ፈልግ

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ክቡር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፤ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ክቡር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፤ 

ዶ/ር ሩፊኒ፣ “በአፍሪቃ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስወገድ የሚቻለው በውይይት ነው”።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በቫቲካን ሬዲዮ የአፍሪካ ክፍል የእንግዚኛ ቋንቋ አገልግሎት የተጀመረበት 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለአፍሪቃ ካቶሊካዊ የብዙሃን መገናኛ ባለሞያዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአፍሪቃ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማቆም የሚቻለው በውይይት መሆኑን አስታውቀዋል። ባለሞያዎቹ በሚያበረክቱት ማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎት ቅድስት መንገር ከጎናቸው በመቆም ድጋፏን የምትቅጥል መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ከአፍሪቃ አህጉር ሕዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 29/1967 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ወደ አፍሪካ አህጉር ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ለአፍሪካ ቤተክርስቲያን የነበራቸው ምኞት እና ማኅበራዊ ተልዕኮ አገልግሎት ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በቫቲካን ሬዲዮ የአፍሪካ ክፍል የእንግዚኛ ቋንቋ አገልግሎት የተጀመረበትን 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ዓርብ ሐምሌ 10/2012 ዓ. ም. በአፍሪካ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ሚዲያ ተወካዮች ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል መልዕክት መለዋወጣቸው ታውቋል። በቫቲካን ሬዲዮ የአፍሪካ ክፍል የእንግሊዚኛ ቋንቋ አገልግሎት እና ሲግኒስ አፍሪካ የተሰኘ ማኅበራዊ መገኛኛ ተቋም በጋራ ሆነው ያዘጋጁት የቪዲዮ ኮንፌረንስ ዋና ርዕሥ “በአፍሪካ ውስጥ የሚከሰቱ የጎሳ ግጭቶችን እና ሕዝባዊ አለመረጋጋቶችን መቋቋም የሚቻለው በውይይት ነው” የሚል እንደነበር ታውቋል።  ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በውይይታቸው እንዳስገነዘቡት፣ ማኅበራዊ መገናኛዎች ሁለት ጎኖች እንዳሉት ገልጸው አንደኛው ማኅበራዊ ሕይወትን በማሳደግ፣ የተሻለ ዓለምን ለመገንባት እንደሚያግዝ፣ በሁለተኛ ጎኑ አለመግባባትን በመፍጠር ልዩነትን እና ጥላቻን ሊያስከትል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።  

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ጽሕፈት ቤታቸው የቫቲካን ዜና ማዕከልን ለማቋቋም እቅድ መዘርጋቱን ገልጸው በዚህ የዜና ማዕከል የአፍሪካ ካቶሊካዊ ሚዲያ ባለሞያዎች በብርታት እንዲሳተፉ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ዓርብ ሐምሌ 10/2012 ዓ. ም. በተደረገው የቪዲዮ ኮንፌረንስ ላይ ከናይጀሪያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ብጹዕ አቡነ ኤማኑኤል ባዴጆ፣ የቫቲካን ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት እና የኢየሱሳዊያን ማኅበር አባል ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ሲስተር ሜሪ ክሎድ ኦው ከናይጀሪያ፣ ወ/ሮ ሺላ ፒርስ ከደቡብ አፍሪካ እና የወቅቱ የኢግኒስ አፍሪካ ፕሬዚደንት ክቡር አባ ዎልተር ሄጂሪካ መካፈላቸው ታውቋል።      

ክቡር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለአፍሪካ ካቶሊካዊ መገናኛ ባለሞያዎች በላኩት መልዕክታቸው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 23/2019 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የማኅበራዊ መገናኛ ባለሞያዎችን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ “በቤተክርስቲያን የማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎት ራሱን የቻለ ተልዕኮ ነው” ማለታቸውን አስታውሰው፣ መልካም ዜናን ከማብሰር የበለጠ ጥሩ ነገር የለም ማለታቸውን አስታውሰው፣ በመሆኑም “እያንዳንዱ የሚዲያ ባለሞያ ችሎታውን በሚገባ በመጠቀም ፍሬን እንዲያፈራ፣ የሥራችንም እውነተኛነት የሚገለጸው በዚህ መንገድ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።  ክቡር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመልዕክታቸው፥ “በሥራችን ሊያጋጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶች ብዙ ናቸው” ብለው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተናገሩትን በማስታወስ፣ ሁላችንም በአንድ ጀልባ የተሳፈርን በመሆናችን ተስፋን ሳንቆርጥ፣ አንዳችን ለሌላው እንደምናስፈልግ በመረዳት፣ ብቻችን ሳይሆን በጋራ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንችላለን ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ክቡር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፣ በአፍሪካ ካቶሊካዊ መገናኛ ባለሞያዎች መካከል ያለውን ሕብረት በማሳደግ፣ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ አሳስበው፣ ለ70 ዓመታት ያህል ተባበረን በመሥራት ወደዚህ ደረጃ ቢንደርስም የሥራ ብቃታችንን በማሳደግ ለበለጠ ፍሬያማነት በኅብረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። 

18 July 2020, 20:52