ፈልግ

“የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ወንድማማችነት” መጽሐፍ፣ “የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ወንድማማችነት” መጽሐፍ፣ 

“ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የሚኖረን ጊዜ የወዳጅነት ጊዜ ይሆናል”።

በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በቅርቡ ባሳተሙት “የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ወንድማማችነት” በሚለው መጽሐፋቸው ከኮሮና ቫይረስ በኋላ የሚኖረን ጊዜ የወንድማማችነት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በግል ደረጃ በእያንዳንዱ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ገብቶ ጉልበቱን አሳይቶናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓሊያ፣ የመሠረትናቸው ቤተሰባዊ፣ መንግሥታዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት ሕይወታችንን ለመንከባከብ እና ለማሳደግ፣ እንዲሁም ራሳችንን ችግር ለመከላከል ያቋቋምናቸው ቢሆንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም አቅመ የሌላቸው መሆኑን አይተናል ብለዋል። ሊቀ ጳጳሱ እንዳስረዱት፣ የወደ ፊት ማኅበራዊ ሕይወት ጠንካራ እንዲሆን ከተፈለገ በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ የአንድነት ሕይወት መሆን አለበት ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንሶ ፓሊያ ከዚህም ጋር በማያያዝ እንዳስረዱት እርሳቸው የሚመሩት የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፣ ከኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ሥነ ምግባር እና ባህልን የተላበሰ ሰፊ የውይይት መድርክ የሚከፍት መሆኑን አስታውቀዋል። ዋና መንደርደሪያ ሃሳብም “ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት እና ጸረ ወረርሽኝ አንድነት” የሚል እንደሚሆን በቫቲካን ዜና አገልግሎት ከጣሊያንኛ ቋንቋ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በሕመም ላይ የሚገኝ ዓለማችንን ሳናውቅ እውነት መስሎን እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ወደ ፊት ስንጓዝ ነበር ፤ ነገር ግን ይህ ሩጫችን ትክክለኛ አልነበረም፤ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቀድሞ ሌላ ወረርሽኝ በመካከላችን ገብቶ ነበር በማለት የተናገሩትን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ “ቫይረስ የብቸኝነት፣ የራስ ወዳድነት እና የስግብግብነት ቫይረስ ነበር፤ ማኅበረሰባችንን እጅግ ጎድቶ የቆየ ነበር። እንዳይታይብን የምንደብቀውን ራስ ወዳድነት የኮሮና ቫይረስ ይፋ አደረገው፤ የኮሮና ቫይረስ ድክመታችን እና ስህተታችን እንድንመለከት አደረገን፣ እውነተኛ ማንነታችንን እንድንመለከት አደረገን” በማለት በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ አስረድተዋል።

ዕለታዊ ሕይወታችንን የተመለከትን እንደሆነ፣ ዓለማችንን ያየን እንደሆነ እርስ በእርስ የጠበቀ ግንኙነት አለን ያሉት ሊቀ ጳጳሳ ፓሊያ እያንዳንዳችን የምናከናውነው መልካም ሆነ ክፉ ሥራ የግል ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የሚያካትት መሆኑን አስረድተው፣ በዛሬው ዘመን የምናደርገው ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የግል ውሳኔዎች እና ምርጫዎች ወንድማማችነትን የተላበሱ የጋራ አመለካከት ያላቸው መሆን አለበት ብለው፣ ካልሆነ ግን ጥፋትን የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ በማከልም ዓለም አቀፋዊ አንድነትን ማበጀት የእግዚአብሔር እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል ብለው ይህን ለመፈጸም ፍጥረትን በጋራ በመንከባከብ ምድራችንን ለመጭው ትውልድ ማስረከብ ይኖርብናል ብለዋል። የኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰውም ለፍጥረታት አስፈላጊውን ክብር እና እንክብካቤን ካለማድረጋችን ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ በሰው ሕይወት ላይ የሞት አደጋ የደረሰው በትውልድ እና በፍጥረት መካከል ጤናማ ግንኙነት ካለመኖሩ የተነሳ ነው ብለዋል።                     

30 April 2020, 20:24