ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣  

ቅድስት መንበር፣ የሁሉንም ብልጽግና የሚያረጋግጥ ገንቢ አካሄድ እንዲኖር አሳሰበች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣ በዓለም ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ወደ ተሻለ ማኅበረሰብ ለመድረስ የሚያደርገው ጉዞ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። በጀኔቭ የተዘጋጀው 15ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት የሚኒስትሮች ጉባኤ “ብልጽግና ለሁሉ ሰው” ይረጋገጥ የሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት መሪ ቃል ያለው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓርብ ታኅሳስ 2/2013 ዓ. ም. በሁለተኛው ዙር በተካሄደው የጉባኤው የስምምነት ሰነድ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ስብሰባን የተካፈሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ ጉባኤው ዓለማችን ከገባችበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመውጣት ጥረት እየተደረገ ባለበት ባሁኑ ጊዜ፣ ውጤታማ የሆኑ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ትብብሮችን ከዘላቂ ውጤቶች ጋር በማስተባበር በተለይም በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም መሠረት የካሬቢያ ደሴት በሆነችው ባርባዶስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ከሚያዝያ 25-30/ 2021 ዓ. ም. የሚካሄደው 15ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ፣ የልማት ማኅበረሰቡ የ2030 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ ሰነድ ለማዘጋጀት ቀዳሚ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። 

በተ. መ. ድ. የንግድ እና ልማት ተቋም፣ ብልጽግናን ለሁሉ ለማድረስ ይሠራል

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ተቋም፣ በማደግ ላይ ላሉት አገሮች ድምጽ በመሆን ዘላቂ የሆነ ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ተሃድሶ ሥርዓትን ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት ዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ሥርዓት ለእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚያገለግል፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የኤኮኖሚ ሥርዓቱ ዘላቂነት እንዲኖረው አድርጓል ብለዋል።

“ብልጽግና ለሁሉም” የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ተቋም መሪ ቃል ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ ኮቪድ-19 ያስከተለው የወቅቱ ቀውስ ከገንዘብ አቅም ወደ ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ቀውስ ቢሸጋገርም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የገንዘብ ሥርዓት መቃወስ ለዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ሥርዓት አለመረጋጋት ምክንያት እንዲሆን መፈቀድ የለባቸውም ብለዋል። ይልቅስ የኤኮኖሚ ቀውስ እንዳያጋጥም ፈጣን እርምጃን መውሰድ ይገባል ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን አክለውም ዓለም አቀፍ አካሄዶችን ወደ ንግድ እና ልማት መለወጥ ያስፈልጋል ብለው፣ ከኤኮኖሚ ቀውስ ወጥቶ በዘላቂነት ለማገገም አሮጌውን ዘዴ ከመጠቀም ይልቅ ሙሉ በሙሉ ከመሠረቱ ጀምሮ አንዳንድ ገጽታዎችን እንደገና መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም፣ በባርባዶስ ሊካሄድ የታቀደው ጉባኤ፣ ካለፉት ስህተቶች በመማር፣ ያልተጠቀምናቸውን ዕድሎች ለመጠቀም ፈር ቀዳጅ እና ወደ ቀድሞ የንግድ ሥርዓታችን እንዳንመለስ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ችላ የምንልበት ጊዜ አይደለም

አሁን የምንገኝበት ወቅት መላው ዓለም እየተሰቃየ ያለበት እና አስከፊውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመታገል በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ነው ብለው፣ በዚህ ሂደት መካከል ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እና በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚኖሩት የማኅበረሰብ ክፍሎች ተዘንግተው እንዳይቀሩ በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ኢቫን በመጨረሻም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ኮሚቴ አባላት በሚያዘጋጁት ሰነድ ውስጥ ገንቢ ሃሳቦችን ማበርከት እንዲቻል የቅድስት መንበር ልኡካን በኮሚቴው አባላት ውስጥ ቢካተቱበት በማለት ጥያቄአቸውን አቅርበዋል።                       

14 December 2020, 18:29