ፈልግ

ሰው ሠራሽ አዕምሮ፣ ሰው ሠራሽ አዕምሮ፣  

ሰው ሠራሽ አዕምሮ ስነ ምግባርን የተከተለ መሆን አለበት ተባለ።

በቫቲካን፣ የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፣ ዛሬ የካቲት 18/2012 ዓ. ም. የዘመናችንን የቴክኖሎጂ እድገት የሚያጠና ጉባኤ መካሄዱ ታውቋል። ጳጳሳዊ አካዳሚው ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተለያዩ ምሁራን፣ የሳይንስ ተመራማሪዎች እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች መካፈላቸው ታውቋል። በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የተለያዩ የምርምር ተቋማት መሪዎች በዘርፉ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሰነድ እንደሚፈርሙ ይጠበቃል ተብሏል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጉባኤው ተካፋዮች በጋራ ሆነው የሚወስዱት ውሳኔ፣ በሕክምና ፣ በኤኮኖሚ እና በማሕበራዊ ዘርፎች እንደሚወሰዱ ሌሎች ውሳኔውች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸው ታውቋል። የተለያዩ የቴክንሎጂ ውጤቶች የሚያመጡት ውጤቶች ለሰው ልጅ እድገት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን እና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ መሆኑን የጉባኤው ተካፋዮች አስምረውበታል። ከሁሉ በላይ የሰው ልጅ ሕይወትን በቀዳሚነት የተመለከተው ጉባኤ በሁለቱ መካከል፣ በሰው ልጅ እና በስልተ-ቀመር በቴክኖሎጂ መካከል ያለውን ግንኙነት ለይቶ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ወደ አወሳሳቢ ደርጃ ላይ መድረሱ ሃላፊነትን ለመቀበል ችግር መፍጠሩን የጉባኤው ተካፋዮች አስታውቀዋል። ዛሬ የካቲት 18/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተገኙት፣ በቅድስት መንበር የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼሶ ፓሊያ፣ በሰው እና ሰው ሰራሽ አዕምሮ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ፣ ሥነ ምግባርን ፣ ሕግን እና ጤናን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቀጣይነት ያለው ጥረት፣

ከዛሬ የካቲት 18/2012 ዓ. ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የተለያዩ ምሁራን፣ የሳይንስ ጠበብት እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በጉባኤያቸው ማጠቃለያ ላይ ወደ ፊት አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን፣ “የሥነ ምግባር ጥሪ” የተሰኘ የጋራ ስምምነት ሰነድ እንደሚያጸድቁ ይጠበቃል ተብሏል። የጋራ ሰነዱ ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።

አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት፣

በእንፋሎት ፣ በኤሌክትሪክ እና በራሱ ኃይል ከሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የኢንዱስትሪ አብዮት የሆነው የስልተ-ቀመር ቴክኖሎጂዎች የሰውን ልጅ የሥራ እንቅስቃሴዎች ለመተካት ወይም ለመቆጣጠር ችሎታ አላቸው ተብሏል። በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ውስጥ መምህር የሆኑት ክቡር አባ ፓውሎ ቤናንቲ እንደገለጹት የስልተ-ቀመር ቴክኖሎጂዎች በሕክማና ዘርፍም የትኛው የአካል ክፍል ለየትኛው ሕመምተኛ ሊሆን እንደሚችል የመለየት አቅም እንዳላቸው ገልጸው፣ የባንክ አገልግሎቶችን ጨምሮ በሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎቶች በሚሰጡበት ቦታዎች ውጤታማ ሥራን ማከናወን የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሮች በኮምፒዩተር የሚወገዱ አይደሉም፣

ኮምፒዩተርን በመጠቀም አንዳንድ የስታቲስቲክስ፣ የግራፎች እና የስሌት ጥያቄዎችን ማቃለል ቢቻልም ይህ ማለት ደግሞ ኮምፒዩተር ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት እንዳማይችሉ የገለጹት መምህር አባ ቤናንቲ፣ አንድን ችግር ለማቃለል ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ የሰው ልጅ ምርጫን ከማድረግ በፊት ጥልቅ እና መሠረታዊ መንገድ ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል። በጣሊያን፣ ፒሳ ከተማ የቅድስት ሐና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የባዮ ኢንጂኔሪ ተቋም መምህር የሆኑ ወይዘሮ ማርያ ኪያራ በበኩላቸው በሕክምናው ዘርፍም ያየን እንደሆነ አርቴፊሻል አዕምሮ በሕክምና ዘርፍ ለሕክምና ባለሞያ ድጋፍ ከመሆን ባሻገር ሕኪምን ተከቶ ለመሥራት የሚያስችል ቁመና የለውም ብለዋል።

የስልተ-ቀመር የሥነ ምግባር፣

በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ውስጥ መምህር የሆኑት ክቡር አባ ፓውሎ ቤናንቲ በገለጻቸው የሰው ሠራሽ አዕምሮ ቀመሮችን ብቻ የሚከተሉ ሳይሆን ስነ ምግባርንም የተከተለ መሆን አለበት ብለው በዘርፉ ተሰማርተው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያመርቱ ድርጅቶች ሥነ ምግባርን የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል። በቅድስት መንበር የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼሶ ፓሊያ በበኩላቸው በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ምርት የተሰማሩ፣ አይ ቢ ኤም እና ማይክሮ ሶፍት የመሳሰሉ ትላልቅ የዓለማችን ኩባንያዎች በተመሳሳይ የውይይት እና የጥናት መድረኮች ላይ መገኘት አለባቸው ብለዋል። የጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼሶ ፓሊያ አክለውም በቴክኖሎጂ ምርቶች የተሰማሩት ድርጅቶች ከሌሎች ተቋማት ጋር መተባበር አለባቸው ብለው ከእነዚህም ተቋማት መካከል አንዳንዶቹ የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ የትምህርት እና የሐይማኖት ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 February 2020, 18:19