ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአካል ጉዳተኛው ወጣት ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአካል ጉዳተኛው ወጣት ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፣  

አቡነ አይቫን፣ “እግዚአብሔር ቅዱስ አድርጎ ከፈጠራት ነፍስ የተለየች ሌላ የለችም”።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አይቫን ጀርኮቪች፣ በጄኔቭ ለ43ኛ ጊዜ በተካሄደው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ እግዚአብሔር ቅዱስ አድርጎ ከፈጠራት ነፍስ የተለየች ሌላ የለችም ማለታቸው ታውቋል። ጉባኤው ሰብዓዊ መብቶችን አስመልክቶ ያካሄደው ጉባኤ፣ ለአካል ጉዳተኞች ሊደረግ በሚገባው ጥበቃ እና የአገልግሎት ተሻሽሎ ላይ መወያየቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጀርኮቪች በንግግራቸው እንዳስታወቁት፣ እግዚአብሔር በአምሳሉ ውብ አድርጎ ከፈጠራት አንዲት ነፍስ በላይ ፣ በጥራትም ሆነ በትርጉም የተለየች ሌላ ነፍስ የለችም ብለዋል። ከሰው ልጅ ምን ጊዜም ቢሆን ሊሻር የማይችል፣ አካል ጉዳተኞች ለማኅበረሰቡ ሊያበረክቱ የሚችሉት ከፍተኛ አስተውጽዖ እንዳላቸው ቅድስት መንበር ሁል ጊዜ ስትመሰክር መቆየቷን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጀርኮቪች ገልጸዋል። የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብት ማስከበርን አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተናገሩትን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀርኮቪች፣ የእነዚህን ሰዎች ሰብዓዊ መብት በማስከበር ሂደት የማይናቅ እድገት የተመዘገበ ቢሆንም በሕይወታቸውን በተመለከተ አፍራሽ አመለካከቶች አሁንም ማህበራዊ መሰናክሎች ሆነው እንደቀጠሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀርኮቪች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በማስታወስ አክለው እንደተናገሩት ይህ አመለካከትም የሕይወትን ውበት ከመመልከት ይልቅ በጥቅም እና በራስን በማምለክ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተው፣ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አካል ጉዳተኞችን አሳንሰው የሚመለከቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥቂቶች አይደሉም ብለው ፣ ይህም አካል ጉዳተኞች ያካበቱትን በርካታ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ብልጽግና ካለመገንዘብ የተነሳ ነው ብለዋል።

የሥነ ሕይወት የሕክምና ዘርፍ ለሰው ልጅ አገልግሎት ይሁን፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አይቫን ጀርኮቪች፣ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን አስመልክተው ባሰሙት ንግግር፣ ሥነ ጥበብን፣ ባሕልን እና ታሪክን ያገናዘበ የሥነ ሕይወት የሕክምና ዘርፍ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ቅድሚያን በመስጠት የሰውን ልጅ የሚያገለግል እንጂ ትርፍን ለማካበት የቆመ መሆን የለበትም ብለዋል። ይህን አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ያቀረቡትን አስተምህሮ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አይቫን ጀርኮቪች፣ ለሰው ልጅ ለሚሰጥ ክብር ታማኝነትን በመግለጽ፣ በጤና ዘርፍ የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት ከእናት ማሕጸን ጀምሮ እስከ ተፈጥሮአዊ ሞት ድረስ መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2016 ዓ. ም. በጣሊያን የሥነ ሕይወት የሕክምና ብሔራዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት “የሥነ ሕይወት የሕክምና ዘርፍ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ፣ ለሰው ልጅ ጥቅም ሊውሉ የሚያስፈልጉ ምክንያታዊ የጥናት ውጤቶችን፣ ሳይንሳዊ የሥነ ተፈጥሮ ቴክኖሎጂዎች እና መድኃኒቶች እጠቃቀም እና ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ ነው” ማለታቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ ፈጣን ለውጥ በማሳየት ላይ የሚገኙ የሥነ ሕይወት ቴክኖሎጂዎች፣ መድኃኒቶች እና የሕክምና ዘርፎች የሰውን ልጅ ለማገልገል እንጂ በግል ጥቅም እና ትርፍ ላይ ያተኮሩ መሆን የለባቸውም ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ሕጎች በቂ አይደሉም ፤ የአስተሳሰብ ለውጥም እንዲደረግ ያስፈልጋል፣

የዘመናችን አሳሳቢ ጉዳይ ይህ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አይቫን ጀርኮቪች፣ በሂደት ላይ የሚገኝ ዘመናዊው የ“ቅድመ ወሊድ የዘር ፍተሻ” ጥናት፣ ከባድ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕጻናት “ፈጽሞ መወለድ የለባቸውም” የሚለውን መልዕክት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፣ የዚህ ጥናት መጨረሻው ጽንስን ማስወረድ ወደሚለው ውሳኔ ያመራል ብለው፣ ቅድስት መንበር በሕክምና ድጋፍ ነፍስ መግደልን በጽኑ የምትቃወም መሆኑን ገልጸዋል። እግዚአብሔር በአምሳሉ ከፈጠራት አንዲት ነፍስ በስተቀር ፣ በጥራትም ሆነ የበለጠ ትርጉም በመስጠት የተለየች ሌላ ነፍስ የለችም ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አይቫን ጀርኮቪች፣ በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት “የአካል ጉዳተኞችን ማሕበራዊ ሕይወት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሕጎችን ማጽደቅ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በማኅበረሰብ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥን ማምጣት ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 March 2020, 16:38