ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ 

“በአውሮፓ ውስጥ የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተግባር ሰብዓዊ ክብር ማስጠበቅ ነው”።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት የሚከታተል ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ቤተክርስቲያን በአውሮፓ ውስጥ በምታከናቸው ሐዋርያዊ ተግባራት መካከል ቅድሚያን የሰጠችው ሰብዓዊ ክብር መሆኑን አስታወቁ። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር ይህን ያስታወቁት፣ የፈረንሳይ ሰሜን ምሥራቅ ከተማ በሆነችው በስትራስቦርግ ላይ፣ ቅድስት መንበር በአውሮፓ መንግሥታት ምክር ቤት ውስጥ አባል የሆነችበት 50ኛ ዓመት ለማስታወስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በንግግራቸው እንዳብራሩት፣ የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር “እውነተኛ የማዕዘን ድንጋይ ነው ካሉ በኋላ፣ ድንጋጌው በባሕሎች መካከል ያለውን ልዩነት ባገናዘቡ የጋራ እሴቶች ላይ በመመርኮዝ አውሮፓ ማንነቱን እንዲያውቅ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮአል” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቅድስት መንበር የአውሮፓ መንግሥታት ምክር ቤት አባል የሆነችበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ እና በአውሮፓ አገሮች የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ስምምነት የተፈረመበትን 70ኛ ዓመት ለማስታወስ ተብሎ በፈረንሳይ፣ የስትራስቦርግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የሥነ መለኮት ምርምር ማዕከል ባለፉት ቀናት ውስጥ በተደረገው ጉባኤ ላይ፣ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት የሚከታተል ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

ቤተክርስቲያን ለአውሮፓ ያላት አመለካከት፣

“ቤተክርስቲያን ለአውሮፓ ያላት አመለካከት” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው እና በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ስምምነት የተፈረመበትን 70ኛ ዓመት ለማስታወስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በአውሮፓ ወስጥ የሚገኙ አገራት በሙሉ ተመሳሳይ አቋም እንደሌላቸው አስታውሰው፣ ለአውሮፓ ያላቸውን አመለካከት ሲገልጹ፣ “አውሮፓ ምን ጊዜም ቢሆን ክርስቲያናዊ መሠረቷን መዘንጋት የለበትም” ብለው የአውሮፓ ክርስቲያናዊ መሠረቱ የሚያንጸባርቀው የካቶሊክ ወይም የክርስቲያን ማሕበረሰብ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ሰው በጎ ፈቃድን ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2014 ዓ. ም. በተካሄደው የአውሮፓ ምክር ቤት ጉባኤ የተናገሩትን የቅድስት መንበር አቋም በመጥቀስ ንግግር ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ በሚቀርቡ አስተያየቶች ላይ የአውሮፓ ተቋማት አቋም ከቤተክርስቲያን አቋም ይለያል ብለው፣ ሰብዓዊ መብቶች በሥነ መለኮታዊ እና ስነ-ልቦናዊ እይታ ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ግንዛቤን የማስጨበጥ አስፈላጊነት፣

በአውሮፓ ውስጥ ሊከናወን የሚገባው ሌላው መሠረታዊ ተግባር፣ ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሆኑን ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮ፣ ሂደቱን ጠብቆ ወደ ቋሚ ልማት የሚደርስ መሆኑን አስረድተው ለዚህም ግንዛቤን ማስጨበጥ ወይም ትምህርትን ማዳረስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ማስተማር ሲባል ሌላ ሳይሆን  አንድን ሕጻን ከሕጻንነቱ ጀምሮ ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት እና በመምራት ወደ ሙሉ እውቀት እስኪደርስ ማገዝ ነው ብለዋል።

ስደትን የተመለክቱ አዳዲስ አቅጣጫዎች፣

ስደትን በተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ያካፈሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር፣ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የሚያደርጉት ጉዞ ለራሳቸውም ሆነ ለሚሄዱበት አገር ሕዝብ ጥቅም አለው ብለው፣ ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞች በሚኖሩበት ባዕድ አገር ራሳቸውን አግልለው ከመኖር ይልቅ ከማሕበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነትን ፈጥረው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል ብለውል። ስደት አስክፊ የሚሆነው ሕጋዊ ሳይሆን ሲቀር ነው ያሉት ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ጋላገር፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት የስደት ጉዞ ሕጋዊ ሳይሆን ሲቀር ለተለያዩ አደጋዎች ይጋለጣሉ ብለው ከአደጋዎቹ መካከል አንዱ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋልጠው ለብዝበዛ እና ለጥቃት መዳረግ ነው ብለው ይህን ለማስቀረት ስደትን የሚመለክቱ አዳዲስ አቅጣጫዎችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያላቸውን አስተያየት ለጉባኤው አካፍለዋል።

ባሕልን እና ውይይትን ማሳደግ፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር በንግግራቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት አህመድ አል ጣይብ መካከል የተፈረመውን የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ አስታውሰው፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ባሕሎች የሰው ልጆች እውነተኛ ሃብት ናቸው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፣ ባሕሎች ከሚያጋጥማቸው እንቅፋቶች ከሚደርስባቸው የማበላለጥ ዝንባሌ የተጠበቁ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የክርስቲያን ሥነ ምግባራዊ ሚና፣

የሰዎች ሥነ ምግባር በአዳዲስ ሕጎች እየተገደበ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጋላገር ይህ ከሚሆን ሕግ በሥነ ምግባር የታገዘ መሆን አለበት በማለት አስተያየታቸውን አካፍለዋል። ለዚህም ክርስቲያን ማሕበረሰብ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በማከልም የሰዎች ሥነ ምግባር መሠረትን የሚያገኘው በሕግ አውጭው ፈቃድ እና ፍላጎት ላይ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ሕጎችን የተከተለ መሆን አለበት ብለዋል።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት የሚከታተል ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት የእያንዳንዱ የፖለቲካ ስልጣን ሃላፊነት ፣ በእግዚአብሔር እና በሰዎች ፊት ለሚገቡት ቃል ኪዳኖች እና ድርጊቶች፣ ሕግ አውጭው ክፍል ለሚያወጣቸው ድንጋጌዎች እና ለሚያደርጋቸው ውሳኔዎች መሠረታዊ መርህ መሆን አለበት ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 January 2020, 16:50