ፈልግ

የካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን የካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዝ ዕርዳታ ለቤተክርስቲያናት የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ።

ካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ በመባል የሚታወቅ ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ ቤተክርስቲያናት የሚያግዝ መሆኑን አስታወቀ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋቢት 28/2012 ዓ. ም. በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመርዳት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ማዋቀራቸው ይታወሳል። ይህን የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በጋራ የሚያስተባብሩት ካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅት እና በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር አስተባባሪ ጽሕፈት ቤትን የሚመሩ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ሲሆኑ ዋና ጸሐፊው ክቡር አባ ብሩኖ ማሪ ዱፌ እና ምክትል ዋና ጸሐፊው ክቡር አባ አጉስቶ ዛምፒኒ መሆናቸው ታውቋል። የካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን በበኩላቸው የመርሃ ግብሩ ምክር ቤት አባል በመሆን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ያላቸውን መረጃ በማጋራት ምክር ቤቱን በአባልነት የሚያግዙ መሆኑን አስታውቀዋል።

ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን፣ ጽሕፈት ቤታቸው ከቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ መሠረታዊ እገዛዎችን የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ጽሕፈት ቤታቸው ከሚያዝያ 8/2012 ዓ. ም. ጀምሮ የድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር መጀመሩን ያስታወቁት ክቡር አቶ አሎይሲስ፣ ከለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በሚገኙ ድጋፎች በየአገራቱ የሚገኙ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶችን በመደገፍ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጎዱ ቤተሰቦች የምግብ፣ የሕክምና አገልግሎት እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ዕርዳታው በቀዳሚነት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቁ አገራትን ለመርዳት እና የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ የሚውል መሆኑን የተናገሩት ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን ይህም የሕክምና አገልግሎትን፣ የመከላከያ እና መቆጣጠር መንገዶችን በማስተማር ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የመጸዳጃ አገልግሎትን ማሳደግ፣ የመከላከያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እንደሚሆን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለሕዝቡ የመረጃን በስፋት ለማዳረስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጽሕፈት ቤታቸው በርትቶ የሚሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሁን የምንገኝበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ጥረት የምናደግበት ብቻ ሳይሆን በየአገራቱ የሚገኙ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችን በማገዝ፣ ለተረጂዎች የሚደረገው አገልግሎት ፍሬያማ እንዲሆን ከጎናቸው የምንቆምበት ጊዜ መሆኑን ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን አስታውቀዋል።                  

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ከካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅት ጋር ያዋቀሩት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በየአገራቱ ለሚገኙ ቤተክርስቲያናት ዕርዳታን መላክ የጀመረ መሆኑንም ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብር አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ከ140 በላይ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በባገኘው መረጃ መሠረት የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከል በወጡ እቅዶች በመመራት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ታውቋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማሰባሰብ መርሃ ግብርን መደገፍ የሚፈልጉ በሙሉ ወደ ካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ ድረ ገጽ በመግባት፣ እርዳታ ማሰባሰቢያ ቅጽን በመሙላት ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ መሆኑን ክቡር አቶ አሎይሲስ ጆን አስታውቀዋል።

23 April 2020, 23:04