ፈልግ

የስደተኞችን ሕይወት ያገናዘቡ ሐዋርያዊ አስተምህሮችን የያዘ መጽሐፍ መታተሙ ተገለጸ።

ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እስከ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ድረስ ያሉትን ሐዋርያዊ አስተምህሮች መሠረት በማድረግ ስለ ስደተኞች ጉዳይ የሚናገር አዲስ መጽሐፍ በቫቲካን ማተሚያ ቤት መታተሙ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ስደትን አስመልክተው ያወጡትን ሐዋርያዊ ደንቦችን እና አስተምህሮችን መሠረት በማድረግ በመጽሐፉ ውስጥ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያበረከቱት፣ ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ እና ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ መሆናቸው ታውቋል። መጽሐፉ ታትሞ ለንባብ የበቃውም ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በተከበረበት ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ዓ. ም. መሆኑን የቫቲካን ኒውስ አስታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ስደትን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ይደርስባቸው ከነበረው ስቃይ እና መከራ ለማምለጥ ወደ ግብጽ የተሰደደው የናዝሬቱ ቅድስት ቤተሰብ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ በዘመችንም ከአገራቸው ወጥተው ለሚሰደዱት፣ ለነጋዲያን እና መፈናቀል ለሚደርስባቸው በሙሉ ጥሩ ምሳሌ ናቸው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

አውሮፓ ከጦርነቱ በኋላ፣

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1952 ዓ. ም. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ማኅበራዊ ቀውሶች ለመቋቋም የአውሮፓ አገሮች ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት እና በጦርነት ምክንያት ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያቸው በመፈናቀል ለስደት የተዳረጉበት መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንን ይመሩ የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የሕዝቦችን ስቃይ እና ስደት በመመልከት፣ ቤተክርስቲያን ለስደተኞች ያላትን እናታዊ ርህራሄን የገለጸችበት፣ “ስደተኛ ቤተሰብ” የሚል ሐዋርያዊ ደንብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በሐዋርያዊ ደንባቸ በኩል፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ሕይወት፣ የናዝሬቱን ቅዱሳ ቤተሰብ፣ ሕጻኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሴፍ ከኖሩት የስደት ሕይወት ጋር አገናዝቦ እንዲመለከት የተጠራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

በቀላሉ የሚገኝ ጽሑፍ አልነበረም፣

በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው “ስደተኛ ቤተሰብ” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ሰነድ ብዙ ያልተነበበ እና በቀላሉ የማይገኝ በመሆኑ ለዘመናችን አንባቢያን እንዲደርስ ለማድረግ በቫቲካን ማተሚያ ቤት እንዲታተም መደረጉ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ሰነድ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተጓዘችባቸው ዘመናት ሁሉ ለስደተኞች እና ለተፈናቃዮች ስታደርግ የቆየችውን ድጋፍ እና እንክብካቤን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል።

“በግዞት የሚገኙ ቤተሰቦች” በሚል ርዕሥ የታተመው አዲሱ መጽሐፍ 152 ገጾች ያሉት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ እና የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሥራች እና የታሪክ ተመራማሪ ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ ሰፋ ያለ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን በማበርከት የተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል። በመጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ሃሳቦች፣ የሁለቱ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ሰነድ እና የዘመናችንን የስደተኞች እና የተፈናቃዮች ጉዳይ በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ሐዋርያዊ አስተምህሮ ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲን ሲቀበሏቸው፤
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲን ሲቀበሏቸው፤

ሪካርዲ፥ ቤተክርስቲያን የስደተኞች እናት ናት፣

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሥራች እና የታሪክ ተመራማሪ ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ እንደገለጹት፣ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለሕዝቦች ሐዋርያዊ አባት በመሆን እንደገለጹት ሁሉ፣ እናት ቅድስት ቤተክርስቲያን በታሪኳ እንደ ስደተኛ የምትቆጠር መሆኗን አስረድተው፣ በዚህም አካባቢያቸውን ለቀው ለሚሰደዱት በሙሉ በእናታዊ የርህራሄ ዓይን የምትመለከታቸው መሆኑን ገልጸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ሰነድም ይህን የሚያስገነዝብ መሆኑን አስረድተዋል።

ምድር የተፈጠረችው ለጋራ ጥቅም ነው፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ “ስደተኛ ቤተሰብ” በሚለው ሐዋርያዊ ሰነዳቸው፣ ምድር የተፈጠረችው ለጋራ ጥቅም መሆኑን ገልጸው፣ ሰነዱን ይፋ ያደረጉበት ዘመንም የቅኝ ግዛት ሥርዓት የገነነበት፣ አገሮች ድንበራቸውን በመዝጋት ሰዎች ከቦታ ቦታ የመጓዝ መብታቸውን የተነፈጉበት በመሆኑ ሕዝቦች ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ በማለት ያሳሰቡበት ሰነድ መሆኑ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በሐዋርያዊ ሰነዳቸው፣ ለጋራ ጥቅም በተፈጠረች ምድራችን ሕዝቦች ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በመካከላቸው ወዳጅነትን እና አብሮ የመኖር ባሕልን ማሳደግ እንዲቻሉ፣ መንግሥታትም ለዚህ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያሳስብ፣ ለስደት የተዳረጉ ቤተሰቦች ከስቃይ የሚያመልጡበትን መንገድ የከፈተ መሆኑን አስታውሰዋል።

 

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አቋም፣

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ ተፈናቃዮችን እና በምድራችን ችግሮች ሰለባ የሆኑትን በማስመልከት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ መልዕክቶች እና አስተምህሮችን አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ወደ ሚገኙባቸው ሥፍራዎች፣ በጣሊያን ወደ ላምፔዱሳ፣ በግሪክ ወደ ሌስቦ እና በሞሮኮ ወደ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስታውሰዋል።

የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮች፣

“በግዞት የሚገኙ ቤተሰቦች” በሚለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም ክርስቲያን ማኅበረሰብ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ የዕርዳት እጅ በመፈለግ ድምጻቸውን ለሚያሰሙ ስደተኞች መልካም አቀባበል፣ መስተንግዶ፣ የሕይወት ከለላ እና ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ሕይወታቸውን መምራት እንዲችችሉ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ማሳሰባቸውን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስታውሰው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክቶቻቸው ሁሉ የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮችን፣ “ስደተኛ ቤተሰብ” የተሰኘን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ደንብ መጥቀሳቸውን ገልጸዋል። “በግዞት የሚገኙ ቤተሰቦች” በሚል አርዕስት የታተመው አዲሱ መጽሐፍ፣ እናት ቅድስት ቤተክርስቲያን በችግር ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ለሚሰደዱት በሙሉ በእናታዊ የርህራሄ ዓይን የምትመለከታቸው መሆኑን የሚያስገነዝብ፣ ከዚህ በፊት ለንባብ ያልበቁ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። 

22 June 2020, 13:33