ፈልግ

የጤና ባለሞያዎች የሕክምና አገልግሎት በማበርከት ላይ፣ የጤና ባለሞያዎች የሕክምና አገልግሎት በማበርከት ላይ፣ 

“ለፍቅር ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች አሉ”!

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ፣ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ካህናት እና ሕሙማንን በመርዳት ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚያሳዩት ምሳሌ፣ መማር ያለብን ጠቃሚ ትምህርት መሆኑን ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ “ከኮሮና ወረርሽኝ በስተጀርባ ያለ ሕይወት” ባሉት አጭር ጽሑፋቸው አስታውቀዋል።

የቫቲካን ዜና

ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰዎች ላይ ያስከተለው ሕመም ቀልባችንን ስቧል ያሉት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ በራሳችን ላይ ካሉ ሕመሞች ጋር በመደመር መጽናናትን የምናገኝበት መሆኑን አስረድተዋል። ወረርሽኙ ሰዎችን በቀጥታ ከመጉዳቱ በተጨማሪ፣ በወረርሽኙ ተይዘው ለሚሰቃዩት ስጋዊ እና መንፈሳዊ እርዳታን ለማቅረብ የተሰማሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን አባ ፌደሪኮ አስረድተው ለእነዚህ ሰዎች በሕብረት ሆነን ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። የሕክምና እና መንፈሳዊ አገልግሎት ለማበርከት የተሰማሩት በርካታ የጤና ባለሞያዎች እና መንፈሳዊ አባቶች በወረርሽኙ መያዝ ብቻ ሳይሆን በሞት አደጋም የሚጠቁ መሆናቸውን አባ ፌደሪኮ ገልጸዋል።  

በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ስቃይ በሚታይበት ባሁኑ ወቅት በሕክምና ሞያም ሆነ በመንፈሳዊ አገልግሎቶች ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ሰዎች፣ የተጠሩበት የአገልግሎት ዘርፍ የሞት መስዋዕትነትን ጭምር የሚያስከፍል መሆኑን ለመገንዘብ በቅተዋል ያሉት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ በድፍረት መጋፈጣቸው በግድ የለሽነት ሳይሆን የተጠሩበት የፍቅር አገልግሎት ፍርሃትን የሚያደንፍ መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ነው ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 11/2001 ዓ. ም. በኒዩ ዮርክ ከተማ ወደ 3000 የሚሆኑ ሰዎች በአሸባሪዎች ጥቃት መሞታቸውን ያሳታወሱት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከሦስት መቶ በላይ ሰዎች የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች መሆናቸውን አስታውሰዋል። አደጋው ካስከተለው ድንጋጤ እና ስቃይ ባሻገር የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተግባር፣ በኒዩ ዮርክ ከተማ ነዋሪዎች ስነ ልቦና ውስጥ ታትሞ መቅረቱን አባ ፌደሪኮ አስታውሰዋል። ከእሳት አደጋ ሠራተኞች በተጨማሪ በአደጋው የተጠቁትን ለመርዳት ወደ ሥፍራው የደረሱ የጤና ባለሞያዎች እና በጎ ፈቃደኞችም መኖራቸውን አባ ሎምባርዲ አስታውሰው፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ፣ በጎርፍ እና በሌሎች አደጋዎች ምክንያት በሕይወታቸው ሊደርስ የሚችለውን ከባድ አደጋን ሳይፈሩ ነፍስ አድን ተግባርን የፈጸሙ ሰዎች መኖራቸውን ክቡር አባ ፌደሪኮ አስታውሰዋል።

በከባድ ስቃይ መካከል ፍቅር ሊገለጽ እንደሚችል የተናገሩት ክቡር አባ ፌደሪኮ፣ የዚህ ዓይነት ፍቅር ሞትን የማይፈራ፣ ምንም የማይሰስት እውነተኛ ፍቅር መሆኑን አስረድተዋል። “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመካከላችን አንዳንድ ሰዎች፣ በልባቸው የያዙትን ፍቅር አውጥተው በተግባር ሲገልጹ እንመለከታለን” ያሉት አባ ፌደሪኮ፣ በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እስካዩበት ቀን ድረስ በልባቸው ያለው ፍቅር ምን ያህል መሆኑንም አያውቁም ይሆናል ብለዋል።

በስቃይ እና በፍቅር መካከል አስገራሚ የሆነ ምስጢራዊ ግንኙነት አለ ያሉት ክቡር አባ ፌደሪኮ፣ ስቃይ፣ ፍቅር የሚበቅልበት፣ ልባችንም በፍቅር እሳት የሚቃጠልበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። እነዚህን የመሳሰሉ አጋጣሚዎች የሚናየው ባል ለሚስት ወይም ሚስት ለባል፣ በሕመም በሚሰቃዩበት ጊዜ አንዱ ለሌላው በሚያሳየው የፍቅር ምልክት የሚገልጽ መሆኑን ያስረዱት አባ ፌደሪኮ፣ በዚህ የፍቅር ዓይነት፣ የስቃይ ታሪክን በሙሉ ወደ ፍቅር የሚለውጡ መሆኑን አስረድተዋል።

“ራስን ለሞት አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር የለም” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ያስታወሱት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ርህራሄን እና ፍቅር በመገንዘብ ወደ እርሱ የፍቅር ጎዳና እንድንገባ ይጋብዘናል ብለዋል። አባ ፌደሪኮ በማከልም በራስ ወዳድነት መንፈስ ካልተያዝን በስተቀር “ራስን ለሞት አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር የለም” የሚለውን መልዕክት መረዳት የሚሳነው አይኖርም ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ከስቃይ ጊዜነት በተጨማሪ የደስታም ጊዜ ነው ያሉት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ ቫይረሱ ተላላፊ እንደመሆኑ ሁሉ ፍቅርም ከሰዎች ወደ ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል ብለዋል። በኒዩ ዮርክ ከተማ የተከሰተውን አደጋ በድጋሚ ያስታወሱት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ የእሳት አደጋን ለመከላከል የሰማሩ ሰዎች፣ ልጆቻቸው ዛሬ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ተሰማርተው መሥራት እንደሚፈልጉ እና እንደ አባቶቻቸው ለሌሎች የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የሚፈልጉ መሆኑን ገልጸዋል።  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ፣ ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ካህናት እና ሕሙማንን ለመርዳት የተሰማሩ ሰዎች ምሳሌ መማር ጠቃሚ እንደሚሆን ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ተናግረዋል።      

07 May 2020, 18:48