ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን፣ 

ካርዲናል ታርክሰን፣ ለድሆች እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የበለጠ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል አሉ።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን፣ የፓሪሱ ስምምነት የተፈረመበት አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በፓሪስ ከተማ ለተሰበሰቡት የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። ካርዲናል ታርክሰን በመልዕክታቸው “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳንደናቀፍ፣ አጋጣሚው ለድሆች እና ለምድራችን ተጨማሪ እንክብካቤን የምናደርግበት መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን “ምኞታችንን በሁሉም ደረጃ ማሳደግ አለብን” በማለት መልዕክት ያስተላለፉለትን የፓሪሱ ስምምነት አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ጉባኤን ያስተባበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሆኑ ታውቋል። ታኅሳስ 3/2013 ዓ. ም. የተካሄደውን የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጉባኤ በጋራ ሆነው ያዘጋጁት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ሲሆኑ ተባባሪ አገሮች ቺሊ እና ጣሊያን መሆናቸው ታውቋል። ካርዲናል ታርክሰን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ “የምድራችን እና የድሆች ጩሄት” የሚለውን ጠቅሰው በላኩት መልዕክታቸው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለድሆች እና ለምድራችን የሚያደርገው ድጋፍ ጠንካራ እና አስቸኳይ መሆን ይገባል ብለዋል። ካርዲናል ታርክሰን አክለውም “ሁሉ አቀፍ ዕድገትን ማምጣት የሚቻለው እና የሰውን ልጅ ከደረሰበት ችግር አውጥቶ ወደ አዲስ ሕይወት ማሸጋገር የሚችለው ባሕልን በማደስ፣ የኤኮኖሚ ሕልሞችን ተግባራዊ በማድረግ፣ አንድነትን በማሳደግ፣ ተፈጥሮን በጋራ በመንከባከብ፣ ማኅበራዊ ተሳትፎን በማሳደግ፣ እኩልነትን እና ፍትህን በማምጣት ነው” ብለዋል።

ተጨባጭ የሆኑ የአጭር ጊዜ ዓላማና ተግባራት ሊኖሩ ይገባል

በ196 አገራት የተፈረመው የፓሪስ ስምምነት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በፖለቲካውም ዘርፍ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲደረግ፣ የልብ መለወጥ እና በምድራችን አብረን የምንኖርበት ምቹ መንገድ ሊኖር ይገባል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በተጨማሪም የአየር መበከልን የሚያስከትል የተቃጠለ አየር ልቀት መቀነስ እንዲቻል ተጨባጭ የሆኑ የአጭር ጊዜ ዓላማ እና ተግባራት እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2030 ዓ. ም. ድረስ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል ብለው፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ምድራችንን ከአየር ብክለት ለመከላከል የሙቀት መጠንን በ1.5 ºC መገደብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አውሮጳም ሃላፊነቷን ተገንዝባ በዓለም አቀፍ ጥረቶች የራሷን ሚና በመጫወት ሳይንሳዊ መፍትሔን እንድታገኝ እና ጉዳቱ የደረሰባቸው ሕዝቦች እና የወጣት ትውልድ አቤቱታን በማድመጥ መልስ እንድትሰጥ አደራ ብለዋል።

ምድርን ከውድመት ለማዳን የአገራት መሪዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን ለፖለቲካ መሪዎች ባስተላለፉት ጥሪ፣ መሪዎቹ እቅዳቸውን እና የተቀበሉትን እውነተኛ ጥሪን በተግባር ለማዋል ምን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠይቀው፣ በምድራችን የሚገኘውን የተፈጥሮ ጸጋ ለጋራ ጥቅም ለማዋል ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው አደራ መኖሩን በማስታወስ፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለግል ጥቅም ለማዋል ከማሰብ ይልቅ ለጋራ እድገት በማዋል በድህነት ሕይወት ለሚሰቃዩት እና ዕርዳታን ለሚሹት የማኅበረሰብ ክፍል ቅድሚያን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።    

በቅሪተ አካል ኃይል መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ይቁም

መንግሥታት መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚወስዱት እርምጃ ወሳኝነት ያለው መሆኑን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በውሳኔአቸው መካከል ድሆችን እና መጭው ትውልድን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው አሳስበዋል። “G20 የሚባሉ ሃብታም አገሮች ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደርጉት ዕርዳታ፣ ታዳሽ ኃይልን ከሚጠቀሙ አገሮች ይልቅ ቅሪተ አካል ኃይልን ለሚጠቀሙት አገሮች 50 ከመቶ ከፍ ማድረጋቸው ለምንድር ነው?” ብለው፣ መንግሥታት በቅሪተ አካል ኃይል ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሌለባቸው አሳስበው፣ በማደግ ላይ ያሉ ድሃ አገሮች አዲስና ዘላቂ የሆነ ታዳሽ ሃይልን መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል። ካርዲናል ታርክሰን በማከልም “በአንድ ስብዕና ላይ ቆመን የጋራ ሕልማችንን በመግለጽ፣ የዚህች ምድር ልጆች እንደመሆናችን፣ በእምነታችን እና በምናሰማው ድምጽ መጠን ‘ሁላችንም ወንድማማቾች ነን’” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት አስታውሰዋል።

ድሆችን መርዳት እና የአካባቢ ጥበቃን ማሳደግ የፖለቲካ ቀዳሚ ርዕስ ይሁኑ

ካርዲናል ታርክሰን፣ ድሃ አገራትን በገንዘብ ለመርዳት የተገባው ቃል በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውሰው፣ በርካታ አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የዕዳ ጫና እጅግ በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ “ያለ ፍትሃዊነት ዘላቂ እድገት አይኖርም” ብለው ድሆች በፖለቲካው እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ዕቅድ ውስጥ ቀዳሚ ሥፍራ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል። የአንድ ቤተሰብ አባል በመሆናችን፣ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ ስንኖር አንዱ ስለ ሌላው ደህንነት በመጨነቅ የእርስ በእርስ መተሳሰብ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።  

14 December 2020, 15:53