ክቡር አቶ ጉቴረዝ፣ ቅድስት መንበር ለምታበረክተው ድጋፍ ቅዱስነታቸውን አመሰገኑ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ በዓለማችን የሚከሰቱ አዳዲስ ችግሮችን ለመፍታት አዲስ የአንድነት እና የመደጋገፍ መንገድ ማመቻቸት የሚያስፈልግ መሆኑን አስታወቁ። አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አንዳንድ አገራት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ለማድረግ ቅድስት መንበር ላደረገችው ድጋፍ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አመስግነዋል።
የቫቲካን ዜና፤
“ከሁሉ አስቀድሜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ማመስገን እፈልጋለሁ” ያሉት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ የድርጅታቸው ቀዳሚ ዓላማ እና ተግባር በአገሮች መካከል ሰላምን እና አንድነትን በማሳደግ በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና መከራ በመቀነስ ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ መሆኑን ለቫቲካን ሚዲያ ገልጸዋል። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች የተነሱ ጦርነቶችን እና አመጾችን ማስቆም፣ በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጥፋትን እያስከተለ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለማስቆም የጋራ ጥረት የሚያስፈልግ መሆኑንም አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪን 115 መንግሥታት፣ በርካታ ክልላዊ ድርጅቶች ፣ ከሁለት መቶ የሚበልጡ ማኅበራዊ ቡድኖች እና ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ መሪዎች ተስማምተውበት ያጸደቁት መሆኑን እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግለ ሰቦች አቋማቸውን በፊርማቸው የገለጹ መሆኑን አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ አስታውቀዋል። በመሆኑም አስራ ስድስት የሚሆን የተለያዩ መሣሪያ ታጣቂ ቡድኖች የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ከአመጽ እና ከጦርነት አውድማ የወጡ መሆኑን አስታውቀዋል። ሌላው እጅግ አስፈላጊው የድርጅታቸው ጥሪ፣ ሰላም በቤተሰብ መካከል እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑን የገለጹት አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ በሴቶች እና በወጣት ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት በአሳሳቢ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ መንግሥታት፣ ማኅበራዊ አገልግሎትን በቅረብ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች፣ ሴቶችን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ገልጸው፣ የሐይማኖት ተቋማትም እገዛቸውን በማከል በሴቶች እና ወጣት ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት እና ክፉ ተግባርን በሙሉ ድምጻቸው እንዲቃወሙት ጥሪ ማስተላለፋቸውን አስረድተዋል።
ኮቪድ-19 በሰው ሕይወት ላይ ያስከተለው የጤና መቃወስ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በውጭ አገር ዘጎች ላይ የሚያሳዩት የጠላትነት ስሜት በርካታ የሕክምና ባለሞያዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ያነጣጠረ መሆኑን አስረድተው፣ ወረርሽኙ እያስከተለ ካለው የጤና መቃወስ ጋር ተደምሮ ችግሩን ያባባሰው መሆኑ አስረድተዋል። ይህ ተጨማሪ ቀውስን እንዳያስከትል በኅብረተሰብ እና በአገሮች መካከል አንድነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀው፣ የድርጅታቸው ተግባር የሰዎችን ነጻነት እና ክብርን ማስጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል። የትምህርት እና የዲጂታል ሚዲያ ተቋማት በሕዝቦች መካከል የሚታየውን የዘረኝነት መንፈስ እንዲታገሉት ማሳሰቢያ መስጠታቸውን ያስታወሱት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕዝቡ መካከል ጥላቻን የሚቀሰቅሱ መረጃዎችን እንዳያሰራጩ፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕጎችን እንዲያከብሩ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በማኅበረሰብ መካከል ሰላምን እና ፍቅርን በመስበክ እና በማስተማር ከፍተኛ ሚናን መጫወት የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመትረፍ የሚያግዝ ጠቃሚ ሃሳብ እና ምክር በመፈለግ ላይ የሚገኙ በርካታ ማኅበረሰቦች በዓለም ዙሪያ መኖራቸውን ያስታወሱት ክቡር አቶ ጉቴረዝ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚሰራጩ የተለያዩ የሐሰት መልዕክቶችን በማረም እና ሙሉ በሙሉ በመቃወም ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ በማድረስ ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን እና የመረጃ ማዕከላትን አመስግነዋል። ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከየአገራቱ የጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መንግሥታት እና የሐይማኖት ተቋማት ማኅበረሰቡ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ የሚያግዙ ምክሮችን እና ትምህቶችን በመስጠት ትልቅ አስተዋጾን ማበርከት የሚችሉ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኮሮና ቫይረስ አስከፊነትን በአንክሮ የተናገሩት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተረዝ፣ "ከምን ጊዜም በበለጠ እርስ በእርስ ተሳስሮ የሚገኝ ዓለማችን፣ ሙሉ በሙሉ ከኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ነጻ መሆን ካልቻለ፣ ማንም ከወረርሽኙ ነጻ መሆን አይችልም" ብለዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ውስጥ የህክምና ድጋፍ እና መድኅኒቶችን ለተወሰኑ አገሮች እና ማኅበረሰቦች ብቻ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ያስረዱት ዋና ጸሐፊው፣ እያንዳንዱ አገር፣ ማኅበረሰ እና ግለሰብ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን የገንዘብ አቅም ግንዛቤን ውስጥ በማስገባት፣ ውጤታማ የክትባት እና የመድኃኒት አቅርቦትን በቀላሉ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። "የኤኮኖሚ አለመመጣጠን በጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በተቀሩትም ማሕበራዊ ሕይወት ተጽዕኖን ፈጥሯል" ያሉት ክቡር አቶ ጉቴረዝ "ዓለማችንን ያጋጠመው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይህን ሃቅ ጉልህ አድርጎ አሳይቶናል" ብለዋል። በዓለማችን በሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በአምስት መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት ሕይወት ሊጠቁ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ ይህ እንዲከሰት ፈጽሞ አንፈቅድም ብለው፣ በኤኮኖሚ የበለጸጉት አገሮች በማደግ ላይ ወዳሉ አገሮች ሄደው የተፈጥሮ ሃብታቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙበትን መንገድ እንዲያሳዩ እና እንዲያግዟቸው አሳስበይ፣ ይህን አንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መሻገር፣ ዓለማችን ደህንነቱ ወደ ጠበቀ ፣ ጤናማ ፣ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነው ማኅበራዊ ህይወት ሊያሸጋግር እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለማገገም ሌሎች ተጨማሪ ማኅበራዊ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ያሉት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ በኤኮኖሚ አለመመጣጠን መቀነስ ፣ የጾታ እኩልነት ማረጋገጥ፣ የአካባቢ ጥበቃን እና እንክብካቤን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የእድገት ግቦችን እና የፓሪሱ የአየር ለውጥ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለ መሆኑን የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ ድርጅታቸውም ሆነ መላው ዓለም ቅድሚያን ሰጥቶ ጥረት እያደረገ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን አስረድተው፣ ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ በመላቀቅ ለሁሉም የሰው ልጅ የተሻለ ዓለም ለመገንባት ድርጅታቸው እየሠራ መሆኑ ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።