ፈልግ

በኢንዶኔዢያ ከሚገኙ የሮሂንጊያ ስደተኞች በከፊል በኢንዶኔዢያ ከሚገኙ የሮሂንጊያ ስደተኞች በከፊል 

ቅድስት መንበር የስደተኞች ደህንነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ አሳሰበች።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣ የስደተኞች መልሶ ማስፈር መርሃ ግብርን በማስመልከት ሰኔ 30/2012 ዓ. ም. በጀኔቭ በተደረገው ስብስባ ላይ መገኘታቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ኢቫን በስብሰባው ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ቅድስት መንበር የስደተኞች ደህንነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲጠበቅ አጥብቃ የምትፈልግ መሆኗን አስታውቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ቅድስት መንበር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የሕዝቦች መሰደድ ለማስቀረት ተጨባች መፍትሄን በማግኘት፣ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና ሁሉ አቀፍ እድገትን ለማምጣት የምትፈልግ መሆኗን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ይህን የገለጹት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ሰኔ 30/2012 ዓ. ም. በጀኔቭ፣ ስዊዘርላንድ ባዘጋጀው የመንግሥታቱ ኅብረት ስብሰባ ላይ መሆኑ ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ “ስደተኞችን መልሶ ለማስፈር ተጓዳኝ መንገዶች መጥቀም” በሚለው የድርጅቱ ሰንድ ላይ መወያየቱ ታውቋል። ተጓዳኝ መንገዶቹ ስደተኞች በደረሱባቸው አገሮች ዓለም አቀፍ የደኅንነት ዋስትና ኖሯቸው፣ ሠርተው ራሳቸውን ማገዝ የሚችሉበት ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝላቸው የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ሰነዱ እንደገለጸው ስደተኞችን በአዲስ መልክ ማዋቀር ወይም ማስፈር ተጓዳኝ የኑሮ መንገዶችን በማግኘት፣ ለችግሮች ፍትሃዊ ምላሽ ለመስጠት እና ሃላፊነትን በመጋራት ለመወጣት ተጨባጭ ዘዴዎችን የሚያመላክት መሆኑ ታውቋል።

የሦስተኛ አገር የመፍትሄ መንገዶች፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የሦስተኛ አገር የመፍትሄ ሃሳብ በሚለው መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተውን እና “ስደተኞችን መልሶ ለማስፈር ተጓዳኝ መንገዶች መጠቀም” የሚለውን የሦስት ዓመት ዕቅድ የሚደግፉት መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ይህንን ዕቅድ ለማሳካት፣ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. የተደረጉትን አውደ ጥናቶችን እና የተደረሱባቸውን ውሳኔዎች በደስታ የሚቀበሉ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መሠረት በርካታ አገሮች እና የግሉ ማኅበረሰብ ስደተኞችን በሚመለከቱ ደንቦች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ ስደተኞችን ተቀብለው ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማድረግ መንገድ እንደሚያመቻቹ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተስፋ ማድረጋቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ገልጸዋል።  

ጥቅምን መጋራት፣

ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱት አገራት የሚያገኙት ጥቅም መኖንሩን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ ስደተኞች በማኅበራዊ እና ሞያዊ ሥራዎች እንዲሳተፉ ማድረግ ለአንድ አገር ትልቅ ጥቅም መሆኑን አስረድተው፣ ስደተኞች ልስሉስቸው ሞያዊ ብቃት ዋጋን በመስጠት የሥራ ዕድልን ማስፋት እና ቋንቋን በመማር ንቁ የዜግነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የድንበር መተላለፊያዎችን ነጻ ማድረግ፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች፣ ስደተኞች ለአደጋ ከሚጋለጡባቸው አገሮች በመውጣት ወደ ሌላ አገር እንዲዛወሩ የሚያደርጉ መተላለፊያ መንገዶች እንዲመቻቹላቸው ጠይቀዋል። በሊቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ሕይወት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ መውደቁን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ በሊቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ወደ አጎራባች አገር ኒጀር ወይም ደግሞ ወደ ሩዋንዳ የሚዛወሩበት መንገድ እንዲመቻች በማለት ጠይቀዋል። ስደተኞች በብዛት የሚገኙባቸው የሰሜን አፍሪቃ አገሮች፣ በተለይም በሊቢያ የሚገኝ የስደተኞች ማጎሪያ ማዕከላት እንዲዘጉ በማድረግ ስደተኞችን ወደ ሌላ አገር ለማዛወር አገራቱ ድንበሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ አጥንተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ፣ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚገኘኙ ሴቶችን፣ ሕጻናትን እና ሕሙማንን ከሞት ማዳን እንደሚያስፈልግ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ጠይቀዋል።

የብዙዎቹ ስደተኞች ዕድል እርግጠኛነት

የወደ ፊት ዕጣ ፈናታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል የማያውቁ ፣ ዛሬም ቢሆን መሠረታዊ የዕለት ምግባቸውን በበቂ ሁኔታ ማግኘት ያልቻሉ በርካታ ስደተኛ ቤተሰቦች መኖራቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኛ ቤተሰቦች በጊዜያዊ እስር ቤት ውስጥ ሆነው የትምህርት ዕድልን፣ የጤና አገልግሎቶችን እና የሥራ ዕድሎችን ተነፍገው የተቀመጡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ስደተኞቹ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል እና ለዘመናዊ ባርነት የሚጋለጡ መሆናቸውን አስረድተው፣ ቅድስት መንበር ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የሕዝቦች መሰደድ ተጨባች መፍትሄዎችን በማግኘት፣ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርስ አደጋን ለመከላከል፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና ሁሉ አቀፍ እድገትን ለማምጣት የምትፈልግ መሆኗን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ዩርኮቪች ገልጸዋል። 

09 July 2020, 17:23