ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋረል፣ ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋረል፣  

ካርዲናል ፋሬል “በችግር ውስጥ ብንገኝም ለቤተሰብ እና ወጣቶች ዕድገት መሥራትን አላቋረጥንም”።

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል፣ ጽሕፈት ቤታቸው የሚያስተባብሯቸው ሁለት ትላልቅ ስብሰባዎች ለሌላ ጊዜ መዛወራቸውን በማስመልከት ባደረጉት ቃለ ምልል፣ የኮርሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምቹ ጊዜን ባለመስጠቱ ፣ በሰኔ ወር 2013 ዓ. ም. በሮም ሊካሄድ የታቀደው የቤተሰብ ጉባኤ ወደ ሰኔ ወር 2014 ዓ. ም. መዛወሩንና በነሐሴ ወር 2014 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው የወጣቶች ፌስቲቫል ወደ ነሐሴ ወር 2015 ዓ. ም. መዛወሩን አስታውቀዋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ሁለቱም ስብሰባዎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ አሁን የምንገኝበት የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ፊት ምን ዓይነት ጊዜን ሊያስከትል እንደሚችል በውል ማውቅ አስቸጋሪ ነው ብለው በተለይ በሚቀጥለው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ላይ ምን ያህል ሰው እንደሚካፈል እርግጠኛ መሆን አልተቻለም ብለዋል። ካርዲናል ፋሬል አክለውም ጽሕፈት ቤታቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሮም ሀገረ ስብከት እና በፖርቱጋል፣ ሊስቦን የ2014 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አዘጋጅ ጽሕፈት ቤት ጋር በተደረገው ውይይት መሠረት ወደ ፊት ለማራዘም ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን አስረድተዋል። “አሁን የምንገኝበት የችግር ወቅት አልፎ ዕለታዊ ኑሮአችን ወደ ቀድሞ መንገድ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ከሞላ ጎደል በየአገሮቻቸው የቤተሰብ እና የወጣቶች ስብሰባዎችን እንደሚያዘጋጁ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል፣ ጽሕፈት ቤታቸው ከእነዚህ ሀገረ ስብከቶች ጋር አብሮ በመሥራት የቤተሰብ እና የወጣቶች ሕይወት ለመንከባከብ እና ለማሳደግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ወደ ፊት ቀጣይነት ይኖራቸዋል ብለው እርግጠኛ መሆን ያልቻሉትም ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ሥራቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ማስተባበር ብቻ ሳይሆን፣ የቤተሰብ እና የወጣቶች ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማሳደግ በየቀኑ በርትተው የሚሠሩ መሆኑን አስረድተዋል። ጽሕፈት ቤታቸው የየዕለቱን ተግባራትን በሚገባ ማከናወኑን አላቋረጠም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል፣ እርሳቸውም በየቀኑ በጽሕፈት ቤታቸው የሚገኙ መሆኑን ገልጸው በወረርሽኙ ምክንያት ከተቀጣሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ሥራቸውን በቤታቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ ቢሮ ውስጥ እንደሚሠሩ ገልጸው፣ የተቀሩት በሚመቻቸው ቀን እየመጡ የሚያከናውኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም ሕዝብ መልዕክታቸውን በየቀኑ የሚያስተላልፉ መሆኑን የገለጹ ካርዲናል ፋሬል፣ ቤተሰብ ብዙ ነገሮችን የሚያስተምር የሕይወታችን ማዕከል ነው ብለዋል። የምንገኝበት የችግር ጊዜ ብዙ ነገርን ያስተምረናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፋረል፣ የብቸኝነት ሕይወት ተወግዶ በቤተሰባዊነት መንፈስ እርስ በእርስ ተጋግዞ መኖር የግድ ነው ብለው፣ አሁን የምንገኝበት ወቅት የብቸኝነት ሕይወት ወደ ጎን አድርገን የጋራ ሕይወት እንድንማር ከእግዚአብሔር የተሰጠ ድዕል ነው ብለዋል። በመሆኑም እያንዳንዱን ሰው እንደ እህት እና እንደ ወንድም መመልከት ያስፈልጋል ብለው በዚህ ጊዜ መማር ያለብን ትልቅ ነገር ቢኖር፣ ቤተሰብ ከምን ጊዜም በበለጠ እርስ በእርስ የምንተዋወቅበት ሥፍራ ነው ብለዋል። እያንዳንዳችን ብቻችን ብንሆን ማከናወን የማንችላቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ይህን ዘንግተን ለራሳችን ብቻ ስንጨነቅ እንታያለን ብለዋል። ጊዜው የሰው ልጆች ስቃይ ጎልቶ የሚታይበት ቢሆንም በሌላ ወገን ይህ ወቅት መረዳዳትን እና መተሳሰብን የምንማርበት ወቅት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፋሬል አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሕይወታችን ጸጥታን መማር አስፈላጊ እንደሆነ፣ ከዚህም ጋር መንፈስ ቅዱስ የሚለውንም በማድመጥ፣ ልጆቻችንም መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን እንዲያዳምጡ ማስተማር ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰው እግዚአብሔርን በማሰብ፣ ስለ ሕይወታችን በማሰብ፣ ዛሬ እንዴት እንደምንኖር፣ ይህ ወረርሽኝ ሲያልፍ እንዴት እንደምንሆን ማሰብ ያስፈልጋል ማለታቸውንም አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየዕለቱ በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መላውን ዓለም የሚያስታውሱ መሆኑን ገልጸው እርሳቸውን ማድመጥ አስፈላጊ እንደሆነ፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል ገልጸዋል።

23 April 2020, 22:34