ፈልግ

የፍልስጤም ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ፤ የፍልስጤም ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ፤  

የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሰላም ጥረት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ተባለ።

ከሰሜን አሜሪካ እና ከእስራኤል አምባሳደሮች ጋር ተገናኝተው የተወያዩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሆኑት እስራኤል እና ፍልስጤም አንዱ ከሌላው ጋር  ሳይወያይ በተናጠል የሚወሰደው ውሳኔ እና እርምጃ የመካከለኛውን ምስራቅ አገሮች ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አክለውም “ሁለቱም አገሮች ዓለም አቀፍ እውቅና በተሰጣቸው ድንበሮቻቸው ተከልለው በሰላም የመኖር መብታቸው የተጠብቀ ነው” በማለት ገልጸዋል። ከሁለቱ አገሮች መካከል አንዱ ከሌላው ጋር የጋራ ውይይት ሳያደርግ በተናጠል የሚወስደው እርምጃ የመካከለኛውን ምስራቅ አገሮች ሰላም አደጋ ላይ መጣሉ ቅድስት መንበርን ያሳሰባት መሆኑን ረብዕ ሰኔ 24/2012 ዓ. ም. ወደ ማምሻው አካባቢ ይፋ የሆነው የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ዋና ጸሐፊው ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ማክሰኞ ሰኔ 23/2012 ዓ. ም. ከሰሜን አሜሪካ እና ከእስራኤል መንግሥታት አምባሳደሮች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ጋዜጣዊ መግለጫው አክሎ አስታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከሁለቱ አገሮች አምባሳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የጋራ ውይይት ሳይደረግ በተናጠል የሚወሰድ እርምጃ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ስጋት ላይ መጣሉ ቅድስት መንበርን ያሳሰባት መሆኑን አስታውቀዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫው በመቀጠልም ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ኅዳር 20/2019 እና ግንቦት 20/2020 ዓ. ም. የተደነገገውን እና ሁለቱ አገሮች፣ እስራኤል እና ፍልስጤም እንደ ሁለት መንግሥታት፣ እያንዳንዳቸው ዓለም አቀፍ እውቅና በተሰጣቸው ድንበሮቻቸው ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው በሰላም የመኖር መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆነ ቅድስት መንበር በድጋሚ የምታረጋግጥ መሆኗን አስታውቋል። በመሆኑንም ቅድስት መንበር እነዚህ ሁለቱ አገሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ፣ በመካከላቸው የእርስ በእርስ መተማመንን በማሳደግ ድፍረትን አገኝተው፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 8/2014 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የአትክልት ሥፍራ፣ በቅድስት አገር ሰላም እንዲወርድ በማለት ባደረጉት ንግግር መሠረት፣ ሁለቱ አገሮች ለአመጽ ሳይሆን ለመልካም የጋራ ውይይት ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ፣ ለግጭት ሳይሆን ለሰላማዊ ድርድር ፣ የሚያስቆጣ ድርጊት ከመፈጸም ይልቅ ለስምምነት፣ ከግትርነት ይልቅ በቅንነት ውይይታቸውን እንደገና ለመጀመር የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ቅድስት መንበር የምትፈልግ መሆኗን ጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል።        

03 July 2020, 08:18