ፈልግ

በየመን በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ፣ በየመን በጦርነት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ፣ 

ቫቲካን ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚያገለግል መመሪያ አወጣ።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በአገር ውስጥ ለሚከሰተው የሕዝቦች መፈናቀል ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱ ታውቋል። ማክሰኞ ሚያዝያ 27/2012 ዓ. ም. ይፋ የተደረገውን መመሪያ አዘጋጅቶ ያቀረበው የተዘጋጀ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኝ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና

“ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማበርከት የሚረዱ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ መመሪያው የተለያዩ ሐዋርያዊ መርሃ ግብሮችን እንደ መመሪያ በማቅረብ  በአገር ውስጥ ለተፈናቀሉት አስፈላጊው እገዛ እርዳታ የሚደረግባቸውን አራት የተግባር ዘርፎችን የያዘ ሲሆን እነርሱም በማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት የሚኖሩበትን አካባቢ ለቀው ለሚፈናቀሉ ቤተሰቦች የመጠለያ፣ የከለላ፣ ራሳቸውን ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር የማስተዋወቂያ መንገዶችን ማሳየት እና እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ መገኘት መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ባላቸው አክብሮት እነዚህን አራት የተግባር ዘርፎችን ማቅረባቸው ታውቋል። ከእነዚህ አራት የተግባር ዘርፎች በተጨማሪ ቤተክርስቲያን የተጠራችበትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ተፈናቃዮችን ለሚያጋጥሟቸው የትለያዩ ችግሮች በቂ ምላሽ እንድትሰጥ የሚያግዛት መሆኑ ታውቋል።

ለተፈናቃዮች የሚደረግ አቀባበል፣

ለተፈናቃዮች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት የተግባር አቅጣጫዎችን የሚያጠቃልል ሲሆን በተለይም በማኅበረሰብ መካከል ተረስተው የቀሩ ሰዎች ሕይወት ምን እንደሚመስል ግልጽ በማድረግ ቤተክርስቲያን የበኩሏን ሚና እንድተጫወት ያደርጋታል። ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ተቀብለው የሚያስተባግዱት በችግር ውስጥ ቢገኙም ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ ማንንም በማይጎዳ መልኩ ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ ሁለቱ ወገኖች የሚረዱበትን ሁኔታን ማመቻቸትን ይጠይቃል።

ለተፈናቃዮች ሕጋዊ ከለላን መስጠት፣

በመመሪያ ውስጥ የተቀመጠው የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑና፣ በአገር ውስጥ የሚፈናቀሉ ሰዎች ድንበርን ተሻግረው ወደ ሌላ አገር ክልል የማይገቡ ቢሆንም የደህንነት ዋትናን እና ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ተግባር በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት ያላው መሆኑ ታምኖበታል። በመሆኑም የየአገራቱ መንግሥታት ቀዳሚ ተልዕኮ ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከለላን እና የሕይወት ዋስትናን መስጠት መሆኑን መመሪያው ያስገነዝባል። መመሪያው ከዚህ በተጨማሪ የጦርነት ሰለባ ለሆኑት፣ ጾታዊ ጥቃት ለሚፈጸምባቸው ሴቶች ሕጻናት፣ ለወታደሮች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና በጎሳዎች መካከል በሚፈጠር ግጭቶች መገለል ለሚያጋጥማቸው በሙሉ የሕይወት ዋስትናን መስጠትን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል።

ለተፈናቃዮች የሚደረጉ አገልግሎቶችን ማጠናከር፣

ለተፈናቃዮች ቁሳዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ መካከል ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ማድረግ፣ በማኅበራዊ እና ኤኮናሚያው ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ተግቢ ይሆናል። የተሟላ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ለተፈናቃዮች ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን መመሪያው ያስገነዝባል። ብዙ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ቁሳዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በሌላ ወገን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ሳይሟላላቸው መቅረቱ ይስተዋላል። አዲስ መመሪያ ይህን ችግር በመገንዘብ ለተፈናቃዮች የሚደረጉ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን የተሟሉ ለማድረግ ተፈናቃዮች ከሚኖሩባቸው ሀገረ ስብከት ወይም ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመተባበር አስፈላጊ በሆኑ ዘርፎች ሐዋርያዊ ዕቅዶችንም ለማበርከት መርሃ ግብሮችን ዘርግቷል።      

ተፈናቃዮች ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ፣

ተፈናቃዮች ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግብ በተመለከተ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ዘላቂ መፍትሄን ማግኘት የሚችል ሃላፊነት ያለው የማኅበረሰብ ክፍል እንዲኖር ያሳስባል። የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ሥፍራ እንጂ ቋሚ መኖሪያቸው አይደሉም። በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎችን የተፈናቃዮች መጠለያን በተመለከተ ጥራቱን የጠበቀ የርጅም ጊዜ መጠለያን አዘጋጅቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል በማለት መመሪያው ያሳስባል።

የጋራ ጥረቶችን በተመለከተ፣

ከካቶሊካዊ ድርጅቶች እና ሀገረ ስብከቶች ከሌሎች ሐይማኖታዊ ተቋማት እና የአብያተ ክርስርቲያናት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች የሚደረገውን አገልግሎት የተሟላ እንዲያድረጉ መመሪያው ያበረታታል። ይሁንና የአገልግሎቱ ተልዕኮ እና ዓላማ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጥሪ እና አስተምህሮን የተከተለ እንዲሆን በማለት መመሪያው ያሳስባል። ሃሳቦችን፣ ዕውቀቶችን እና መረጃዎችን እርስ በእርስ መካፈል አስፈላጊ መሆኑን በማመን ካቶሊካዊ ድርጅቶች ያላቸውን መረጃዎችን ከተቀሩት ተባባሪ ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር እንዲጋሩ በማለት መመሪያው ያሳስባል።

ጠንካራ ግንኙነት ያለውን ማኅበረሰብ መገንባት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ105ኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ባላቸው አክብሮት አራት የተግባር ዘርፎችን ማቅረባቸው ሲታወስ እነርሱም የመጠለያ፣ የከለላ፣ ራሳቸውን ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር ማስተዋወቅ እና እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ መገኘት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል። እነዚህ የሐዋርያዊ ተግባር ዘር ቤተክርስቲያን ከማኅበረሰብ ለተገለሉት ለማቅረብ የተጠራችባቸው የተልዕኮ ተግባራት መሆናቸውን መመሪያው በግልጽ ያስቀምጣቸውል።

በተግባር የሚውሉ ተጨባጭ አስተያየቶች፣

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ በመጨረሻም አዲስ የወጣውን መመሪያ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል አንዳንድ ሃሳቦችን በውስጡ አካትቷል። የሐዋርያዊ ተግባሮች አቅጣጫን በተመለከተ ለአጋር ድርጅቶች የማኅበረሰብ ክፍሎች መረጃዎችን ማዳረስ፣ ግንዛቤን ማስጨበጥ እና ከመንግሥት አካላት ጋር የጋራ ውይይቶችን ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ መመርያው ያሳስባል።  የመመሪያውን ሙሉ ጽሑፍ “Migrants and Refugees websiteውስጥ በመግባት ማግኘት የሚቻል መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ያሳስባል።  

07 May 2020, 22:48