ፈልግ

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ የቀረበ የመቁጠሪያ ጸሎት የብዙዎችን ልብ መቀየሩ ተገለጸ።

በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ረዳት ጳጳሳ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ኮማስትሪ፣ በግንቦት ወር በቫቲካን ከሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበው እና በቴሌቪዥን በቀጥታ የተላለፈው የመቁጠሪያ ጸሎት የብዙዎችን ልብ የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በግንቦት ወር ውስጥ በቫቲካን ከሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት በቀጥታ የተከታተሉት፣ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ከግማሽ የሚሆኑ ምዕመናን የምስጋና መልዕክታቸውን በመላክ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በባዚሊካው ውስጥ የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ኮማስትሪ እንደተናገሩት የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ እጅግ አስደናቂ እና በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል ብዙዎች መሳተፍ የቻሉት መሆኑን አስታውሰዋል።

ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት የተካፈሉት በርካታ የጣሊያን አገር ምዕመናን የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ የገለጹ ሲሆን፣ ከጣሊያን ውጭ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ምዕመናንም በጸሎት ለመተባበር በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጸሎት ልምድ ፈጽሞ የሌላቸው ምዕመናን የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ የተካፈሉት በእንባ በመተናነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ልብን ሁሉን ቻይ ለሆነው እግዚአብሔር ክፍት ሲያደርጉ ችግሮች ይወገዳሉ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ኮማስትሪ፣ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ሕይወት ከንቱ ነው ብለዋል። ወደ እመቤታችን ዘንድ በቀረበው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ ምዕመናን መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ በሕይወታችን ውስጥ ማድረግ ማድረግ ከምንችላቸው መልካም ተግባራት መካከል አንዱ ጸሎት ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ኮማስትሪ፣ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ስለምንችል ነው ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁለተኛ ደረጃ የጥንቃቄ ወቅትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ኮማስትሪ፣ በዚህ አስጨናቂ ወቅት ስልጣን ኃይል በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር እጅ መሆኑን አስረድተው የዓለምን ኤኮኖሚ ለማሽመድመድ ቫይረስን የምያህል በዓይን የማይታይ ተህዋሲ በቂ ነው ብለዋል። አክለውም በእንዚህ ወራት ለሌሎች መልካም ማድረግ ጥሩ መሆኑን ተምረናል ብለው፣ ብዙ ወጣቶች በየቤቱ ሄደው አቅመ ደካሞችን ሲያግዙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በርካታ ሰዎች ከካህናት አንድ ዕርዳታ ብቻ እንደሚፈልጉ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኮማስትሪ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት እንደነበር ገልዘዋል። ችግሮቻችንን በሌላ በምንም መንገድ ማቃለል አንችልም ብለው፣ ሕይወትን መቀየር የምንችለው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት የቻልን ቀን ብቻ ነው ብለዋል።  

ብጹዕ ካርዲናል ኮማስትሪ በጸሎት ሥነ ሥርዓት ወቅት መንፈሳውዊ ዝግጅቱን በየቀኑ ተከታተለው በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ወደ መላው ዓለም ማድረስ ለቻሉት የቫቲካን ሚዲያ ሰራተኞች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ተመሳሳይ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲያዘጋጁ ከበርካታ ምዕመናን ጥያቄ የቀረበላቸው መሆኑን ግልጸው፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መደበኛውን እና ዕለታዊውን መንፈሳዊ ዝግጅቶች የጀመረ መሆኑን አስታውቀዋል።    

10 June 2020, 19:38