ፈልግ

ካርዲናል ፓሮሊን፣ የአየር ንብረት ለውጥ አዳዲስ የልማት ሞዴሎችን ለመፍጠር ያግዛል አሉ።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ በሚል ርዕስ በያዝነው አዲሱ የውሮፓዊያኑ ዓመት 2021 ዓ. ም. በሆላንድ በተዘጋጀው ጉባኤ መክፈቻ ላይ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስም በላኩት መልዕክት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለው፣ ይህም በድሆች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቋቋም እና ለአደጋው ተጋላጭ የሚሆኑትን ከመከላከያ ዘዴ ጋር ለማላመድ ይጠቅማል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መከላከል አዳዲስ የልማት ሞዴሎችን ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል እንደሚሰጥ የገለጹት ካርዲናል ፓሮሊን፣ ከዚህም በተጨማሪ የሰዎችን የኑሮ ደረጃን፣ የጤና ሁኔታን፣ የሕይወት ዋስትናን እንደሚያሻሽል እና የሥራ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሆላንድ አገር ከጥር 17-18/2013 ድረስ ለሚካሄድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመወከል የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዝግጅት ወደ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP26)

በሆላንድ እንዲካሄድ የተወሰነው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዚህ በፊት እ.አ.አ በመስከረም ወር 2019 ዓ. ም. በኒውዮርክ ከተማ ከተካሄደው ጉባኤ በኋላ የታዩትን እድገቶች በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ እ.አ.አ ከኅዳር 1 – 12 በሚደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ትንተናን ለመስጠት  ያለመ መሆኑ ታውቋል። መጭውን ጉባኤ በግላስጎው ከተማ ለማዘጋጀት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት አስተባባሪዎች፣ የአየር ንብረት ለውጦችን አዳዲስ የልማት ሞዴሎች ተጠቅሞ በመቋቋም በእርሻው ዘርፍ አጥጋቢ ውጤቶችን ማግኘት እንዲቻል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ እርዳታን እንዲያደርግ ተማጽነዋል። 

የካርቦን ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ፈጣን እርምጃ መውሰድ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቪዲዮ መልዕክታቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት በዘመናችን ውስጥ በጋራ ጥቅም ላይ የመጣ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተው፣ የካርቦን ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ አደጋውን ለመከላከል ከሚዘረጉት ዘዴዎች ጋር መላመድ እና የመቋቋም አቅምን ከማሳደግ ጋር ተዳምሮ አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለማስቀረት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለማከናወን ስነምግባራዊ የሕሊና አስገዳጅነት ሊኖር ያስፈልጋል ብለው፣ ምክንያቱም ጎጂ የሆኑ የአየር ንብረት ለውጦች በቅድሚያ የሚያጠቁት ለአደጋ የተጋለጡ ድሆችን እና መጭውን ትውልድ መሆኑን አስረድተዋል። የአየር ንብረት ለውጡ በሚያስከትለው አደጋ ዝቅተኛ ሃላፊነት ያላቸው ድሃው ማኅበረሰብ እንደሆነ አስረድተው፣ ድሃ ማኅበረሰብ አደጋውን የመቋቋም ዕድሉ አነስተኛ ስለሆነ እና የሚኖሩትም ለአደጋው በተጋለጡ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች መሆኑን አስታውቀዋል። 

ተጨማሪ የአደጋ ቅነሳ እና የማላመድ እንቅስቃሴዎች

የአየር ንብረት ለውጡ በሰው ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ የማላመድ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ እንደሚያስፈልግ የጠየቁት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ለረጅም ዘመን የሚያገለግል አዳዲስ የልማት ሞዴሎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ መዘርጋት እና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ፣ ድህነትን ለመዋጋት የሚደረገውን የጋራ ጥረት ማስተባበር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል በማከልም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሚገባ ለመማር እንደተቻለው የጋራ ጥረት ካልታከለበት የትም መድረስ የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል።     

ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር ሊኖር ያስፈልጋል

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የቪዲዮ መልዕክታቸውን በመቀጠል፣ “የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ዘላቂነት ያለው ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር፣ አደጋውን ለመቋቋም የሚያግዝ ቴክኖሎጂን ማሳደግ፣ በአቅም ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ፣ እነዚህን ፍትሃዊ የሆኑ ተግባራትን ለአደጋው ተጋላጭ ወደ ሆኑት ሀገራት ማስተላለፍ ይቀጥላል” ብለዋል። የመጀመሪያ ደረጃ እንቅስቃሴን ማድረግ እንደሚቻል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ባለፈው መስከረም ወር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ መልዕክት መላካቸውን ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰው፣ የቅዱስነታቸው መልዕክት፣ በማኅበረሰቡ መካከል የደኸዩትን ወደ ጎን ከሚያደርግ ራስ ወዳድነት፣ የብሔርተኝነት ስሜት፣ ግለሰባዊ አመለካከቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ሁለገብነትን ማጎልበት ፣ የታደሰ ዓለም አቀፍ የጋራ ሃላፊነትን በተግባር መወጣት ላይ የሚያተኩር መሆኑን አስታውሰዋል።

የሕይወትን አጠቃላይ ገጽታ ለማሻሻል ዕድሎችን ማመቻቸት

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምኞት ለአየር ንብረት ለውጥ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ጠቅላላ የሰው ልጅ የሕይወት ደረጃን፥ ጤናን፣ የመጓጓዣ እና የኃይል አቅርቦትን፣ የደህንነት ዋስትናን እና አዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር መሆኑን ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል። እነዚህን ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተግባራዊ ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ነጻነት፣ በቂ ጥበብ እና ቴክኖሎጂዎችንም በመምራት እና በማንቀሳቀስ ወደ አዲስ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ሁለገብ የእድገት ደረጃ ለመድረስ የሚያስችል በቂ ችሎታ መኖሩን አስረድተው፣ እነዚህን ዕቅዶች ሃላፊነትን ወስዶ በተግባር ለመግልጽ የፖለቲካ ፍላጎት መኖሩን ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል። 

26 January 2021, 11:28