ፈልግ

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፒዮስ 11ኛ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ካህናት ጋር፣ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፒዮስ 11ኛ ዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ካህናት ጋር፣ 

በዓለም አቀፍ የጥሪ ቀን፥ “ለእግዚአብሔር እውነተኛ መልስ እንድንሰጥ ተጠርተናል”።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የችግር ወቅት እምነትን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ፣ ለጥሪ እውነተኛ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቲት ወር ባስተላለፉት የጥሪ ቀን መልዕክታቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል። እግዚአብሔርን በታማኝነት እና በፍቅር ለማገልገል የወሰኑ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በጸሎታችን እንድናግዛቸው ቤተክርስቲያን ጥሪ ማቅረቧ ታውቋል። በዚህም መሠረት በቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ ጥሪ እንዲያድግ፣ እሑድ ሚያዝያ 25/2012 ዓ. ም. ለ57ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቲት 29/2012 ዓ. ም. ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ በጣሊያን የቅዱስ ሳቨሪዮ ገዳማውያን ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ሮዛሪዮ ጃናታሲዮ እና የዘርዓ ክህነት ተማሪ ወጣት ካርሎስ ዱራን አስተያየታቸውን ማካፈላቸው ታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መደረጉ ሲታወቅ፣ በፖርቱጋል አገር የፖርቶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማኑኤል ዳ ሲልቫ ሮድሪገስ ሊንዳ በበኩላቸው የሀገረ ስብከታቸው ወጣቶች በጸሎት በመተባበር ብርታትን እንዲያገኙ አደራ ብለዋል። በአይርላንድም የዎተርፎርድ እና ሊስሞር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አልፎንሶ ኩሊናን፣ እግዚአብሔርን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው በሙሉ በድፍረት ተሞልተው ለጥሪያቸው ምላሽ እንዲሰጡ አደራ ብለዋል። በላቲን አሜሪካ የኮሎምቢያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትም በበኩላቸው ቤተክርስቲያንን ማገልገል አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለጥሪው ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የስፔን ብጹዓን ጳጳሳትም ወጣቶች በቤት ሆነው የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ቁጥር እንዲጨምር ጸሎት እንዲያደረጉ አደራ ማለታቸው ታውቋል። “መረብህን ጣልባቸው”! በሚል መርህ ቃል በመታገዝ የሁለት ቀናት የጸሎት ሥነ ሥርዓት በጀርመን መካሄዱ ታውቋል።

ቅዱስ ኩራቶ ዳርስ ያረፈበት 160ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጥሪ ቀንን ምክንያት በማድረግ ለካህናት ባስተላለፉት መልዕክት በአራት ቃላት እነርሱም፥ ስቃይ፣ ምስጋና፣ ድፍረግት እና ውዳሴ በሚሉት ቃላት ላይ ማስተንተናቸው ይታወሳል። እነዚህ አራቱ ቃላት አሁን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከትለውን የችግር እና የሕመም ጊዜን የሚገልጹ መሆናቸው ታውቋል። የቅዱስ ሳቨሪዮ ገዳማውያን ማሕበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ሮዛሪዮ ጃናታሲዮ እንደገለጹት የማኅበራቸው አባላት ወደ ዓለማችን ክፍሎች ሄደው  ወንጌልን በመመስከር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ 20 የማኅበራቸው አባላት በወረርሽኙ ተይዘው መሞታቸውን ተናግረው፣ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ድፍረት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። እጅግ አስፈሪ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜን ለማለፍ ድፍረት ያስፈልጋል ያሉት ክቡር አባ ሮዛሪዮ፣ ከኤኮኖሚያዊ ጉዳይ ይበልጥ ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሰሜን ጣሊያን፣ ፓርማ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የማኅበራቸው ጥውቅላይ ቤት በ43 ቀናት ውስጥ ብቻ 18 የማኅበሩ አባላትን በሞት እንዳጣቸው፣ የተቀሩት ሁለቱ በጣሊያን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ማረፋቸውን ክቡር አባ ሮዛሪዮ ገልጸዋል። ሐዋርያዊ እረኛ ከሚያገለግሉቸው ምዕመናን ጋር መሆን እና እነርሱን መምሰል አለበት በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ክቡር አባ ሮዛሪዮ፣ ምንም እንኳን ማኅበራቸው እነዚህን አባላት በሞት ያጣቸው ቢሆንም የወንጌል ምስክርነታቸውን ማህበርተኞቹ በሚገኙበት ሁሉ ቤተክርስቲያንን በማገልገል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሕብረትን በተግባር መግለጽ የማኅበራቸው ቀዳሚ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ሮዛሪዮ፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ልዩ ልዩ ታሪኮች፣ ባሕሎች እና ልማዶች ጋር ሕብረት በመፍጠር የማኅበሩን ዓላማ ተግባራዊ በማድረግ መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ኃይል የማገኘው ደካማ በምሆንበት ጊዜ ነው” (2ቆሮ። 12:10) ያለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ያስታወሱት ክቡር አባ ሮዛሪዮ፣ ዓለማችን በችግር ውስጥ ወድቆ በመቃተት ላይ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት ራስን በማጽናናት ብርታትን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አስረድተው ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ የሚገኘው ከጠንካራ ተቋም ሳይሆን በችግር ጊዜም እግዚአብሔርን ለማገልገል ደስተኞች ከሆኑ ወንዶች እና ሴቶች የግል መልስ ነው ብለዋል። ደስታ የሚገኝው ከምዕመናን ጋር በመሆን ፣ ወንጌልን በመመስከር እና በጸሎት መሆኑን ክቡር አባ ሮዛሪዮ አስረድተዋል።

ሮም ከተማ በሚገኝ “የቤተክርስቲያን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም” ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርትን በመከታተል ላይ የሚገኝ ተማሪ ካርሎስ ዱራን በበኩሉ፣ እንደ ማንኛውም ወጣት መደበኛ ሕይወቱን ይኖር እንደነበረ እና በየዕለቱ ጸሎት እንዲያቀርብ የሚገፋፋ ኃይል በልቡ ውስጥ እንደተፈጠረ ገልጾ፣ በልጅነት ዕድሜው እመቤታችን ቅድስት ማርያም ታይታው “ኢየሱስ ሆይ! አንተ የምትፈልገኝ ከሆነ ምን ጊዜም ያንተ ነኝ” ብሎ እንዲጽፍ ያደረገች መሆኑን አስታውሷል። ወላጅ እናቱም በጥሪው ደስተኛ መሆኑን የገለጸው ካርሎስ፣ በልቡ የካህናት እጥረት መኖሩን እንደሚያስብ አሳታውሷል። በልጅነቱ ትምህርተ ክርስቶስን መከታተል ሲጀምር ደስታ የተሰማው መሆኑን አስረድቷል። ከቁምስናው መሪ ካህን ጋር ሃሳብ መለዋወጥ ጀመርኩ ያለው ወጣት ካርሎስ፣ ካህኑ የወደፊት ሕይወት ግልጽ እንዲሆንለት እመቤታችን ማርያምን በጸሎት እንዲጠይቅ ምክር የተሰጠው መሆኑን አስታውሷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጥሪ ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሰው ወጣት ካርሎስ፣ ጥሪ ማለት ሁሉን ነገር በነጻ የምንቀበልበት፣ ስለዚህም ምስጋናችንን ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት አጋጣሚ መሆኑን ገልጾ፣ መጠራታችንን በትክክል ባንገነዘብም በስተጀርባው የእግዚአብሔር እጅ ያለበት መሆኑን ማወቅ ያቻላል ካለ በኋላ፣ እግዚአብሔር ራሱን አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን መውደዱን  ተናግሯል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣

   

04 May 2020, 16:43