ፈልግ

በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በፓናማ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል፤ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በፓናማ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል፤ 

ሁለት ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ለሌላ ጊዜ መዛወራቸው ተነገረ።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በመግለጫቸው እንዳስገነዘቡት  በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሁለት ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ለሌላ ጊዜ መዛወራቸው አስታውቀዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሰኔ ወር 2021 ዓ. ም. በሮም ሊካሄድ የታቀደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ወደ ሰኔ ወር 2022 ዓ. ም. መዛወሩን እና እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በነሐሴ ወር 2022 ዓ. ም. በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ሊካሄድ የታቀደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልም ወደ ነሐሴ ወር 2023 ዓ. ም. መዛወሩን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል፣ ጽሕፈት ቤታቸው የሚያስተባብሯቸው ሁለት ትላልቅ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለሌላ ጊዜ መዛወራቸውን ገልጸው፣ የኮርሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምቹ ጊዜን ባለመስጠቱ ፣ በሰኔ ወር 2013 ዓ. ም. በሮም ሊካሄድ የታቀደው የቤተሰብ ጉባኤ ወደ ሰኔ ወር 2014 ዓ. ም. መዛወሩንና በነሐሴ ወር 2014 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው የወጣቶች ፌስቲቫል ወደ ነሐሴ ወር 2015 ዓ. ም. መዛወሩን አስታውቀዋል።   

ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ሁለቱም ስብሰባዎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ አሁን የምንገኝበት የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ፊት ምን ሊያስከትል እንደሚችል በውል ማውቅ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በተለይ በሚቀጥለው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ምን ያህል ሰው እንደሚካፈል እርግጠኛ መሆን አልተቻለም ብለዋል። ካርዲናል ፋሬል አክለውም ጽሕፈት ቤታቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሮም ሀገረ ስብከት እና በፖርቱጋል፣ የሊስቦን ከተማ የ2014 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በተደረገው ውይይት ወደ ፊት ለማራዘም ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን አስረድተዋል። “አሁን የምንገኝበት የችግር ወቅት አልፎ ወደ መደበኛ ኑሮ ለመመለስ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ብሔራዊ የቤተሰብ እና የወጣቶች ስብሰባዎችን እንደሚያዘጋጁ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል፣ ጽሕፈት ቤታቸው ከእነዚህ ሀገረ ስብከቶች ጋር አብሮ በመሥራት የቤተሰብ እና የወጣቶች መንፈሳዊ ሕይወት ለመንከባከብ እና ለማሳደግ የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ በቀጣይነት እንደሚደረጉ የገለጹት ካርዲናል ፋሬል፣ እርግጠኛ ሆነው ለማዘጋጀት ያልቻሉትም ከአንድ ዓመት እና ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄዱ ስብሰባዎች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ሥራቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ከማስተባበር አልፎ የቤተሰብ እና የወጣቶች ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማሳደግ በየቀኑ በርትተው የሚሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም ሕዝብ መልዕክታቸውን በየቀኑ የሚያስተላልፉ መሆኑን የገለጹ ካርዲናል ፋሬል፣ ቤተሰብ ብዙ ነገሮችን የሚያስተምር የሕይወታችን ማዕከል ነው ብለው፣ የምንገኝበት የችግር ጊዜ ብዙ ነገርን እንደሚያስተምረን እና የብቸኝነት ሕይወት ተወግዶ በቤተሰባዊነት መንፈስ እርስ በእርስ ተጋግዞ መኖር የግድ ነው ብለዋል። ይህ ጊዜ የብቸኝነት ሕይወትን ወደ ጎን አድርገን የጋራ ሕይወት እንድንማር ከእግዚአብሔር የተሰጠ ድዕል ነው ብለዋል። እያንዳንዱን ሰው እንደ እህት እና እንደ ወንድም መመልከት ያስፈልጋል ብለው፣ መማር ያለብን ትልቅ ነገር፣ ቤተሰብ አብሮ በመኖር እርስ በእርስ የምንተዋወቅበት ሥፍራ መሆኑን ነው ብለዋል። ብቻችን ስንሆን ማከናወን የማንችላቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ጊዜው የሰው ልጆች ስቃይ ጎልቶ የሚታይበት ቢሆንም በሌላ ወገን መረዳዳትን እና መተሳሰብን የምንማርበት ወቅት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል አስረድተዋል።

በሕይወታችን ጸጥታን መማር አስፈላጊ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን ያስታወሱት ካርዲናል ፋሬል፣ በዚህ ወቅት መንፈስ ቅዱስ የሚናገረንን በማድመጥ፣ ልጆቻችንም እንዲያደምጡት ማስተማር ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዘወትር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸው መላውን ዓለም የሚያስታውሱ መሆኑን በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል ገልጸዋል።

30 April 2020, 19:42