ፈልግ

የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት፣ 

ክርስቲያናዊ እምነትን ባልተከተለ የጋብቻ ሕይወት ላይ ውይይት መደረጉ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ምክር ቤት፣ መንፈሳዊ እምነትን እና ቅዱሳት ምስጢራትን አስመልክቶ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ፣ ክርስቲያናዊ እምነትን ባልተከተ የጋብቻ ሕይወት ላይ ውይይት ማድረጉን አስታወቀ። በካቶሊክ እምነት እና ቅዱሳት ምስጢራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያብራራ ሥነ መለኮታዊ ሰነድ ተዘጋጅቶ መቅረቡን የኢየሱሳዊያን ማኅበር አባል እና የሥነ መለኮት ጠበብት የሆኑት ክቡር አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ አስታውቀዋል። አባ ጋቢኖ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ሰነዱ ቤተክርስቲያን ለምዕመናን የምታቀርበውን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በብቃት ለማዳረስ ተጨማሪ እገዛን ያበረክታል ብለዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፉ ሥነ-መለኮታዊ ምክር ቤቱ በ50 ዓመት ዕድሜው በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት እና በቅዱሳት ምስጢራት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ ያጠና መሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ2014 – 2019 ዓ. ም. ጥናቱን በበላይነት የመሩት ክቡር አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ እንዳስታወቁት ከአምስት ዓመት ጥልቅ ጥናት በኋላ ለውይይት የቀረበው የመጨረሻ ሰነድ በሥነ መለኮታዊ ምክር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱን ገልጸዋል።  

በቅዱሳት ምስጢራት እና በእምነት መካከል ያለው ግንኙነት የሚያብራራውን ሰነድ በቅድስት መንበር የምዕመናን እምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጉባኤ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ፍራንችስኮ ላዳሪያ በኩል እንዲጸድቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ታኅሳስ 19/2019 ዓ. ም. መፍቀዳቸውን ክቡር አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ ገልጸዋል።

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የሚገኝ ዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ምክር ቤት ይፋ ያደረገውን ሰነድ በማስመልከት ክቡር አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ቅዱሳት ምስጢራት የያዙትን ጠቅላላ ሥነ-መለኮታዊ አቅጣጫ በዝርዝር ለመመልከት መጽሐፍ ቅዱስን፣ ለምዕመናን የሚቀርቡ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን፣ ቅዱሳት ምስጢራትን እና የተለያዩ አህጉራት ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ አስፈላጊ እንደነበር አስረድተው፣ ይህንንም ለማድረግ ረጅም ጊዜ የወሰደባቸው መሆኑን አስረድተዋል። አምስት ምዕራፎች ያሉት ሰነዱ፣ ሐዋርያዊ ተግባራትን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ መንፈሳዊ መመሪያዎችን የያዘ መሆኑ ታውቋል። በተለይም የሰነዱ ሁለተኛ ምዕራፍ በቅዱሳት ምስጢራት እና በእምነት መካከል ያለው ግንኙነት የሚያብራራ መሆኑኑ ታውቋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ውስጥ የተቀመጡት ሦስት መሠረታዊ ጽንሰ-ሐሳቦች፣ አንደኛ እግዚአብሔር ስጋን ለብሶ ወደ ዓለም በመምጣት የማዳን ኃይሉን የገለጠበትን እና ቅዱሳት ምስጢራትም ይህን የእግዚአብሔርን ስጋ መልበስ እና የማዳን ኃይሉን በግልጽ የሚያስዩ መሆናቸውን፣ በሁለተኛ ጽንሰ-ሃሳቡ ቅዱሳት ምስጢራትም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ የድነት ጸጋን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት በኩል እንዲረዱ ማድረግ ሲሆን፣ በሦስተኛ ጽንሰ-ሃሳብም የክርስትና እምነት ቅዱሳት ምስጢራት በግልጽ የሚታዩበት እና ክርስቲያናዊ እምነት በራሱ የቅዱሳት ምስጢራት ይዘት ያለው መሆኑን የሚያስረዳ መሆኑ ታውቋል። ሰነዱ በሦስተኛ ምዕራፉ ምስጢረ ተክሊልን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ቅዱሳት ምስጢራትን በማብራራት፣ በእምነት እና በቅዱሳት ምስጢራት መካከል ያለውን ግንኙነት በካቶሊካዊ እምነት መሠረት የሚገልጽ መሆኑን አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ አስረድተዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እና በአሁኑ ወቅት ሐዋርያዊ የአስተዳደር ስልጣን ያላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዲሁም ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1980 ዓ. ም. በ2014 ዓ. ም. እና በ2015 ዓ. ም. ቤተሰብን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች መወያየታቸው፣ እንዲሁም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2005 ዓ. ም. በቅዱስ ቁርባን ምስጢራት ላይ ተወያይተው ይፋ ያደረጉት ሰነድ በቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተግባር ውስጥ የሚታየው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ፣ እንደዚሁም የቤተክርስቲያንን እምነት በትክክል ሳያገናዝብ የሚፈጸም የጋብቻ ምስጢርም መልካም ውጤት ያላመጣ መሆኑን አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ ገልጸዋል። እነዚህን እንቅፋቶችን ማለፍ እንዲቻል የሚያግዝ ሕገ ቀኖናዊ ሥነ-መለኮትን በቅድሚያ መመልከታቸውን የግለጹት አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ ለጋብቻ ሥነ ሥርዓት የሚሰጥ ክብር እና ቅድስናውም የሚገለጸው ሕገ ቀኖናዊ የሥነ-መለኮትን ደንብ ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

በእምነት ላይ ያልተመሰረተ ጋብቻ ሕጋዊነቱን አደጋ ላይ የሚጥለው ለምንድር ነው ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ የሰጡት አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ፣ በዘፍጥረት 2:24 ላይ “ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” የሚለውን ተፈጥሮአዊ ሕግን በመጥቀስ እንዳብራሩት ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተፈጥሮ ሕግ ወደ ቅዱሳት ምስጢር ከፍ እንዳደረገው አስረድተው፣ ለቤተክርስቲያንም ቢሆን ይህ ተፈጥሮአዊ የጋብቻ ሕግ መንፈሳዊ ይዘትን ተጎናጽፎ ወደ ቅዱሳት ምስጢራት ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስን 16ኛ ሐዋርያዊ አስተምህሮ መሠረት፣ በእምነት መታገዝ የጋብቻ ሕይወትን ጨምሮ በእያንዳንዱ ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን እውነታ የሚያገናዝብ መሆኑን አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ አስረድተዋል። የጥምቀት ጸጋን የተቀበሉ ነገር ግን ክርስቲያናዊ እምነት የሚጎላቸው ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት አባ ጋቢኖ፣ የጥምቀት ጸጋን ተቀብለው ነገር ግን ክርስቲያናዊ እምነታቸውን ባጡት ሰዎች መካከል ተፈጥሮአዊ የጋብቻ ሕግ በተግባር የማይውል መሆኑን ገልጸው እውነተኛ የጋብቻ ሕይወት አለመሆኑን አስረድተዋል።          

በሰነዱ ውስጥ የክርስቲያናዊ ጋብቻ ሕይወት ትርጉም ለማብራራት ጥረት ተደርጓል ያሉት አባ ጋቢኖ፣ በምስጢረ ተክሊል ሥነ ሥርዓት ላይ ካህናት በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በመመራት፣ ሁለቱ ተጋቢዎች፣ ከሁሉ አስቀድሞ በክርስቲያናዊ እምነት በመታገዝ፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1601 ላይ እንደተገለጸው፣ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በመዋዕለ-ሕይወታቸው በአንድነት ለመኖር የሚያደረጉት ስምምነት የጋብቻ ቃል ኪዳን ይባላል። የጋብቻ ባሕርይ እንደሚያስረዳው ጋብቻ የተደነገገው ለባል እና ሚስት ደህንነት ልጆችን ለመውለድ እና እነርሱን ለማስተማር ጭምር ነው። ይህ በተጠመቁ ሰዎች መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን በጌታ ክርስቶስ ወደ ምስጢር ደረጃ ከፍ እንዲል ተደርጓል ማለቱን አስታውሰዋል።

የምስጢረ ተክሊል ትምህርትን በማዳረስ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ካህናት እና ረዳቶቻቸው በጋብቻ ሕይወት ለመኖር የወደዱትን ለማገዝ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ አገልግሎት ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ነግር ቢኖር በጋብቻ ሕይወት አብረው ለመኖር የቆረጡ ሁለቱ ተጋቢዎች ከሁሉ አስቀድሞ በእምነታቸው እንዲያድጉ ማገዝ ቀጥለውም የምስጢረ ተክሊል ትክክለኛ ትርጉም እንዲያውቁ ማገዝ መሆኑን አባ ጋቢኖ አስረድተዋል። ለባለ ትዳሮች መጸለይ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አባ ጋቢኖ፣ የዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ምክር ቤት፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምስጢረ ተክሊል አስተምህሮን በሚል ርዕሥ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1977 ዓ. ም. ባወጣው ሰነድ እንዳስረዳው፣ የእምነት እጥረት፣ በተለይም የመዳን ጸጋን ለማግኘት ያለው ፍላጎት ከቀነሰ ፣ የቅዱሳት ምስጢራት እውነተኛነትን ያጎድፋል ማለቱ አስታሰው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከረጅም ጊዜ ውይይት በኋላ ቤተሰብን በማስመልከት ባቀረቡት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደገለጹት “ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ ሁለት ጓደኛሞች የጋብቻን ምስጢር በሚገባ እንዲያውቁ በማለት ከቤተክርስቲያን አባቶች በኩል የሚሰጠውን የትምህርት እገዛ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነው ካልተገኙ ምስጢረ ተክሊልን አለመስጠቱ ይመረጣል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ሰነዱ በቤተክርስቲያን ምስጢራት ውስጥ የሚያመጣቸው ዕድገቶች ምን እንደሆኑ ያስረዱት፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የሚገኝ ዓለም አቀፍ ሥነ-መለኮታዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ጋቢኖ ኡሪባሪ፣ የቤተክርስቲያን ምስጢራት በሙሉ የወንጌል ተልዕኮ ባሕርይ እንዳላቸው ገልጸው፣ ቅዱሳት ምስጢራት የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነች ቤተክርስቲያን ጥንካሬን እንድታገኝ እና የትንሳኤውን ክብር ለመመስከር የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ለምዕመናን የሚሰጥ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው በቅዱሳት ምስጢራት አማካይነት የሚሰጥ የእግዚአብሔር የድነት ጸጋ መቋረጥ የለበትም ብለዋል። በጥምቀት ጸጋ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ቀጣይነት ያለው መሆኑን አስረድተው፣ የሕጻናትን የምስጢረ ጥምቀት ጸጋን በተመለከተ ወላጅ ቤተሰብ እና ጎልማሶች ሁል ጊዜ ከሕጻናት ጎን ሆነው የእምነት ብርታትን መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 March 2020, 16:44