ፈልግ

የአረጋዊያን ምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ፣ የአረጋዊያን ምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጉባኤ፣ 

አረጋዊያን የማሕበረሰብ ውድ ሃብት መሆናቸው ተነገረ።

በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጥር 19/2012 ዓ. ም. ባዘጋጀው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ፣ አረጋዊያን የማሕበረሰብ የረጅም ዓመታት ውድ ሃብት መሆናቸውን አስታወቀ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያነት አገልግሎታቸውን በጀመሩበት ወቅት አረጋዊያን እምነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ሰፊ ሚናን እንደሚጫወቱ መግለጻቸውን ያስታወሰው ዓለም አቀፍ ጉባኤ አረጋዊያን ከወጣት ትውልድ ጋር በሚያደርጉት ዘላቂ ውይይት እና ባሕልን ጠብቀው በማቆየት ለማሕበርሰብ ከፍተኛ አስተዋጾን የሚያበረክቱ መሆኑ ታውቋል። አረጋዊያንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍሬዋን ከምትሰጥ ዛፍ ጋር ያመሳሰሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እያንዳንዱ ወቅት የእግዚአብሔር በረከት መሆኑን፣ አስፈላጊነቱንም ተገንዝበው ምስክርነትን የሚሰጡ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የአረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ጉባኤን ያዘጋጀው፣ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የጉባኤው ርዕሥም “አረጋዊያን የማሕበረሰብ ውድ ሃብት ናቸው” ማለታቸው ታውቋል። ከጥር 19 ቀን ጀምሮ ለአራት ቀናት በቆየው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ፣ በ60 አገሮች ውስጥ ከሚገኙ የምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያዎች የመጡ፣ 550 አባላት የተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጉባኤው ርዕሦች፣

ጉባኤው በአራት ቀናት ውስጥ ውይይት ካደረገባቸው ርዕሦች መካከል አንዱ አረጋዊያንን ወደ ጎን እያደረገ በመጣው የዘመናችን ባሕል ላይ ሲሆን የጉባኤው ተካፋዮች ርዕሡን ከየአገራቸው ማሕበራዊ እና ባሕላዊ የእድገት ደረጃ ጋር በማዛመድ ቤተክርስቲያን የተጠራችበትን የምሕረት ጎዳና በመከተል ለአረጋዊያን የፍቅር ሐዋርያዊ አገልግሎት መደረግ እንደሚገባ መወያየታቸው ታውቋል። በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ አረጋዊያን ትልቅ ሥፍራ እንደሚሰጣቸው ቤተክርስቲያን በሚገባ እንደምታውቅ እና ለዚህ ዓላማ መጠራቷን የገለጹት የጉባኤው ተካፋዮች በተለይም ረዳት በማጣት የብቸኝነት ሕይወት ለሚኖሩት አረጋዊያን ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን የምታቀርብ መሆኗንም አስታውቀዋል። ጉባኤው በተጨማሪም በኑሮ መደላደል ምክንያት የሰዎች ዕድሜ መራዘሙን በመረዳት የሚሰጣቸው እንክብካቤ እና አገልግሎት ማደግ እንዳለበት አስታውቀዋል።

ለአረጋዊያን የሚሰጥ የወንጌል ምስክርነት፣

በጉባኤው ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች፣ ዕድሜያቸው 65 እና ከዛም በላይ የሚሆናቸው የዓለማችን ሰዎች ቁጥር 703 ሚሊዮን መሆኑን በጎርግሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ሪፖርት ዋቢ በማድረግ አስታውቀዋል። ሪፖርቱ በማከልም በሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ይህ ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምር እና በጎርጎሮሳዊያኑ 2050 ዓ. ም. ወደ 1.5 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል አስታውቋል። በመሆኑም ለአረጋዊያን የሚሰጥ የወንጌል አገልግሎትም የሚያድግ መሆኑን በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወንጌል አገልግሎት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሼልዞ አስታውቀዋል።

አረጋዊያን በቁምስና ውስጥ የሚያበረክቱት አስተዋጾ፣

አረጋዊያን በየቁምስናዎቻቸው የሚያደርጉት ተሳትፎ ለቁምስናው ትልቅ ሃብት መሆኑን ያስታወሱት ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሼልዞ ወደ ቁምስናቸው የሚመጡት አዛውንት ምናልባትም የሚንከባከባቸው የሌላቸው፣ ነገር ግን ያላቸው የክርስቲያናዊ ሕይወት ከሌሎች ጋር ሊጋሩ እና በጎ አገልግሎታቸውን ለማበርከት የሚመጡ መሆናቸውን በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወንጌል አገልግሎት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ክቡር አቶ ቪቶሪዮ ሼልዞ አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

03 February 2020, 16:17