ፈልግ

 ለሰላም ጸሎት የተደረገበት ዓለም አቀፍ ጉባኤ   ለሰላም ጸሎት የተደረገበት ዓለም አቀፍ ጉባኤ  

በአንድነት ጎዳና በጋራ መጓዝ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ

ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ በክርስቲያኖች ውሕደት የተወያየውን የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ “ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ” ለተባለ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ጽሑፋቸውን አበርክተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ታላቁ መታሰቢያ በዓል

በኒቂያ የተካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያን የዓለም ክርስቲያኖች እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2025 ዓ. ም. ለማክበር መቃረባቸው ይታወቃል። የክርስቲያኖችን ውሕደት አስመልክቶ የተወያየው የኒቂያው ጉባኤ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ325 ዓ. ም. መካሄዱ ይታወሳል። ለዚህ ጉባኤ መካሄድ በርካታ ታሪካዊ ምክንያቶች መኖራቸው ሲታወቅ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ ጉባኤው እንዲካሄድ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ነው። ይህን ማወቅ የሚቻለው ታሪካዊውን ዳራ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ማለትም በወቅቱ በክርስቲያኑ ዓለም ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት አስመልክቶ በክርስትና እምነቶች መካከል የተነሳውን ክርክር ለማስታረቅ ነው። በዚህ ውዝግብ መካከል ንጉሠ ነገሥቱ በክርስቲያን እምነት አንድነት ላይ በመመርኮዝ የግዛታቸውንም አንድነት ለማጠናከር የሚያደርጉት ጥረት ስጋት ውስጥ ከትቷቸው ነበር። ንጉሠ ነገስቱም በቤተክርስቲያኗ መከፋፈል ውስጥ ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ችግር መሆኑን ተመልክተው፣ የቤተክርስቲያኗ አንድነት የሚገኘው በፖለቲካ ጥረት ሳይሆን በሃይማኖታዊ መንገድ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ችለዋል። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ፣ ተቃራኒ ወገኖችን አንድ ለማድረግ በመፈለጋቸው በቁስጥንጥንያ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ በኒቂያ ከተማ ውስጥ የመጀመሪያውን የክርስቲያኖች ውህደት የሚያጠናክር ጉባኤ እንዲካሄድ አደረጉ።

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እና ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን በእምነት በመግለጽ በእስክንድሪያው የሃይማኖት ምሁር በሆነው በአርዮስ እየተስፋፋ የሚገኘውን የአሃዳዊነት ፍልስፍናዊ አገላለጽን ውድቅ አደረጉ። በዚህም ምክንያት የኒቂያ የሃይማኖት መግለጫ ለክርስትና እምነት የጋራ መሠረት ሊሆን መቻሉ ሲረጋገጥ፣ ጉባኤው የተካሄደው በክርስትና እምነት መካከል ሌሎች ተከታታይ መለያየቶች ከመፈጠራቸው በፊት መሆኑ ነው። የኒቂያው የኃይማኖት መግለጫ መንገድ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን አንድ በማድረግ ለክርስቲያኖች ውሕደት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። የቤተክርስቲያንን አንድነት ዳግም መመስረቱ በእምነቱ አስፈላጊ ይዘቶች ላይ የሚደረገውን ስምምነት የሚያመለክት ነው። ይህ ስምምነት ዛሬ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት እና ምዕመናን ማኅበረሰቦች መካከል ብቻ ሳይሆን ከጥንቷ ቤተክርስቲያን እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሐዋርያዊ መነሻ ጋር የሚደረግ ስምምነት ነው። በመሆኑም የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ታሪካዊነቱን በኅብረት ለማስታወስ እና ክርስትና እምነትን በታደሰ መንገድ ለማሰብ መልካም አጋጣሚ ይሆናል።

ሲኖዶሳዊነት እና የክርስቲያኖች ውህደት ተግዳሮት

የኒቂያው ጉባኤ የክርስቲያኖችን ውህደት ትልቅነት የሚገልጽበት ሌላ ገጽታ አለው። ይህም የጉባኤው ሰነድ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ወይም ሲኖዶስ ዘንድ ለውይይት ቀርበው ከአንድ ሲኖዶስ ብቻ መልስን ማግኘት የሚቻል መሆኑን ያስገነዝባል። ሲኖዶስ የሚለው የግሪክ ቃል በአንድ ጎዳና በጋራ መጓዝን ያመለክታል። በክርስቲያናዊ አገላለጽም ቢሆን ሲኖዶስ የሚለው ቃል፣ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው በጋራ የሚጓዙ ሰዎች አንድነትን ያመለክታል (ዮሐ. 14:6)። የክርስትና እምነት ከመጀመሪያው ጀምሮ መንገድ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ መንገድ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ ሰዎችም በዚህ መንገድ ለመጓዝ የተጠሩ ናቸው (ሐዋ. 9:2)። ዮሐንስ ክርዚስቶም “ቤተክርስቲያን” ለሚለው ቃል “የጋራ መንገድ” የሚል ትርጉም የሰጠ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያን እና ሲኖዶስ፣ በመዝ. ዳዊት ምዕ. 149 ላይ የተጠቀሰውን አገላለጽ የሚያመለክት ሲሆን ሲኖዶስ የሚለው ቃልም ቤተክርስቲያን ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጥንታዊ ቃል መሆኑን ያስረዳል።

የኒቂያው ጉባኤ ሲኖዶስ የሚለውን ቃል መላዋ ቤተክርስቲያን ከሚለው አገላለጽ ጋር በማዛመድ የሲኖዶስ ሂደት ተግባራዊ የሚሆነው በጋራ በሚወሰዱት ውሳኔዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ያሳስባል። የክርስቲያኖችን የውህደት መንገድ በሁለት ጠቃሚ መንገዶች እንመለከታቸዋለን። ከጥቂት ዓመታት በፊት የአብያተ ክርስቲያናት የእምነት እና የሕግ ምክር ቤት ባሳተመው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ብዙ አቅጣጫዎች ያሉትን የክርስቲያኖች ውህደት የጋራ አመለካከት ከቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ጋር በማዛመድ ይመለከተዋል። በዚህ ጥናት ውስጥ የሚከተለውን የጋራ ሥነ-ቤተክርስቲያን ትምህርት መግለጫን እናነባለን፥ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መላዋ ቤተክርስቲያን በሁሉም ደረጃዎች ማለትም በአካባቢያዊ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ አካባቢዎችም ቢሆን በብጹዓን ጳጳሳት ወይም በቤተክርስቲያን አባቶች ጉባኤ ትመራለች። ቤተክርስቲያን በሲኖዶሱ አባቶች ጉባኤ መመራቷ በእግዚአብሔር ምስጢረ ሥላሴያዊ ይዘት እና የቤተክርስቲያን መዋቅሮች የሚገለጹበትን የማህበረሰቡን ሕይወት እንደ ማህበረሰብ እንድንገነዘብ ያግዘናል” (ቁ. 53)። ይህ አመለካከት ከዓለም አቀፍ የሥነ-ቤተክርስቲያን ትምህርት ሰነድ በቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ተልዕኮ እና ሕይወት ጋር የሚጋራው ሃሳብ እንዳለው ያረጋግጣል። ሰነዱ በማከልም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት በየአገራቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል እያደገ መምጣቱ እና በሲኖዶስ አባቶች በኩል ዕውቅናን አግኝቶ ማለፉ ደስታን እንደፈጠረ ገልጿል (ቁ. 116)።

መንፈስ ቅዱስን በሲኖዶሱ እይታ ማድመጥ

ለክርስቲያኖች ውህደት ድጋፍን በሚሰጥ መንፈስ በመታገዝ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሲኖዶሱ አባቶች በኩል የሚደረገውን የክርስቲያኖች አንድነት ጥረት ለመደገፍ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው፣ ሲኖዶሱ የሚጓዝበትን መንገድ በጽናት ለመከተል እና እግዚአብሔር በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ከቤተክርስቲያን የሚጠብቀውን የጋራ ጉዞ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ምሥረታ 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ ጥቅምት 17/2015 ዓ. ም. ያስተላለፉት መልዕክት)። ከሁሉም አስቀድሞ ቅዱስ አባታችን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የሚያስጨንቃቸው፣ አንዳንድ መዋቅሮች እና ተቋማት መኖራቸው ሳይሆን፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሚና መሠረታዊ ጠቀሜታው የጋራ መደማመጥ እንዲኖር ስለሚያደርግ፣ የጋራ ውይይት በምናደርግበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረንን በጥንቃቄ ማድመጥ ነው (ወደ ሕልማችን እንመለስ ገጽ 97)። በዚህ መንፈሳዊ አገላለጽ መሠረት በሲኖዶስ እና በዴሞክራሲያዊ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካከል ያለውን ልዩነት መገነዘብ እንደሚቻል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሚገባ ሲገልጹ፥ በዴሞክራሲያዊ የአሠራር ሂደት፣ ውሳኔ ላይ የሚደረሰው የብዙሃኑን ድምጽ በመስማት ሲሆን የጳጳሳት ሲኖዶስ ግን ዘላቂ እና አስተማማኝ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመታገዝ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለታቀፈ እያንዳንዱ ምዕመን ሕይወት ዋጋን ሰጥቶ በማሰብ ወደ አጠቃላይ ውሳኔ ላይ መድረስን ይጠይቃል። ስለዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ እንደ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድርድር ወደ ጋራ ውሳኔ የሚደረስበት ሳይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን ለማድመጥ ራስን በማዘጋጀት በሐዋርያዊ ቆራጥነት፣ በወንጌላዊ ትህትና እና በጸሎት በመተማመን በመንፈስ ቅዱስ መመራትን ይጠይቃል (የቤተሰብ ሲኖዶስ፤ እ.አ.አ. ጥቅምት 5/2015 ዓ. ም.)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ለብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚሰጡትን ትርጉም በቀላል መንገድ መረዳት የሚቻል ሲሆን፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥም ለመሠረታዊነቱ እና እጅግ አስፈላጊነቱ ቅድሚያን በመስጠት መረዳት ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን ማለት በጋራ የሚጓዝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማለት ነው፤ የጳጳሳት ሲኖዶስ መኖር በራሱ በቂ አይደለም። ነገር ግን የጳጳሳት ሲኖዶስ መሆን ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያንም በውስጧ ጥልቅ የሆነ መጋራት እንዲኖራት ያስፈልጋል። በመሪዎች እና በምዕመናን መካከል፣ በምዕመናን እና በመሪዎች መካከል ሕያው የጋራ ውይይት ሊኖር ይገባል (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ ሐምሌ 5/2019 ዓ. ም. በዩክሬን ለግሪክ-ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)። ስለዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን ዋና አካል በመሆኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን የአገልግሎት ሥልጣን ተዋረድን በሚገባ ለመረዳት ያግዛል። በቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ባለስልጣን አገልጋዮች ተብለው ይጠራሉ። ምክንያቱም ሲኖዶስ የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ፣ ከሁሉም የሚያንሱ የሚለውን ትርጉም ያንጸባርቃል። (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ምሥረታ 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ ጥቅምት 17/2015 ዓ. ም. ያስተላለፉት መልዕክት)። ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይህ አገላለጽ በተለይም ለቅዱስ ጴጥሮስ ተወካይ፣ በጳጳሳት ሲኖዶስ በምትመራ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትክክለኛ ትርጉምን ለማግኘት ያስችላል ማለት ነው። (ር. ሊ. ጳጳሳት የመላዋ ቤተክርስቲያን መሪ በመሆናቸው  ብቻቸውን እንደሆኑ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም። በቤተክርስቲያን ውስጥ ከተጠመቁት መካከል እንደ አንዱ፣ ከጳጳሳት መማክርት መካከል እንደ አንዱ በማየት በተጨማሪም የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን፣ የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመምራት ቤተክርስቲያናትን በሙሉ በፍቅር ለመምራት የተጠራ ነው። (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ምሥረታ 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ ጥቅምት 17/2015 ዓ. ም. ያስተላለፉት መልዕክት)።

ስለዚህ የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እይታ ግልጽ ነው። ለቅዱስነታቸው በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሲኖዶስ መርሆ እና ቤተክርስቲያንን የሚመራት ጳጳስ አገልግሎት ከፍተኛ እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው። ቤተክርስቲያንን የሚመራ ር. ሊ. ጳጳሳት በአብያት ክርስቲያናት መካከል እርቅ እንዲወርድ በማድረግ የሚያበረክተው አተዋጽዖ ከፍተኛ ነው። (ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ. ሰኔ 27/2015 ዓ. ም. ለቁንስጥንጢንያ ፓትሪያርካዊ ልዑካን ካሰሙት ንግግር)። አንድን ቤተክርስቲያን በሲኖዶስ ደረጃ ለማስተዳደር እና ለማሳደግ የሚደረጉ ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ጥረቶች የአብያተ ክርስቲያናትን ውህደት ለማምጣት፣ ስጦታዎችን ለመለዋወጥ፣ መሠረታዊ የጋራ ውይይቶችን ለማካሄድ እና አንዱ ከሌላው ለመማር የሚያግዝ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስምረው ይገልጻሉ። በመሆኑም እንደ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስተያየት፣ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወንድሞች ጋር በምታደርገው የጋራ ውይይት አማካይነት በጳጳሳቶቻቸው መካከል ያለውን አንድነት እና ሲኖዶዳዊ ትርጉሙን ለመማር ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል። (ከወንጌል የሚገኝ ደስታ ቁ. 246) ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወንድሞች ጋር የሚደረገው የጋራ ውይይት ከዚህ በተጨማሪም የክርስቲያኖችን የውህደት አቅጣጫን በተመለከ እጅግ ጠቃሚ በሆነ ሲኖዶሳዊ ውይይቶች ላይ መሠረት ያደረገ ነው።

በካቶሊክ እና ኦርቶዶክስ ውይይት ውስጥ ሲኖዶሳዊነት ቅድሚያ ይሰጠዋል

በዚህ የውይይት መድረክ እ.ኤ.አ. በ 2007 ዓ. ም በራቨና በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ጠቃሚ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን የቤተክርስቲያናቱ ቅዱስ ምስጢራት ባህሪ እና ቀኖናዊ ስምምነቶችም ጸድቀዋል። እንደዚሁም በቤተክርስቲያን ኅብረት እና ስልጣን ላይ መግባባት ታይቶበታል። ከሥነ-መለኮት አንጻር በዚህ ሰነድ ውስጥ “የጋራ መግባባት” እና “ሥልጣን” ፣ “ሲኖዶሳዊነት” እና “ቀዳሚ መሪነት” የሚሉት ቃላት ማብራሪያን አግኝተዋል። ሲኖዶሳዊነት እና ቀዳሚ መሪነት የሚከናወነው በቤተክርስቲያን ሦስት መሠረታዊ የሕይወት ደረጃዎች፣ ማለትም በአከባቢያዊ ቤተክርስቲያንን ፣ በክልል ደረጃ ፣ እርስ በእርስ የተሳሰሩትን የተለያዩ አካባቢያዊ አብያተ ክርስቲያናት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን የሚመለከት ነው። ይህም ወደ ዓለም ሁሉ የሚዘልቅ እና ሁሉንም የአከባቢ አብያተ ክርስቲያናትን ያካተተ ነው። በተጨማሪም ሲኖዶሳዊነት እና የበላይነት በሁሉም የቤተክርስቲያን የሕይወት ደረጃዎች ላይ የሚታገዝ መሆኑ አፅንዖት ተሰጥቶታል። ይህ በተጨባጭ ሲታይ በሁሉም ደረጃዎች መሪ መኖር አለበት ማለት ነው። በአከባቢ ደረጃ ኤጲስ ቆጶስ ለካህናት እና ለመላው የእግዚአብሔር ህዝብ የሀገረ ስብከቱ መሪ ነው። በክልል ደረጃ ፣ የሜትሮፖሊታን አውራጃ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ መሪ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሮም ር. ሊ. ጳጳሳት የብዙ አከባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን መሪ ሲሆን በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ደግሞ የቁስጥንጥንያው የክርስቲያኖች ውህደት ደጋፊ ፓትርያርክ ተመሳሳይ ሚና ይጫወታሉ ማለት ነው። በማጠቃለያም ሰነዱ የኮሚሽኑን የይሁንታ ስሜት የሚገልፅ ሲሆን የቤተክርስቲያን የኅብረት ፣ የመግባባት እና ስልጣን በሚል መሪ ሃሳብ ላይ የቀረቡት ነፀብራቆች “በውይይታችን ውስጥ አዎንታዊ እና ጉልህ እድገት” እና “ጠንካራ መሠረት” ያላቸው ናቸው።

የክርስቲያኖች ውህደት እርቅ በሲኖዶስ እና በቀዳሚ መሪነት መካከል

ከሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ከካቶሊክ እና ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በስፋት መማር የሚቻል መሆኑን መረዳት ይቻላል። በአንድ በኩል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምታስተዳድራቸው የቤተክርስቲያን ተቋማት ውስጥ የሲኖዶሳዊነት እውቀት በሚገባ እንዲታወቅ እና ይህም በሥነ-መለኮታዊ አገላለጽ እጅግ አስፈላጊ እና የሚቻል መሆኑን፣ በተዋረድ መርሆ እና በሲኖዶሳዊ ማህበረሰብ መርህ መካከል ተአማኒነት ያለው ትስስር እንዲኖር እና ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወንድሞች ጋር ውይይቶችን ለማካሄድ ይረዳል። ሲኖዶሳዊነትን ማጠናከሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለከፍተኛ የአብያተ ክርስቲያናት ውህደት ዕውቅናን መስጠት እንድትችል ለማድረግ አስፈላጊ አስተዋጽኦን እንደሚያደርግላት ማወቅ ይገባል። በተለይም በተወሰኑ አካባቢዎች የሚታየውን ወደ ኋላ የመቅረት አዝማሚያን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህ ደረጃ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በደንብ የዳበረ ሲሆን ምክንያቱም ትላልቅ የሀገረ ስብከት ከተሞች ቀደም ባሉት ዘመናት ውስጥ አስፈላጊ ሥራዎችን መስራት ስለቀጠሉበት እና እ.ኤ.አ. በ 325 ዓ. ም. በኒቅያ የተካሄደው የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ውህደት ምክር ቤት ጉባኤ እና እ.ኤ.አ. በ451 ዓ. ም. በተካሄደው አራተኛው የኬልቄዶን ጉባኤ ጠቃሚ ውሳኔዎችን በማስተላለፉ ነው። በዚህ ረገድ ፣ ታዋቂው ሐዋርያዊ ቀኖና ቁ. 34 በምስራቅና በምዕራብ ጥንታዊት ቤተክርስቲያን እውቅና የተሰጠው በአከባቢው ባሉ የአከባቢ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያስተካክል እና በሲኖዶሳዊነት እና በቀዳሚ መሪነት መካከል ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት ያለው መሆኑ መታወስ ይኖርበታል። “የእያንዳንዱ አውራጃ ኤጲስ ቆጶሳት በመካከላቸው ያለውን የመሪነት ሥልጣን ለይቶ ማወቅ እና እንደ ራሳቸው አድርገው ሊቆጥሩት እና ያለ እርሱ ፈቃድ ምንም ነገር ማድረግ የማይችሉ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ጳጳስ ማድረግ የሚችለው፣ ሀገረ ስብከቱን የሚመለከተውን ጉዳይ እና በእርሱ ላይ ጥገኛ የሆኑት ግዛቶች ላይ ብቻ ነው። ሊቀ ጳጳሳቱ ግን ያለ ሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት ፈቃድ እና ስምምነት ምንም ማድረግ አይችልም። በዚህ መንገድ ስምምነት ሁል ጊዜ ያሸንፋል፤ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ የተመሰገነ ይሆናል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአንድ አገር ውስጥ ባሉ የአውራጃ ቤተክህነት፣ በተለይም በምክር ቤቶች እና በጳጳሳት ጉባኤዎች ደረጃ ማሻሻል ያለባት ብዙ ነገሮች እንዳሏት ይገነዘባሉ። ይህን በማስመልከት ሲናግሩ፥ “አንዳንድ ጥንታዊውን የቤተክርስቲያን ደንቦችን በማቀናጀት እና በማዘመን ምናልባትም በእነዚህ መንገዶች አማካይነት የአንድነት ጥያቄዎችን የበለጠ ለማሳካት ማሰብ አለብን” ብለዋል።

የሲኖዶስ ቅዱስ ቁርባናዊ አፈጣጠር የቤተክርስቲኢያን መሪነት 

እኛ ካቶሊኮች የሮማውን ጳጳስ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኑ እንዳቀረበው ስጦታ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የክርስትና እምነቶች አንድነታቸውን ለማወቅ እንደ መስዋዕት የሚያግዝ እና በሚጓዙበት ጎዳና ላይ ለአንድነት ሕይወት የሚያቁበት ነው። ይህንን በአሳማኝ መንገድ ለማሳየት የሮማው ር. ሊ. ጳጳሳት የበላይነት በቀላሉ በሕግ አባሪነት የሚገለጽ ሳይሆን ለቤተክርስቲያናዊ ቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓት ተጨማሪ ሳይሆን ነገር ግን በትክክል በእርሱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አፅንዖት መስጠት አለብን። ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ማኅበረሰቦችን ለማገናኘት የተፀነሰች ቤተክርስቲያን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን አንድነቷን የሚያረጋግጥላት ጠንካራ አገልግሎት ያስፈልጋታል። የሮማው ጳጳስ የበላይነት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በመጨረሻ ትንታኔአቸው በግልጽ እንዳመለከቱት፣ ከቅዱስ ቁርባን ጀምሮ መገንዘብ ያለበት እና በቅዱስ ቁርባን ስሜት ውስጥ በመሆን እንደ አፍቃሪ መሪ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የቅዱስ ቁርባን ኅብረት እውን እንዲሆን ለማስቻል ያለመ የመጀመሪያ ደረጃ ነው።

ስለሆነም የቤተክርስቲያን ቀዳሚ መሪነት ሆነ ሲኖዶሳዊነት ጥልቅ የሆነ የቅዱስ ቁርባን ሥነ-ሥርዓታዊ ባሕርይ ያላቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ቤተክርስቲያንም ሲኖዶስ ሆና ክርስቲያኖች የቅዱስ ቁርባንን በዓል ለማክበር ከሚሰበሰቡበት ሁሉ በላይ መሆኗ ዓለም አቀፉ የነገረ መለኮት ምክር ቤት በትክክል አፅንዖትን መስጠቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እድገት የሚያገኘው ከቅዱስ ቁርባን በሚያገኘው ድጋፍ መሆኑን ያሳያል። (ቁ. 47) ሲኖዶሳዊነት በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችል ምንጭ ያለው በመሆኑ መሠረታዊ የሆነ መንፈሳዊ ልኬትን ያቀርባል። እንደ ምክር ቤቶች እና እንደ ጳጳሳት ሲኖዶስ ያሉ ጉባኤዎች ብዙውን ጊዜ የሚከፈቱት በቅዱስ ቁርባን አከባበር እና ቀደም ሲል እንደተደነገገው ወንጌልን በከፍታ ቦታ ላይ ማስቀመጥን የሚደነግጉ፣ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በቶሌዶ ከተካሄዱት ጉባኤዎች ጀምሮ እስከ 1984 ዓ. ም (እ.አ.አ) በተካሄዱት የብጹዓን ጳጳሳት ስያሜ ሥነ-ስርዓቶች ድረስ ነው። 

ሲኖዶሳዊ የክርስትና ባህል መነቃቃት ያለበትን የበለፀገ ቅርስ አካቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.ኤ.አ. በ 2022 የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ በሲኖዶሳዊ ጭብጥ ላይ ውይይት እንዲደረግ የወሰዱት ውሳኔ መልካም ከመሆኑ በተጨማሪ በሲኖዶስ ለምትመራ ቤተክርስቲያን ህብረት፣ ተሳትፎ እና ተልዕኮ አስፈላጊ ነው። ይህ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ አስፈላጊ ክስተት ከመሆን ባለፈ ትርጉም ያለው የክርስቲያኖች ውህደት መልዕክትን ያካትታል። ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ የክርስቲያኖችን ውህደት የሚያበረታታ እና በጥልቀት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ስለሆነ ነው።

20 January 2021, 00:54