ፈልግ

ጸሎት በቤተሰብ ሕይወት፤ ጸሎት በቤተሰብ ሕይወት፤ 

ቤተሰብ የሕብረተሰብ ውድ ሃብት መሆኑ ተገለጸ።

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ለኮሎምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ ቤተሰብ የሕብረተሰብ ውድ ሃብት መሆኑን አስታውቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ሁለት ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን መሠረት በማድረግ ለጋብቻ ሕይወት አስፈላጊውን እንክብካቤ መስጠት ያስፈልግል ያሉት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ ከቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች መካከል የመጀመሪያው፣ ባለ ትዳሮች የተክሊል ምስጢር ታላቅነት በጥልቀት እንዲያውቁ፣ በዚህ ቅዱስ ምስጢር አማካይነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታቸው ውስጥ መገኘቱን እንዲገነዘቡ ማገዝ ሲሆን፣ ሁለተኛው የዚህ ቅዱስ ምስጢር ፍሬ የሆኑ ልጆችን መልካም አስተዳደግ ኖሯቸው በትምህርት መኮትኮት መሆኑን አስረድተዋል። በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ መልዕክታቸውን የላኩት ከሰኔ 29 - ሐምሌ 1/2012 ዓ. ም. በኮሎምቢያ ውስጥ 110ኛ ጉባኤያቸውን ላካሄዱት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ ታውቋል።

ቤተሰቦች ብቻቸውን መተው የለባቸውም፤

የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ሰኔ 29/2012 ዓ. ም. የጋብቻ ሕይወታቸን እና የእናትነት ልምዳቸውን መሠረት በማድረግ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው እንደገለጹት፣ በተለይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለቤተሰብ የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ቤተሰብ የማኅበረሰብ ውድ ሃብት መሆኑ በግልጽ የታየበት ወቅት ነው ብለዋል። ቤተሰብ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ባሳየው የችግር መቋቋም ጥረቱ ሃላፊነቱን መወጣት እና እርስ በእርስ መተጋገዝን በተግባር የገለጸ መሆኑን አስረድተዋል። ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በማከልም ቤተሰብ አሁንም ቢሆን ታላቅ የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ትምህርታዊ ዘርፍ አጋዥ ሆኖ ይቀጥላሉ በማለት አስረድተዋል። በመሆኑም ቤተሰቦችን ብቻቸውን መተው የለባቸውም ብለው፣ የምንገኝበት ጊዜ አስቸጋሪ ቢሆንም ለቤተሰብ የሚደረግ ሐዋርያዊ ድጋፍ ሳይጓደል፣ የደስታ ሕይወት እና የመንፈሳዊ አገልግሎት ጥሪ መገኛ ተቋም መሆኑን ለአዲሱ ትውልድ ማስረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የቤተክርስቲያን ሃላፊነት፣

የጋብቻ ሕይወት ከቤተክርስቲያን ምስጢራት አንዱ ነው ያሉት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ በዚህ ምስጢራዊ ጸጋ የተሳሰሩት ባለ ትዳሮች የቤተክርስቲያን ምሳሌ መሆናቸውንም አስረድተው፣ ይህ ማለት ቤተሰቦች በዕለታዊ ሕይወታቸው ለልጆቻቸው እና ለተቀረው ማኅበረሰብ መንፈሳዊ መሪ በመሆን ሃላፊነታቸውን ሊወጡት ይገባል ብለዋል። ቤተሰቦች ይህን ጥሪ እንዲገነዘቡ ሐዋርያዊ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው የገለጹትም ይህን መሆኑን ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እንደገለጹት በዛሬው ዘመን ቤተሰብን ለሚያጋጥሙ ችግሮች መልስ መስጠት የሚቻለው ከባለትዳሮች ጋር በቅርበት በመወያየትና ሐዋርያዊ ድጋፍን በማድረግ እንደሆነ አስረድተው፣ በዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ ቤተሰብን ዋና ተዋናይ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ቤተሰብ ቤተክርስቲያንን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖን የሚያበረክቱ በመሆናቸው ይህን ጥሪ በብቃት ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ ለኮሎምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት አስታውቀዋል። የቤተሰቦች ከፍተኛ ስጋት ትምህርትን ለወጣቶች በአግባቡ አለማዳረስ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ገብርኤላ፣ ዘመናዊ የማኅበራዊ መገናኛዎች ወጣቶችን ከእውነተኛ ሰብዓዊ ግንኙነት እና ባሕላዊ እሴቶች በማራቅ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመሯቸው እንደሚገኝ አስታውሰው፣ ያለንን አቅም በማስተባበር ለቤተሰብ ሕይወት እድገት በርትቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ወጣቶችን ለጋብቻ ማዘጋጀት፣

ወጣቶችን ለጋብቻ ሕይወት የሚያዘጋጁ የትምህርት መስጫ መንገዶን በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ፣ የቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ዓላማ ቤተሰብ ልጆቻቸውን ስለ ጋብቻ ሕይወት ትርጉም እንዲያውቁ፣ የጋብቻን ሕይወት እንዲወዱ ማድረግ፣ በጥምቀት የተቀበሉትን ጸጋ ታላቅነት አውቀው የቅዱስ ወንጌል ታማኝ መስክሮች እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ ጋብቻ ጥሪ ውበት ከሕጻንነታቸው ጀምሮ እንዲያውቁ በማድረግ፣ ለጋብቻ ሕይወት ሲደርሱ ከቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ጋር በማዛመድ እውቀታቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።   

11 July 2020, 17:55