ፈልግ

ካርዲናል ታርክሰን፣ ሰዎች በበሽታ ምክንያት ከማህበረሰቡ መገለል እንደሌለባቸው አሳሰቡ።

በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” “የሕጻኑ ኢየሱስ ሆስፒታል” በመባል በሚታወቅ የሕክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ሕጻናት ልዩ በዓል መዘጋጀቱ ታውቋል። በበዓሉ ላይ የተገኙት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በሥፍራው ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ ሰዎች በበሽታ ምክንያት ከማህበረሰቡ መገለል እንደሌለባቸው አሳስበዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ ሕክምናቸውን በመከታተል ለይ ለሚገኙት ሕጻናት የቀረቡ አዝናኝ እና አስቂኝ ትርዒቶችን የተከታተሉት የሆስፒታሉ ፕሬዚደንት ወይዘሮ ማሪየላ ኤንኮ፣ ሕሙማንን ማዝናናት እና ማስደሰት ከእንክብካቤ መንገዶች አንዱ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሆስፒታሉ ተገኝተው ለታካሚ ሕጻናት ትርዒታቸውን ያቀረቡት የሮኒ ሮለር ሰርከስ ቡድን፣ ሕጻናቱ በሚገኙበት ክፍል እየተገኙ አስቂኝ እና አዝናኝ ጨዋታዎችን ማቅረባቸው ታውቋል። በሆስፒታሉ የተከበረውን በዓል በጋራ ላስተባበሩት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን እና የሆስፒታሉ ፕሬዚደንት ለሆኑት ለወይዘሮ ማሪየላ ኤንኮ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ሕጻናት ስጦታ ማበርከታቸው ታውቋል።

ደስታን እና ሳቅን ማድረስ፣

በሽታ በሕጻናት መካከል እንዲሁም በአዋቂዎችም መካከል መገለልን እያስከተለ ይገኛል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በሕክምና ላይ ለሚገኙት ህሙማን እነዚህን የመሳሰሉ አዝናኝ እና አስደሳች ዝግጅቶችን ማቅረብ በሕሙማን መካከል የሚታየውን የመገለል ስሜት በማስወገድ መቀራረብን ከማምጣት በተጨማሪ ደስታን በማጎናጸፍ፣ ህመምን በመቀነስ በመካከላቸው የደስታ ስሜትን ያሳድጋል ብለዋል።

ብርታትን የሚሰጡ ትርዒቶች፣

የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታሉ ፕሬዚደንት፣ ወይዘሮ ማሪየላ ኤንኮ በበኩላቸው፣ በሕመም ላይ ከሚገኙት ታካሚዎች ጋር የሚደረግ የግንኙነት መድረክ እና የደስታ እና የመዝናኛ ቀን በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ለታካሚውም የውስጥ ደስታን ለመፍጠር እገዛን የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። በተለይም ሕክማናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት ሕጻናት የተለያዩ አዝናኝ ጨዋታቸውን ማቅረብ፣ ሕመማቸውን እንዲዘነጉ እና ሃሳባቸውን በጨዋታው ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አስገራሚ እና የማይቻል መስለው የሚታዩ ጨዋታዎችን ለሕጻናት ማሳየት፣ ብርታትን በመስጠት የማይቃለል መስሎ የሚታየውን ችግር ለማለፍ ሃይልን ይጨምራል ብለዋል።

ትህትናን የሚያሳዩ የሥነ ጥበብ ባለሞያዎች፣

በሆስፒታሉ ተገኝተው አዝናኝ እና አስደሳች የጥበብ ሥራቸውን ያቀረቡትን አርቲስቶች ያመሰገኑት የሆስፒታሉ ፕሬዚደንት፣ ወይዘሮ ማሪየላ ኤንኮ፣ ለሕጻናቱ ላሳዩት ጥንቃቄ እና ትህትና አድናቆትን ሰጥተው፣ ወጣቶቹ ለሌሎች ደስታቸውን በማከፈል፣ ሕሙማን መልካም ጊዜን እንዲያሳልፉ በማድረግ ትልቅ ድጋፍ ያበረክታሉ ብለዋል።

በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነትን ማስወገድ፣

በልባቸው ውስጥ በደስታ የተሞሉ ሰዎችን ማግኘት ሕጻናትን እንደሚያስደስት የተናገሩት ወይዘሮ ማሪየላ ኤንኮ፣ ከፈውስ አግልግሎት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ በዕለቱ የተዘጋጀው የመዝናኛ ዝግጅት በመጭው የካቲት 3/2012 ዓ. ም. ተከብሮ በሚውለው የዓለም ሕሙማን ቀን ዝግጅቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በንግግራቸው እንደገለጹት፣ በበሽታ ምክንያት በሰዎች መካከል የሚታየው መገለል ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በዕለቱ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እና በተለያዩ ትርዒቶች አማካይነት፣ በሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ሳይዘነጉ ዘወትር የሚታወሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
22 January 2020, 14:36