በቫቲካን የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል ስምሪት 515ኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን ተከበረ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ጁሊዬስ 2ኛ፣ ከስዊስዘርላንድ የሚላኩ የክቡር ዘብ አባላት ቅድስት መንበርን እንዲጠብቁ በማለት እ.አ.አ በ 1506 ዓ. ም. ማቋቋማቸው ይታወሳል። በቫቲካን የተሰማራው የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል ቁጥር በዓለም ትንሹ ነው ተብሏል። በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል ከዋናው የስዊዘርላንድ መከላከያ ሠራዊት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ሲታወቅ፣ ቃለ መሐላን በማድረግ ታማኝነቱን ለር. ሊ. ጳጳሳት በመግለጽ አገልግሎቱንም ለካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል። የመሐላ ሥነ-ሥርዓቱ በየዓመቱ እ.አ.አ ግንቦት 6 ቀን የሚፈጸም ሲሆን፣ ይህም እ.አ.አ 1527 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቀለሜንጦስ 7ኛን ከጥቃት ለመከላከል ሲሉ የተሰው 150 የስዊዘርላንድ የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል የሚታወሱበት ዕለት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ቀለሜንጦስ 7ኛ በ22 የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል በመታጀብ፣ በቫቲካን ድንበር አካባቢ በሚገኝ "ካስትል ሳንት አንጄሎ" በሚባል ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብተው ከለላን ማግኘታቸው ይታወሳል።
ዘቦቹ ከስዊዘርላንድ የተመረጡበት ምክንያት
በመካከለኛው ዘመን ስዊዘርላንድ በአውሮፓ ውስጥ በጣም አስተማማኝ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማቅረብ የምትታወቅ አገር መሆኗ ይታወሳል። ይህን የተገነዘቡት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ጁሊዬስ 2ኛ ለቅጥረኛ ወታደሮቹ አድናቆታቸውን ማሳየታቸው ይታወሳል። የፈረንሳይ ንጉሥም በበኩላቸው ቤተመንግሥታቸውን የሚጠብቁላቸው 200 ቅጥረኛ ወታደሮችን ከስዊዝወርላንድ ማስመጣታቸው ይታወሳል። 150 ቅጥረኛ ወታደሮች ረጅም መንገድ በእግር ከተጓዙ በኋላ እ.አ.አ. ጥር 21/1506 ዓ. ም. ወደ ሮም መድረሳቸው ይታወሳል።
ዛሬ የስዊዘርላንድ የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል በቫቲካን ውስጥ
ቅድስት መንበር እ.አ.አ. በ2015 ዓ. ም. ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት በቫቲካን ውስጥ በጥበቃ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ የስዊዘርላንድ የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል ቁጥር ከ110 ወደ 135 ከፍ ማለቱ ሲታወቅ፣ ምልምሎቹ ወደ ቫቲካን ከመድረሳቸው በፊት በቂ ስልጠና በትውልድ አገራቸው ስዊዘርላንድ የሚሰጣቸው መሆኑ ታውቋል። ወደ ሮም ከመጡ በኋላም ለአገልግሎት የሚያበቃቸው የአምስት ሳምንታት ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ቀጥሎም የጥንቱ ቅጥረኛ የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል በ16ኛ ክፍለ ዘመን ይገለገሉባቸው ከነበሩ የጥበቃ መሣሪያዎች ጋር ልምምድ አድርገው ከጨረሱ በኋላ ወላጆቻቸው እና ር. ሊ. ጳጳሳት በሚገናኙበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ መሆናቸው ታውቋል።
ዛሬ በቫቲካን ውስጥ የሚገኙት የስዊዘርላንድ የስዊዘርላንድ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ ኃይል ከሌሎች ጳጳሳዊ ዘብ ጠባቂዎች ጋር በመተባበር፣ በቫቲካን ውስጥ ሆነ ከቫቲካን ውጭ፣ ር. ሊ. ጳጳሳት በሚንቀሳቀሱባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ አገልግሎት በማቅረብ ላይ መገኘታቸው ይታወቃል።