ፈልግ

ወላጆች የልጆቻቸውን ደህንነት በመጠበቅ ተግባር፤ ወላጆች የልጆቻቸውን ደህንነት በመጠበቅ ተግባር፤ 

ቤተክርስቲያን ስለ ሕጻናት ደህንነት የምትጨነቅ መሆኗ ተገለጸ።

በጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የሕጻናት ጉዳይ መምሪያ ሰኔ 1/2012 ዓ. ም. በድረ ገጽ ላይ ቪዲዮ መገናኛ በኩል የመጀመሪያ ዙር ሴሚናር ማካሄዱ ታውቋል። በሴሚናሩ ላይ ቤተክርስቲያን ስለ ሕጻናት ደህንነት ዘወትር የምታስብ እና የምትጨነቅ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት ለመከላከል የበኩሏን ጥረት የምታደርግ መሆኑ ተገልጿል።

የቫቲካን ዜና፤

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሕጻናት ጉዳይ መምሪያ፣ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያን የበላይ አለቆች ሕብረት፣ በሮም የግረጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሕጻናት ጥበቃ እና እንክብካቤ ማዕከል እና "ቴሌፎኖ አዙሮ" የተባለ ማዕከል በጋራ ሆነው ባስተባበሩት የድረ ገጽ ቪዲዮ ሴሚናር ላይ የተካፈሉት፣ የፍቅር ሥራ ደናግል ማህበር አባል፣ ሲስተር ኗላ ኬኒ በሴሚናሩ ማጠቃለያ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕጻናት ያደለውን ጸጋ ማድረስ ይኖርብናል ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው እንቅፋት ምክንያት በድረ ገጽ ቪዲዮ መገናኛ በኩል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ሴሚናር፣ ከሁሉም የዓለማችን ክፍሎች የተወጣጡ በቁጥር ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች መካፈላቸው ታውቋል።

ሕጻናትን የማይታደግ ባሕልን መቃወም ያስፈልጋል፣

በሴሚናሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ሲስተር ኗላ ኬኒ፣ ሕጻናት ላይ በየጊዜው ጥቃት የሚደርስባቸው በቂ ጥበቃን እና እንክብካቤን የማያደርግ፣ ለጥቃት አሳልፎ የሚሰጥ ባሕል በመፈጠሩ ነው በማለት አስረድተዋ። በመሆኑም በቤተሰብ እና በቤተክርስቲያን ለውጥ ማድረግ መጀመር ያስፈልጋል በማለት ሲስተር ኗላ ኬኒ አስረድተዋል። ኢፍትሃዊነትን ለመቃወም በተለይም ጥቃቱ በአቅመ ደካሞች ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ሲገኝ ለማጋለጥ ተጠርተናል ያሉት ሲስተር ኗላ ኬኒ፣ በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም ብለው፣ ብቸኛው መከላከያ መንገድም በኢየሱስ መመሥረት፣ አስተምህሮቹን መከተል እና ፍቅራዊ እንክብካቤውን ተግባራዊ ማድረግ ነው በማለት አስረድተዋል።

ለሕጻናት ተስፋ ለመሆን የቤተሰባዊነት ስሜት ሊኖር ይገባል፣

በድረ ገጽ ቪዲዮ መገናኛ በኩል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ሴሚናር የተካፈሉት ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሕጻናት ጉዳይ መምሪያ አባል የሆኑት ክቡር አቶ ኤርኔስቶ ካፎ፣ ሴሚናሩ በመልካም ሁኔታ መካሄዱን ገልጸው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት፣ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በሕጻናት ደህንነት ላይ የተከሰቱ ለውጦች መኖራቸውን አስታውሰው፣ በሴሚናሩ ወቅት በሕጻናት ደህንነት ላይ ስለተከሰቱ ለውጦች ግንዛቤን ማስጨበጥ የተቻለበት ጠንካራ ፍላጎት የታየበት ነው ብለዋል። ሴሚናሩ በአራት ቋንቋዎች መካሄዱን የገለጹት አቶ ኤርኔስቶ ካፎ፣ በድረ ገጽ ቪዲዮ መገናኛ አማካይነት ከላቲን አሜሪካ፣ ከአፍሪካ፣ ከሩቅ የእስያ አገሮች እና ሌሎች አካባቢዎችም መካፈል የቻሉ መሆኑን ገልጸዋል። ሕጻናትን በማስቀደም፣ እነርሱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት ውይይት በማድረግ ወደ ጋራ አቋም ላይ መድረስ እንደተቻለ ገልጸው፣ በቅዱስ ወንጌል እና በቤተክርስቲያን ሕይወት በመመራት፣ ሕጻናት በትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በቤተስብ ውስጥም መልካም እሴቶችን መቅሰም የሚችሉ ማዕከላዊ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደርገው ይቆጠራሉ ብለዋል። በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ አንድ ሕጻን ከፍተኛ ሚናን እንዲቻወት ማድረግ መብቱን እንዲያስከብር እና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑት በሙሉ ጥበቃን እና እንክብካቤን ለማድረግ ያስችላል ያሉት ክቡር አቶ ኤርኔስቶ ካፎ፣ ሕጻንን ማድመጥ፣ ፍላጎቱን ለይቶ ማወቅ፣ ለድህንነቱ ጥበቃን ማድረግ፣ ከማንኛውም ዓይነት ብዝበዛ መከላከል   ማለት በቀዳሚነት ሰብዓዊ መብቱን ማስጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል። ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የሕጻናት መብት ለማስከበር፣ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ክቡር አቶ ኤርኔስቶ ካፎ አስታውሰዋል።

የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሕጻናት ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጡት ሁሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ አንድ ሕጻን የራሱ ሕይወት እና በማኅበረሰብ መካከል የሚጫወተው ሚና ያለው በመሆኑ በቤተሰቡ እና በማኅበረሰቡ ተደማጭነት ሊኖረው ይገባል ማለታቸውን አስታውሰው፣ ሕጻን በማኛውም መንገድ ለጥቃት እና ለአመጽ መዳረግ የለበትም ብለው ይህም ለሕጻናት በሚሰጥ የትምህርት ይዘት እና አስተዳደግ ላይ ትኩረት እንዲሰጥበት ያስገነዝበናል በማለት ክቡር አቶ ኤርኔስቶ አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜን ያስታወሱት አቶ ኤርኔስቶ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ከተወሰዱት የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሆነው ማኅበራዊ ርቀት ውጤታማ ጎን ቢኖረውም በሕጻናት ላይ ያስከተለው የብቸኝነት፣ የፍራቻ እና ለአደጋ ተጋላጭ የመሆን ዕድል መፍጠሩን አስታውሰዋል። የህን የብቸኝነት እና የፍራቻ ሕይወት በርካታ ሕጻናትን በቤተሰባቸው መካከል ያጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም ከሕጻናት እና ከቤተሰብ ጋር ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ያጋጠማቸውን ልምድ በመነጋገር ትክክለኛውን መልስ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ኤርኔስቶ ካፎ አስታውቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ሲያበቃ አዲስ የማኅበራዊ ሕይወት መንገድ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳጳሳዊ ምክር ቤት ለሕጻናት ጉዳይ መምሪያ ያረጋገጡ መሆኑን አቶ ኤርኔስቶ ካፎ ገልጸው፣ ሌሎች ቀጣይ ሴሚናሮችን በድረ ገጽ ቪዲዮ መገናኛ አማካይነት ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የአቅማችንን ውስንነት በመገንዘብ ሕብረትን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለው፣ በሕብረት የምንጓዝ ከሆነ በመካከላችን ቤተሰባዊ መንፈስን ማሳደግ፣ ለወደፊት መልካም ተስፋን በመሰነቅ፣ ለመጭው ትውልድ እምነትን፣ ለሕጻናት ተስፋን መስጠት የሚቻል መሆነኑን፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሕጻናት ጉዳይ መምሪያ ክፍል አባል የሆኑት ክቡር አቶ ኤርኔስቶ ካፎ አስታውቀዋል።       

11 June 2020, 12:46