ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ተካፋይ ሆነው፤   ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ተካፋይ ሆነው፤  

የሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥሪን በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ማግኘት የሚቻል መሆኑ ተገለጸ።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 13/2012 ዓ. ም ሐዋርያዊ ተልዕኮ የሚፈጽሙ መንፈሳዊ ማሕበራት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ የሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥሪን በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል መናገራቸውን አስታወቁ።

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ዘንድሮ በግንቦት ወር በሮም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሐዋርያዊ ተልዕኮ ብሔራዊ ጽ/ቤት መሪዎች ጉባኤ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቢሰረዝም የመልዕክታቸውን ሰነድ ለየአገራቱ መላክ መወሰናቸው ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ አክለውም መልዕክታቸው ለተልዕኮ አገልግሎቱ ደስታቸውን፣ ተስፋቸውን እና ጭንቀታቸውንም የገለጹበት መሆኑን አስረድተዋል። መልዕክታቸውን ለእያንዳንዱ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ብሔራዊ ጽ/ቤት የላኩት በመሆኑ፣ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲያዩት፣ እንዲያጠኑት እና እንዲያስተንትኑበት የፈለጉ መሆኑን አስረድተው፣ የቅዱስነታቸው መልዕክት ለብሔራዊ ጽሕፈት ቤቶቹ መሪዎች መመሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ መላው ምዕመናን በሐዋርያዊ ተልዕኮ አገልግሎት ምን ያህል ተሳትፎ እንዳላቸ ራሳቸውን ለመጠየቅ የሚያስችል መልዕክት መሆኑንም ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮአችን ውጤታማ እና ግልጽ እንዲሆን ይፈልጋሉ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን እና የአመራር መንገዶችን በመጠቀም ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ገደብ ማበጀት እና የውጤቱን መጠን ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ትክክል አይደለም ያሉትን አስታውሰው፣ የተለያዩ የተልዕኮ ስልቶችን እና የአመራር መንገዶችን መጠቀም ውጤታማ ለመሆን የሚያግዝ ቢሆንም መሠረታዊውን የቤተክርስቲያን ሐዋርያነት ተልዕኮ መንገድን የሚተካ መሆን የለበትም ማለታቸውን አስታውሰዋል።  ትኩረቱን በማስተዳደር አገልግሎት ብቻ ያደረገ ቤተክርስቲያን፣ ፍሬው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው መሠረታዊውን እውነት እንድንረዳ ይፈልጋሉ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ በእግዚአብሔር ማመን ራሱ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር መንግሥትም በእግዚአብሔር የተመሠረተ እና ተፈጻሚነቱንም ከእግዚአብሔር የሚያገኝ፣ በእግዚአብሔር የተመሠረተች ቤተክርስቲያን ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ወንጌልን የምታበስረው፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ዘንድ በላከው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው የቤተክርስቲያን ሐዋርያነት ተልዕኮ የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ የሰው ልጅ እቅድ እንዳልሆነ የተናገሩትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ግዴታችን እና ቀዳሚ ሚናችን ዘወትር በመጸለይ፣ በተሰጡን መለኮታዊ ስጦታዎችን በእምነት በመቀበል፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አገልግሎታችንን ማቅረብ ስንችል እንደ ሆነ አስረድተዋል። ከዚህ መሠረታዊ ጸጋ ውጭ የሚካሄድ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ድርጅታዊ ተግባር ብቻ ሆኖ ከመቅረቱ ባሻገር ወደ ሰብዓዊ እቅድ ደረጃ ዝቅ እንደሚል መናገራቸውን አስታውሰዋል። ይህ እንዳይሆን ወደ ትክክለኛው የቤተክርስቲያን ሕይወት በመመለስ፣ የእግዚአብሔር ስጦታ በሆኑት፥ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ ካልታገዝን በቀር ሐዋርያዊ ተልዕኮአችን አድካሚ እና አሰልቺ በመሆን ተስፋን የሚያስቆርጥ ሊሆን እንደሚችል ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ተናግረው፣ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የምንመራ ከሆነ ግን በሐዋርያዊ ተልዕኮአችን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በደስታ እና በተስፋ መቋቋም እንችላለን ብለዋል።

በሐዋርያዊ ተልዕኮ መካከል ራስ ወዳድነት እና ራስን ማስቀደም፣ ተልዕኮን ወደ ተራ አገልግሎት ይለውጠዋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ይህም ቀስ በቀስ ስለ ራስ ብቻ ወደ ማሰብ፣ የግል ዝናን ወደ መፈለግ፣ የመንፈስ ቅዱስ አስደናቂ ሥራን በመዘንጋት ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት የሚገኝበትን መልካም ዜናን እና የኢየሱስ ክርስቶስ ርህራሄ ወደ መርሳት የሚያደርስ መሆኑን አስረድተዋል። በርካታ ሕዝብን መሰብሰብ ሲጀምሩ እና ስማቸው በብዙዎች ዘንድ እንደሚጠራ ሲሰሙ ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ፣ ሌላ ድጋፍ እንደማያስፈልጋቸው የሚያስቡ እንዳሉ ያስታውሱት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ እነዚህ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን እርዳታ መለመን፣ የሰዎች እገዛን መጠየቅ ውርደት መስሎ ይታያቸዋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ድክመት እንድናስወግድ ይፈልጋሉ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ራስን በማስቀደም፣ ከተቀረው ዓለም ራስን መነጠል የሐዋርያዊ ተልዕኮ ተቃራኒ መሆኑን በመገንዘብ ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ስኬታማነት፣ ከራስ አስተሳሰብ ወጥቶ የሚኖሩበትን አካባቢ መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዘወትር ጥሪያቸው፣ በሮቻችንን ከፍተን ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ፣ ወደ ጎረቤቶቻችን፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ወደ ተረሱት፣ ወደ ተናቁት፣ በስቃይ ውስጥ ወደሚገኙ፣ ወደ ቆሰሉት ፣ ግራ ወደተጋቡት እና ወደ ወጣቶች ዘንድ መሄድ ያስፈልጋል ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ አስታውሰው፣ እነዚህን ሰዎች በዓይናችን መመልከት ስንችል ራሳችንን እና እግዚአብሔርን መመልከት እንችላለን ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮአችንን ወደ መንፈስ ቅዱስ ተግባር መመለስ ያስፈልጋል ማለታቸውን ያስታወሱት ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ መኖሪያ እና የብርቱ አገልጋዮቿ መጠለያ መሆኑን አስረድተዋል። ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምራ የተልዕኮ ጥሪ አለባት ያሉት ብጹዕነታቸው፣ ቤተክርስቲያን ዘለዓለማዊ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆኗንም አስረድተዋል። ሐዋርያዊ ተልዕኮ የሚፈጽሙ መንፈሳዊ ማሕበራት የበላይ ተቆጣጣሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተመሠረተበት ዋና ዓላማ በጸሎት ለመበርታት፣ በዕለታዊ ሕይወት የቸርነት አገልግሎትን በማበርከት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የጸጋ ስጦታን በቅድስና ወደ ሌሎች ዘንድ ለማዳረስ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን አስታውሰዋል። የሐዋርያዊ ተልዕኮ ፈጻሚዎች ማሕበራት ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተመሠረተው፣ ራሳቸውን ለጸሎት እና ለቸርነት አገልግሎት ባስገዙት ወንዶች እና ሴቶች መልካም ፈቃድ መሆኑን አስረድተው፣ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን የሐዋርያዊ አገልግሎት ጥሪን በእለታዊ ሕይወታቸው መካከል፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ፣ በትምህርት ቤት እና በቁምስናዎች ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ አስረድተዋል።                   

28 May 2020, 17:45