ፈልግ

ድሆችን ያናከለ የተቀናጀ ልማት ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል ድሆችን ያናከለ የተቀናጀ ልማት ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል 

ድሆችን በኅብረተሰብ ውስጥ ማሳተፍ

ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን ጩኸታቸውን እንሰማለን

እያንዳንዱ ክርስቲያንና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ለድሆች ነጻነትና ዕድገት እንዲሁም ሙሉ የኅብረተሰብ አካል እንዲሆኑ የእግዚአብሔር መሣሪያ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህም የድሆችን ጩኸት ለመስማትና ለመርዳት ዝግጁና ትጉሃን እንድንሆን ይጠይቃል፡፡ ደጉ አባታችን የድሆችን ጩኸት ለመስማት እንዴት እንደሚፈልግ ለመረዳት ቅዱሳት መጻሕፍትን መመልከቱ ብቻ ይበቃናል፡፡ ‹‹በግብፅ የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ፤ ልታደጋቸውም… ወርጃለሁ፡፡ ስለዚህ፣ እልክሃለሁ….›› (ዘጸ.3፡7-8፣10)፡፡ እንዲሁም ለሚያስፈልጋቸው ነገር ምን ያህል እንደሚጨነቅ እንረዳለን ‹‹እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፣ ነጻ የሚያወጣቸውን አስነሣላቸው›› (መሳ.3፡15)፡፡ እኛ ድሆችን ለመስማት የእግዚአብሔር መሣሪያ የሆንን፣ ለዚህ ጩኸት ጆሮአችንን ብንደፍን፣ የአብን ፈቃድና ሀሳብ እንቃወማለን፤ ያ ድሃ ሰው ‹‹ወደ እግዚአብሔር ጮኾ በደለኛ እንዳንሆን እንጠንቀቅ››(ዘዳ.15፡9)፡፡ ለእርሱ ወይም ለእርስዋ ችግር አለመተባበር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በቀጥታ ይነካል፡- ‹‹በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ጸሎቱን ይሰማዋልና›› (ሲራክ.4፡6)፡፡ ዘወትር የሚመላለስ የቆየ ጥያቄ አለ፣ ‹‹ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል?›› (ዮሐ.3፡17)፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ደግሞ ስለተጨቆኑ ሰዎች ጩኸት እንዴት ፍርጥ አድርጎ እንደሚናገር እናስታውስ፡- ‹‹እርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የአጫጆችም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ይጮኻል፡፡›› (ያዕ.5፡4)፡፡

ይህን ጩኸት መስማት በራሱ በእያንዳንዳችን ውስጥ ካለው ነጻ ከሚያወጣ የጸጋ ሥራ የፈለቀ መሆኑን ቤተክርስቲያን ትገነዘባለች፤ በመሆኑም ይህ ሥራ ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ተልእኮ አይደለም፡፡ ‹‹ቤተክርስቲያን፣ በወንጌል ምሕረትና ለሰው ልጆች ባላት ፍቅር ተመርታ፣ የፍትህ ያለህ የሚለውን ጩኸት ትሰማለች፣ ባላት አቅምም ሁሉ ለጩኸቱ ምላሽ ለመስጠት ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ‹‹የሚበሉትን እናንተው ስጡአቸው›› (ማር.6፡37) የሚለውን ትእዛዝ መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ ማለት የድህነትን መዋቅራዊ ምክንያቶች ለማስወገድ መሥራት፣ የድሆችን ሁለንተናዊ ዕድገት መደገፍ እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ተጨባጭ ችግሮች በመፍታት ረገድ በየቀኑ በትናንሽ ሥራዎች መተባበር ማለት ነው፡፡ ‹‹መተባበር›› የሚለው ቃል ትንሽ አገልግሎቱን የጨረሰና አንዳንዴ ሰዎች እምብዛም የማይረዱት ቃል ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉ አልፎ አልፎ ከሚደረጉ ጥቂት የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከፍ ያለውን ነገር የሚያመለክት ነው፡፡ ከማኅበረሰብ አኳያ የሚያስብና ለሰው ሁሉ ሕይወት ቅድሚያ መስጠት ሀብትን በጥቂት ሰዎች እጅ ከማከማቸት የበለጠ መሆኑን የሚገነዘብ አዲስ አስተሳሰብ እንዲፈጠር የሚጠይቅ ነው፡፡

መተባበር የንብረት ማኅበራዊ ተግባርና የሀብት አጠቃላይ ግብ ከግል ሀብት በፊት የሚመጡ እውነታዎች መሆናቸውን የሚያውቁ ሰዎች የሚሰጡት ግብታዊ ምላሽ ነው፡፡ የግል ሀብት ማፍራት የጋራ ጥቅምን በተሻለ ሁኔታ ያገለግሉ ዘንድ ንብረቶቹን መጠበቅና ማሳደግን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ምክንያት መተባበር ለድሆች የሚገባቸውን መልሶ የመስጠት ውሳኔ ነው፡፡ ይህ የትብብርና የእምነት ልምዶች ተግባራዊ ሲሆኑ ለሌሎች መዋቅራዊ ለውጦች መንገድ ይከፍታሉ፣ ተፈጻሚም እንዲሆኑ ይረዳሉ፡፡ አዳዲስ እምነቶችና አስተያየቶች የሌሉአቸው መዋቅራዊ ለውጦች፣ ፈጠነም ዘገየም፣ የተበላሹ፣ ጨቋኝና ውጤት አልባ ይሆናሉ፡፡

‹‹ሰላም ሰብአዊ መብቶችን በማክበር ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መብቶች መከበርም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ›› አንዳንድ ጊዜ የመላ ሕዝቦች፣ የዓለም የመጨረሻ ድሃ ሕዝቦች ጩኸት የመስማት ጉዳይ ይሆናል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር፣ ሰብአዊ መብቶች ገደብ የለሽ የግል መብቶችን ወይም የሀብታም ሕዝቦችን መብቶች ለመጠበቅ በምክንያትነት መቅረባቸው ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሕዝብ ራስ ገዝነትና ባህል እንደተከበረ ሆኖ፣ ይህች ዓለም የሰው ልጅ በሙሉና ለሰው ልጅ ሁሉ የተፈጠረች መሆኑን ከቶ መዘንጋት የለብንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጥቂት የተፈጥሮ ሀብት ወይም ያነሰ ልማት ባሉባቸው ቦታዎች መወለዳቸው ባነሰ ክብር ይኖራሉ ለማለት አያስችልም፡፡ ይልቁንም ‹‹ይበልጥ የታደሉት ሀብታቸውን ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት በልግስና ለመስጠት አንዳንድ መብቶቻቸውን መተው ይኖርባቸዋል››፡፡ ስለራሳችን መብቶች በሚገባ ለመናገር፣ እይታችንን ማስፋትና ከራሳችን አገር ውጭ የሚኖሩ የሌሎች ሕዝቦችንና አካባቢዎችን ጩኸት መስማት ያስፈልገናል፡፡ ‹‹ሕዝቦች ሁሉ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወሰኑ በሚያስችላቸው››  የትብብር መንፈስ ማደግ አለብን፤ ምክንያቱም ‹‹ማንኛውም ሰው ራሱን ለማብቃት ተጠርቷልና››፡፡

በሁሉም ስፍራዎችና አካባቢዎች የሚገኙ ክርስቲያኖች፣ ከመንፈሳዊ እረኞቻቸው ጋር በመሆን፣ የድሆችን ጩኸት መስማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በብራዚል ጳጳሳት በግልጽ እንዲህ ተነግሯል፡፡ ‹‹የብራዚልን ሕዝብ በተለይም በመንደሮችና በገጠር የሚኖሩ መሬት፣ ቤት፣ ምግብና የጤና እንክብካቤ የሌላቸውንና መብቶቻቸውን ያጡ ወገኖችን ደስታና ተስፋ፣ ችግርና ሃዘን በየቀኑ ለማንሣት እንፈልጋለን፡፡ ድህነታቸውን፣ ጩኸታቸውን ስንሰማና ችግራቸውን ስናውቅ አፍረናል፤ ምክንያቱም ለሁሉም የሚበቃ ምግብ እንዳለና ረሃብ የሀብትና የገቢ ስርጭት አለመስተካከል ውጤት እንደሆነ ስለምናውቅ ነው፡፡ ችግሩ የተባባሰው በአጠቃላይ የብክነት አሠራር በመኖሩ ነው››፡፡

ሆኖም ከዚህ የበለጠ ነገር እንመኛለን፤ ሕልማችን ከፍ ያለ ነው፡፡ የምንናገረው የምግብ ዋስትና ስለማረጋገጥ ወይም ‹‹ለሰዎች ሁሉ ክብር ስለሚመጥን ምግብ›› ብቻ ሳይሆን ‹‹አጠቃላይ ዓለማዊ ደኅንነትና ብልጽግና ስለሚያገኙበት ሁኔታ ነው›› ይህ ማለት፣ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት፣ ከሁሉም በላይ የሥራ ዕድል ማግኘት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጆች  ክብራቸውን የሚገልጹትና የሚያዳብሩት በነጻ፣ የፈጠራ ችሎታ በታከለበት፣ አሳታፊና እርስ በርስ ለመረዳዳት በሚያስችል ሥራ አማካይነት ነውና፡፡ ፍትሃዊ ደመወዝ ለጋራ ጥቅማችን መዋል የሚገባቸውን ሌሎች ሸቀጦች በበቂ መጠን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡

ለወንጌል በመታመን በከንቱ አለመሮጥ

የድሆችን ጩኸት የመስማት ግዴታችንን እውን የምናደርገው ለሌሎች ሥቃይ ጥልቅ ሃዘን ሲሰማን ነው፡፡ እስቲ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ምሕረት የሚያስተምረንን እናዳምጥ፤ ያም ቃል በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንዲያስተጋባ እናድርግ፡፡ ወንጌል እንደሚነግረን ‹‹ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና›› (ማቴ.5፡7)፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም ለሌሎች የምናደርገው ምሕረት በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ነጻ እንደሚያወጣን ያስተምረናል፡- ‹‹ስትናገሩም ሆነ ስታደርጉ ነጻነት በሚሰጠው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ሁኑ፣ ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል›› (ያዕ.2፡12-13)፡፡ እዚህ ላይ ያዕቆብ ለምሕረት ልዩ ዋጋ ስለሚሰጠው ስለ ድህረ ስደት የአይሁድ መንፈሳዊነት ያለውን ጥርት ያለ ትውፊት ያሳያል፡፡ ይህም ትውፊት ‹‹ኃጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል›› (ዳን.4፡27) የሚል ነው፡፡ የጥበብ መጽሐፍም ምጽዋት መስጠት ለተቸገሩት ምሕረትን ማሳየት ተጨባጭ ተግባር እንደሆነ ሲናገር፡- ‹‹ምጽዋት ከሞት ታድናለች፤ ከኃጢአትም ሁሉ ታነጻለችና›› (ጦቢት 12፡9) ይላል፡፡ ሲራክ ይህን ሀሳብ ይበልጥ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡- ‹‹የምትነድ እሳትን ውሃ ያጠፋታል፡፡ ምጽዋትም ኃጢአትን ታስተሰርያለች›› (ሲራክ 3፡28)፡፡ ተመሳሳይ አባባል በአዲስ ኪዳንም ውስጥ ይገኛል፡- ‹‹ከሁሉ አስቀድሞ በፍጹም ልቡናችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ፍቅር ኃጢአትን ሁሉ ይሸፍናልና›› (1ጴጥ.4፡8)፡፡ ይህ እውነት የቤተክርስቲያን አባቶችን አስተሳሰብ በእጅጉ ለውጦታል፣ ራስን ማዕከል ያደረገ የአረማውያን ራስን የማስደሰት ባህል ለመዋጋት የሚያስችል ነቢያዊ የሆነ አዲስ ባህል እንዲፈጠር ረድቷል፡፡ አንድ ምሳሌ ማንሣት እንችላለን፡- ‹‹የእሳት አደጋ ሲያጋጥመን፣ እሳቱን ለማጥፋት ውሃ ወዳለበት መሮጣችን ያለ ነገር ነው፡፡…… እንደዚሁም፣ የኃጢአት ፍንጣሪ ከውስጣችን በድንገት ቦግ ቢል ጭንቀት ይይዘናል፤ የምሕረት ሥራ የመሥራት ዕድል በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ እሳቱን የሚያጠፋ የውሃ ምንጭ እንደተከፈተ ያህል መደሰት ይኖርብናል››፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ግልጽና ቀጥተኛ፣ ቀላልና ልብ የሚነካ በመሆኑ እርሱን ከሌላው ጋር የማነጻጸር መብት ያለው የቤተክርስቲያን ተርጓሚ የለም፡፡ ቤተክርስቲያን ለእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ያላት አስተሳሰብ የቃላቱን ኃይል ሊያደበዝዘው ወይም ሊያዳክመው አይገባም፤ ይልቁንም የቃላቱን ምክሮች በድፍረትና በጋለ ስሜት እንድንቀበል ያበረታታናል፡፡ ቀላል የሆነውን ነገር ማወሳሰብ ለምን አስፈለገ? እነዚህ ቃላት ሊገልጹአቸው የሚፈልጉአቸውን እውነታዎች ከእኛ የሚያርቁ ሳይሆኑ ግንኙነቱን እንዲጨምር የሚያደርጉ ንድፈ ሀሳባዊ መሣሪያዎች አሉ፡፡ ይህም በተለይ ለወንድማማችነት ፍቅር፣ ለትሁትና ለጋስ አገልግሎት፣ ለድሆች ምሕረትና ፍትህ ይሰጥ ዘንድ በብርቱ የሚጠሩንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች ይመለከታል፡፡ ኢየሱስ ሌሎችን መመልከቻ መንገድ በቃሉና በምግባሩ አስተምሮናል፡፡ ይህን ያህል ግልጽ የሆነውን ነገር ለምን እንሸፋፍነዋለን? ወደ ትምህርተ ስሕተት የመግባት ጉዳይ ሊያስጨንቀን አይገባም፤ ይልቁንስ የሚያስጨንቀን ለዚህ በብርሃን ለተሞላ የሕይወትና የጥበብ መንገድ ታማኝ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡›› ያልተቃወሰ እምነት ደጋፊዎች አንዳንዴ የፍርደ ገምድልነትን ሁኔታዎችና እነርሱንም የሚያራዝሙ የፖለቲካ አገዛዞችን በተመለከተ ቸልተኝነት፣ ልልነት ወይም አስወቃሽ ግብረ አበርነት ይታይባቸዋል ተብለው ይከሰሳሉ››፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሮጦ ወይም በከንቱ ሮጦ እንደሆነ›› (ገላ.2፡2) ለማወቅ በኢየሩሳሌም ወዳሉ ሐዋርያት ዘንድ በቀረበ ጊዜ፣ እነርሱ የሰጡት ዋና ማረጋገጫ ለድሆች ማሰቡን እንዳይረሳ ነበር (ንጽ.ገላ.2፡10)፡፡ ጳውሎስ የሚያስተምራቸው ማኅበረሰቦች ራስን ማዕከል ላደረገ የአረማውያን የአኗኗር ሁኔታ እንዳይሸነፉ የሚያሳስበው ይህ ትልቅ መርሆ፣ ራስን ማዕከል ያደረገ አዲስ አረማዊነት እያደገ ለመጣበት ላሁኑ ጊዜም ይሠራል፡፡ ሁል ጊዜ የወንጌልን ውበት በበቂ መጠን ለማንፀባረቅ ባንችልም፣ ማጣት የሌለብን አንድ ምልክት አለ፤ እርሱም ከሁሉ አነስተኛ ለሆኑት፣ ኅብረተሰቡ ላገለላቸው  ሰዎች አማራጭ መሆን ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ የልብና የአእምሮ እልኸኝነት አለብን፤ ነገሮችን እንረሳለን፣ በዘመናዊ ኅብረተሰብ በቀረቡ ገደብ የለሽ የፍጆታ ዕድሎች ሀሳባችን ይዛባል፣ ይነሣሣል፡፡ ይህም በየደረጃው የማግለል ሁኔታን ያስከትላል፤ ምክንያቱም ‹‹አንድ ኅብረተሰብ የሚገለለው ማኅበራዊ አደረጃጀቱ፣ አመራረቱና ፍጆታው ራስን አሳልፎ ለመስጠትና በሰዎች መካከል አንድነትን ለመፍጠር ይበልጥ አዳጋች እንዲሆን ሲያደርገው ነው››፡፡

ምንጭ፡ እ.አ.አ 2013 ዓ.ም የወንጌል ደስታ በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ላይ ከቁጥር 186-196 የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

20 August 2020, 08:30