነጥቅ” ሁላችንም በጋራ መሥራ እንደ ሚጠበቅብን ቅዱስነታቸው ጨምረው ጥሪ አቅርበዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ተስፋ ማደረግ እንችል ዘንድ ልባችንን እንክፈት፣ የእርቅ እና የሰላም መሳሪያዎች እንሁን” ብለዋል።
“እርስ በእርሳችን አንዱ አንደኛውን መንከባከብ ከቻለ እና አንድ የጋራ የሆነ እጣ ፈንታ እንዳለን ከተገነዘብን ሰላምን እውን ማደረግ ይችላል” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ዓለማችን፣ እርስ በእርስ እንድትገናኝ እና እንድትተሳሰር ያደረገው አለማቀፋዊነት (globalization) ብቻ ሳይሆን በጋራ እየተጠቀምናት የምንገኘው ምድራችን ጭምር ናት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ዘርፎች ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው አንድ የጋራ የወደፊት ሕይወት እንዲኖረን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ በጋራ መሥራት” ይኖርብናል።
መጽሞ እንደገና መከሰት የለበትም
እ.አ.አ በነሐሴ 6/1945 ዓ.ም 8፡15 ደቂቃ ላይ የተጣለው አቶሚክ ቦንብ በሂሮሺማ ከተማ ላይ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ይህ ጥቃት የሄሮሺማን ከተማ ሙሉ በሙሉ እንድትወድም ማድርጉ የሚታወስ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነችው በእዚህች በሄሮሺማ ከተማ የሚገኘውን “የሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራን በጎበኙበት ወቅት ቀደም ሲል ያደረጉትን ንግግር ባጠቃለሉበት ወቅት ባቀረቡት መማጸኛ “በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ እና ሙከራዎች፣ ግጭቶች ምክንያት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ስም ሆነን ለእግዚአብሔር እና ለሁሉም መልካም እና በጎ ፈቃድ ያላችው ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ፣ አንድ ድምጽ ሆነን፡ ከአሁን በኋላ ጦርነት ያብቃ፣ በጦር መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች ያብቁ፣ በጭራሽ ከእዚህ የበለጠ መከራ እና ስቃይ በሰው ልጆች ላይ እንዳይደርስ እና የሰው ልጆች ስቃይ እንዲያበቃ” ለሁሉ ድምጼን አሰማለሁ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ማጠናቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።