ፈልግ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አዲስ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መመሪያ ይፋ መሆኑ ተገለጸ!

ስብከተ ወንጌልን በአዲስ መልክ ለማስፋፋት የሚሰራው ጳጳሳዊ ምክር ቤት አዲስ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አገልግሎት መስጫ መመሪያ ያፋ መዳረጉ የተገለጸ ሲሆን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቅዱስ ወንጌልን በትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እና በስብከተ ወንጌል አማካይነት እንዴት ማከናውን እንደ ሚገባ የሚገልጽ አዲስ መመሪያ እንደ ሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ ትላንት ሰኔ 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን ይፋ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህ መመሪያ የተዘጋጀው እና የተረቀቀው ስብከተ ወንጌልን በአዲስ መልክ ለማስፋፋት የሚሰራው ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኩል እንደ ነበረም ተገልጿል። ለስብከተ ወንጌል እና ለትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራ የነበረው በ16ኛ ክፍለ ዘመን የኖረው የእስፔናዊው የቅዱስ ቱሪቢየስ መታሰቢያ ቀን እ.አ.አ መጋቢት 23/2020 ዓ.ም በተከበረበት ወቅት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፀድቆ ይፋ የሆነ መመሪያ እንደ ሆነ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። ይህ የመጨረሻው እትም ይፋ የሆነው እ.ኤ.አ. በ1971 ዓ.ም ላይ ይፋ ከሆነው “አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ መመሪያ” እና ከዚያም በመቀጠል እ.አ.አ በ1997 ዓ.ም ከወጣው “አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ መመሪያ” በመቀጠል ይፋ የሆነ መመርያ ሲሆን እነዚህ ሁለቱ ቀደም ሲል የነበሩ መመርያዎች ይፋ የሆኑት በጳጳሳዊው የቄሳውስት ማሕበር በኩል እንደ ነበረ ይታወሳል።

ምስክርነት ፣ ምህረት እና ውይይት

አዲሱ መመርያ በስብከተ ወንጌል እና በትምህርተ ክርስቶስ መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ለማጉላት ይፈልጋል። እያንዳንዱ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበለ ሰው እምነቱን በጽናት እና በኃላፊነት  ለማስተላለፍ የሚያስችሉትን አዳዲስ መንገዶችን በመጠቀም ሚሲዮናዊ ተግባሩን እንዲወጣ የሚያመላክቱ መመርያዎች በስፋት ይገኙበታል። በዚህ ረገድ አዲሱ መመርያ ሦስት ዋና ዋና የድርጊት መርሃግብሮችን ወይም መርሆዎችን ያቀርባል፣ እነዚህም ምስክርነት ፣ ምህረት እና ውይይት የተሰኙ መርሆች ናቸው። ከ300 በላይ ገጾችን የያዘው አዲሱ መመርያ በሦስት ክፍሎች የተከፋፈለ 12 ምዕራፎችን አካቶ ይዟል።

የካቴኪስቶች ህነጻ

የመጀመርው ክፍል “የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በቤተክርስቲያን ወንጌላዊ ተልዕኮ ውስጥ” የሚል ዐብይ አርእስት የተሰጠው ሲሆን ለካታኪስቶች መሰጠት ስለሚገባው የሕነጻ ትምህርት የሚገልጹ ንዑስ አርእስቶች በውስጥ አቅፎ ይዟል።  

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መመርያ በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ የተካተተው ካታኪስቶች እምነት የሚጣልባቸው ታማኝ ምስክሮች ለመሆን “ካቴኪስት ከመሆናቸው በፊት ጥሩ ካታኪስት እንዲሆኑ መታነጽ ይኖርባቸዋል” የሚለው መመርያ በስፊው ይንጸባረቅበታል።  “በሐዋርያዊ ተግባራት ውስጥ ድክመት እንዲከሰት እና መካን ሐዋርያዊ ተግባር መካን እንዲሆን የሚያደርጉትን” ተግባራት ማከም የሚችል እና ይህን ተግዳሮት እንዲሸነፍ ማድረግ የሚቻለው በሚስዮናዊ መንፈሳዊነት መሠረት በበቂ ሁኔታ ፣ በቅንነት እና በታማኝነት መስራትን እንደ ሚያካትት በስፈው ይተነትናል።

ካቴኪስት የተባሉት ሰዎች ደግሞ ልዩ ተግባራቸውን በማከናወን ረገድ ጠንቃቃ እንዲሆኑ ጥሪ የሚያደርጉ አንቀጾች የተካተቱበት ሲሆን “ለሁሉም ሰው በተለይም ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊ ወጣቶችን እና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ፍጹም ዋስትና ሊሰጡ ይገባል” የሚሉ አንቀጾች ተካተውበታል።

የትምህርተ ክርስቶስ አሰጣጥ ሂደት

አዲዱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ “የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ ሂደት” የሚል አርዕስት የተሰጠው ሲሆን  “ጥልቅ እና ውጤታማ የግንኙነት መስመር” መመሥረት አስፈላጊነትን ያጎላል። ከእግዚአብሄር ጋር ለመገናኘት እና ውበቱን ለማሰላሰል የሚረዱንን የኪነ- ጥበብ መንገዶችን በብልሃት በመጠቀም እና  ለእግዚአብሔር ያለንን ፍላጎት በልባችን ውስጥ ሊያነሳሱ የሚችሉ ቅዱሳን የሆኑ መዝሙሮችን የመጠቀም አስፈላጊነትን የሚያትቱ አንቀጾች በብዛት ተካተውበታል።

አዲዱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ ካካተታቸው ሐሳቦች መካከል የቤተሰብ ሚና በግንባር ቀደምትነት የገለጻል። በነዚህ አንቀጾች ውስጥ ስብከተ ወንጌል የተሰበከላቸው ሰዎች እመነታቸውን ቀላል እና ቀጣይነት ባለው መልኩ መኖር የሚችሉበትን ሁኔታዎች በስፋት የተነትናል። እንዲሁም ቤተሰብ ሰዎች የክርስትናን ትምህርት በትህትና እና በርህራሄ ሊቀበሉ የሚችሉበት ቦታ ነው በማለት የሚገልጹ ማብራሪያዎች ይገኙበታል።

በዘመናዊው ማህበረሰብ ውስጥ አዳዲስ የቤተሰብ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ​​ክርስቲያኖች ሌሎችን በተስፋ እና በመተማመን ወደ ቀድሞው ሁኔታቸው ለመመለስ እንዲችሉ ሌሎችን ለመቅርብ ፣ ለማዳመጥ እና ለመረዳት እንደ ተጠሩ ሊገነዘቡ ይገባቸዋል የሚሉ አንቀጾች ተካተውበታል።

አካታች የሆነ ባሕል

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተንህሮ አሰጣት መመርያ በተጨማሪም የተለየ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች  “መቀበል እና እውቅና” መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያጎላል። የተለየ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች  ለሰው ልጆች ህይወት አስፈላጊ ለሆኑት እውነቶች ምስክሮች በመሆናቸው የተነሳ እንደ ታላቅ ስጦታ በመቁጠር እነርሱን መቀበል እንደ ሚኖርብን አጥብቆ ያሳስባል። ቤተሰቦቻቸውም “አክብሮት እና አድናቆት” ሊቸራቸው እንደ ሚገባ ይገልጻል።

በተመሳሳይ መልኩም የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከትውልድ አገራቸው በመራቃቸው የተነሳ የመንፈስ ቀውስ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ስደተኞችን በመቀበል ፣ በመተማመን እና በመተባበር ላይ ማተኮር እንደ ሚገባ አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተንህሮ አሰጣጥ መመርያ ያሳስባል። በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ጭፍን ጥላቻ ለማስወገድ እና በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ እንዳይወድቁ እና በዚህ ረገድ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉትን አደገኛ ሁኔታዎች ለመዋጋት ድጋፍ መስጠት እንደ ሚገባ የሚያትቱ አንቀጾች የሚገኙበት ክፍል ነው።

ለድሆች እና በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ሰዎች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ “የተልዕኮ ትክክለኛ የሆነ ለም መሬት” በማለት በቀዳሚነት ላስቀመጠው ማረሚያ ቤቶች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባል። ለሕግ ታራሚዎች የሚሰጠው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክርስቶስ አዳኝ መሆኑን ማወጅ፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን እናት መሆኗን የሚያሳየውን ፊቷን ቁልጭ አድርጎ በማሳየት የሕግ ታራሚዎችን ማዳመጥ እና ትኩረት መስጠት እንደ ሚገባ የሚገልጹ አንቀጾች ተካተውበታል።

ድሆችን በተመለከተ ደግሞ የሚሰጡ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ሰዎች ስለ ወንጌላዊ ድህነት ማስተማር ማካተት እንደ ሚገባው የገልጻል። እንዲሁም የድሃው የማሕበረሰብ ክፍል ላይ የሚደርሱ ስቃዮች እና የፍትህ መጓደል በመዋጋት የወንድማማችነት ባሕል በማዳበር እና የቁጣ ባሕል በመቀነስ ድሆች የተሻለ ሕይወት ይኖራቸው ዘንደ ተስፋቸው እንዲለመልም የሚያደርጉ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎችን መስጠት እንደ ሚገባ ያትታል።

ቁምስናዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የቤተክርስቲያን ማህበራት

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ  በሦስተኛው ክፍል ውስጥ “በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚሰጥ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ” የሚል አርዕስት የሰጠው ሲሆን  በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስናዎች ውስጥ፣ በተለያዩ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች እና በሌሎች የአምነት ተቋማት ማኅበራት ውስጥ ስለሚሰጠው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በሰፊው የሚተነትኑ መመርያዎችን አቅፎ ይዟል።

ቁምስናዎች “የሐዋርያት ሕበረት ምሳሌዎች” ተደርገው እንደ ሚቆጠሩ በዚሁ በሦስተኛው ክፍል ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሕዝቡ የኑሮ ደረጃ እና ልምድ ጋር በሚዛመድ እና በሚጣጣም መልኩ በፈጠራ ችሎታ የታገዘ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማደረግ እንደ ሚገባ የሚገልጽ መመርያ የሚገኝበት ክፍል ነው። ሌሎች የቤተክርስቲያን ማህበራት ራሳቸው “የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ብልጽግና” እንዲጨምር “ታላቅ ወንጌላዊ አቅም” እንዲኖራት የሚረዷት ማሕበራት መሆናቸውን መመርያው ይገልጻል።

የካቶሊክ ትምህርት ቤቶችን በሚመለከት አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ   ሲገልጽ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደሩ የትምህርት መስጫ ተቋማት “የእውቀት ተቋማት” ከመሆን ወደ “እውቀት ያለው ማሕበረሰብ” ማፍለቂያነት በመሻገር በወንጌል እሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ እምነትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት መርሃግብር መቀረጽ እንደ ሚገባ የሚተነትኑ መመርያዎች ተካተውበታል።  በተጨማሪም ስለሐይማኖት ትምህርት መስጠት እና የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማደረግ ተጉዳኛ የሆኑ ነገሮች መሆናቸውን በስፋት ያትታል።

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ “የሃይማኖት ጉዳይ ጎልቶ ሊወጣ የሚገባው ጉዳይ” እንደ ሆነ የሚዘረዝረው መመርያው የሐይማኖት ጉዳይ መዘንጋት የሌለበት፣ የሃይማኖት ትምህርትን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተቀናጀ የሕንጸት ትምህርቶችን መስጠት እና መቀበል የወላጆች እና የተማሪዎች መብት መሆኑን የሚገልጹ አንቀጾች ይገኙበታል።

ባሕል እና የሐይማኖት ብዝሃነት

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ እንደሚጠቁመው ከአይሁድ እና ከእስልምና የእምነት ተቋማት ጋር ሐይማኖትን በተመለከተ ስለሚደረገው ውይይት በተመለከተ ለየት ያለ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መመርያ ይፋ አድርጓል። የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እውነተኛ የቅዱስ ወንጌል መሳሪያ እንዲሆን “የአንድነትን ፍላጎት ማበረታታት” አለበት በማለት ይገልጻል።

ጸረ-ሴማዊነትን የሚዋጋ እና ሰላምን እና ፍትህን በአይሁዳዊያን ዘንድ ለማስፈን የሚረዳ ውይይቶችን ማደረግ አስፈላጊ መሆኑን መመርያው ይገልጻል። በተመሳሳይ መልኩም ከእስልምና የእመነት ተቋም ጋር የሚድረገው ውይይት ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲቀጥል ለማገዝ እና ለማስቻል ምዕመናን ጥልቅት ከሌለው ጠቅላላ ፍረጃ መራቅ እንደ ሚገባቸው መመርያው ያሳስባል።

አሁን ባለው የሃይማኖት በብዙነት አኳያ አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መመሪያ  “የአማኞችን ማንነት በጥልቀት ማጎልበት እና ማጠንከር” በሚችል መልኩ በተልእኮ መመስከር እንደ ሚገባ፣ እንዲሁም “ወዳጃዊ እና ልባዊ” ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚረዱ ውይይቶች እንዲካሄዱ ማድረግ እንደ ሚገባ ያሳስባል።

ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ዓለም

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጆች አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ በመስጠት በተጨማሪም የሰው ልጅ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አብክረው እንዲሰሩ ይጠይቃል።

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመሪያ ጥሩ እና መጥፎ ይዘት ያላቸውን የዲጂታል ተክኖሎጂዎችን ለይቶ ለማወቅ እና በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሰዎችን ለማስተማር አቅጣጫ መጥቆም እንዳለበት ሃሳብ ያቀርባል። አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መመሪያ እንዲሁ “ቅጽበታዊ በሆነ ባሕል” ውስጥ ወጣቶች እንዳይገቡ እውነትን እና ጥራትን ለይተው እንዲያውቁ በመርዳት ላይ ያተኮረ አስተምህሮ ማደረግ እንደ ሚገባ ይገልጻል።

አዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሰጣጥ መመርያ ጎልተው ከሚታዩት ሌሎች ገጽታዎች ውስጥ “ሥነ-ምህዳራን በተመለከተ ጥልቅ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ” የሚጠይቅ ጥሪ ተካቶበታል። የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ለተፍጥሮ ሐብት ጥበቃ ይደረግ ዘንድ እና ከመጠን ያለፈ ፍጆታን በተመለከተ አስተምህሮ መስጠት እንደ ሚገባ በመግለጽ በዚህ ረገድ አስፈላጊው ለውጥ እንዲመጣ ማደረግ እንደ ሚቻል ያትታል።

እንዲሁም አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን መብቶች ለማስከበር ልዩ ትኩረት በመስጠት የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ላይ መሠረት በማድረግ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የሰራተኞችን መንፈስ ማነቃቃት እንደ ሚኖርበት ይገልጻል። በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶስ እና የጳጳሳት ጉባሄዎችን ጨምሮ በትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አገልግሎት ውስጥ በአካባቢያዊ ደረጃ የሚረቀቁ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎችን እድገት ያበረታታል።

26 June 2020, 18:12