ፈልግ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በብራዚል፣ እ.አ.አ. 1997 ዓ. ም.    የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በብራዚል፣ እ.አ.አ. 1997 ዓ. ም.  

ካርዲናል ፓሮሊን፣ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልብ ለዓለም ሁሉ የተከፈተ ነበር አሉ።

የቅድስት መንበር ጋዜጣ የሆነው “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መቶኛ ዓመት የልደት መታሰቢያን በማስመልከት ይዞት በወጣው ባለ አሥራ አራት ገጽ ልዩ እትሙ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላምታ መልዕክት ጀምሮ እስከ ቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባበረከቱት ጽሑፍ ድረስ የርካታ ሰዎች የምስክርነት ቃላቸውን ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ካርዲናል ፓሮሊን፣

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከጋዜጣው ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የልደታቸውን 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ከማክበራቸው አንድ ሳምንት አስቀድመው 47ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን የተመለሱ መሆኑን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በወቅቱ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት በሜክስኮ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ወቅቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት ወር 1990 ዓ. ም. እንደ ነበር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የግል ትዝታ የሚጀሚረው ከ1990 ዓ. ም. ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል። በዚያን ጊዜ ከሜክሲኮ ሕዝብ መካከል 95 ከመቶ የሚሆነው የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደ ነበር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዋና ከተማው ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ የጓዳ ሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚገኝ በመሆኑ እና በሌሎችም የሃገሪቱ ክፍሎች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የሚጠሩ በርካታ ቤተ መቅደሶች የሚገኙ መሆኑን አስታውሰዋል። በወቅቱ የነበረው መንግሥ የአምልኮ ነጻነት የገደበ፣ ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ፈቃድ የማይሰጥ ቢሆንም በምዕመናኑ ልብ ውስጥ ለእመቤታችን ማርያም ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ወደ ሜክሲኮ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምንም የፖለቲካ ይዘት አልነበረውም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ከሐዋርያዊ ግብኝታቸው በኋላ ብዙ ሳይቆይ ሁኔታዎች ተቀይረው፣ መንግሥት ለረጅም ዓመታት ያህል ከቅድስት መንበር ጋር ሲያደርግ የቆየው የጋራ ውይይት መልካም ውጤት በማስመዝገብ በመካከላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመሩን አስታውሰው በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ በሜክሲኮ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለእምነት ፍለጋ ብቻ የተደረገ መንፈሳዊ ጉዞ መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ወደ ሜክሲኮ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ባሰሙት ንግግር “የታሪክ ባለቤት እና የጉዞአችን መድረሻ የሆነው እግዚአብሔር፣ የእኔ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ዓለም ሁሉ ወንጌልን የምሰብክበት፣ ምሕረት የሚገኝበትን የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜናን የማበስርበት እንዲሆን አመቻችቶልኛል” በማለት መናገራቸውን አስታውሰዋል። ይህን መልዕክታቸውን ካስተላለፉ ከአጭር ጊዜ በኋላ፣ ራሳቸውን የፍቅር እና የተስፋ መንፈሳዊ ተጓዥ በማድረግ፣ በሄዱበት ሁሉ ለምዕመናን መንፈሳዊ ብርታትን በመስጠት ለማበረታታት፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በማፍቀር እና ወንድሞቻቸውን በማገልገል ብዙ ፍሬን እንዲያፈሩ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምኞትን በአጭር አገላለጽ “የወንጌል ተልዕኮ” በማለት መግለጽ ይቻላል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ይህ ተልዕኮ ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ውዴታ ሳይሆን የወንጌል ተልዕኮ ግዴታ መሆኑን አስረድተው ሐዋ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 9:23 ላይ “ይህን ሁሉ ማድረጌ የምስራቹን ቃል በረከት ለመካፈል፣ ስለ ምስራቹ ቃል ብዬ ነው” እንደ ዋና መመሪያ መውሰዳቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል። በሜክሲኮ በነበራቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት ጊዜ በየቀኑ ሁለት ቀጠሮ ከምዕመናን ጋር እንደነበራቸው ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በአገሪቱ በሚገኙ አካባቢዎች በመገኘት ሁለት የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ያሳርጉ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት አማካይነት በየቀኑ የተልዕኮ መንገዶችን በማዘጋጀት፣ በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠሩት ወንድሞች እና እህቶች የቤተክርስቲያን በሮች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከሜክሲኮ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ቀጥለው፣ የዓለም ቤዛ፣ የሰው ልጅ እና የቤተክርስቲያን መንገድ በሚል ርዕሥ የመጀምሪያቸው የሆነውን ሐዋርያዊ መልዕክት ለዓለም ይፋ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከዚያን ጊዜ አንስቶ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣት፣ ቤተክርስቲያንም የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜናን ማብሰሯን የቀጠለች መሆኗን አስታውሰው፣ ይህ የሆነው ካቶሊካዊ ምዕመናን በዓለም ዙሪያ በሙሉ ስለሚገኙ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱ ሰው ልብ በማንኳኳቱ ነው በማለት አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ከፍተኛ ስቃይ እንደደረሳቸው ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፣ የወጣቶች ወዳጅ እንደነበሩ አስታውሰው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ሚያዝያ 15/1984 ዓ. ም. ለመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በላኩት መልዕክታቸው “ሰው መሆን እንደት መልካም ነገር ነው! ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሰው ስለነበረ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በቤተክርስቲያን ቋንቋ የወንጌል ተልዕኮ ማለት ከሁሉም በላይ አንድነት መሆኑን የጉባኤው ሰነድ ያስተምራል ብለው፣ የጉባኤው ሰነድ ቤተክርስቲያ እስከ ዛሬ ለተጓዘችባቸው ጊዜያት እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ወጣት ካህን፣ በኋላም በእርጅና ዕድሜ ላገለገሏት ቤተክርስቲያን መንገድ ከያሽ ሆኖ ማገልገሉን አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ሞመናን ለመጨረሻ ጊዜ የታዩበትን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤው እሑድ እንደነበር አስታውሰው፣ በዕለቱ እጅግ ከመድከማቸው የተነሳ ምንም ቃል ሳይናገሩ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል። “ሕይወት ተከፍቶ እንደሚቆይ መስኮት ነው” የተባለውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን “በዓለማችን በርካታ መስኮቶች እንዲከፈቱ፣ የግል ሕይወታቸው መስኮት ተከፍቶ የዓለም ብርሃን እንዲገባ ስላደረጉት ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልባዊ ምስጋናዬን አቀረባለሁ” ብለዋል።  

18 May 2020, 19:19