ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገና ሰሞን ስብከት ሲከታተሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገና ሰሞን ስብከት ሲከታተሉ፣ 

“የማርያም የምስጋና መዝሙር የቤተክርስቲያንን ጸሎት ያግዛል”።

በቫቲካን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የሥራ ተባባሪያቸው ለሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት እና ቄሳውስት ስብከት በማቅረብ የሚታወቁት ፍራንችስካዊው ካህን ክቡር አባ ራይኔሮ ካንታላሜሳ፣ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር የሚከተሉት ካቶሊካዊ ምዕመናን በጀመሩት የስብከተ ገና ሁለተኛ ሳምንት ላይ ስብከታቸው አቅርበዋል። ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው፣ ረደንቶሪስ ማተር ጸሎት ቤት ተገኝተው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ለሐዋርያዊ ሥራ ተባባሪዎቻቸው ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ “የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና መዝሙር ቤተክርስቲያን ለምታቀርበው ጸሎት ድጋፍ ይሰጣል” ማለታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘጋቢ አመደዎ ሎሞናኮ የላከልን ዘገባ አመልክቷል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በእግዚአብሔር እና በዓለም ላይ ያለን አዲስ አመለካከት፣

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና መዝሙር በእግዚአብሔር እና በምንኖርበት ዓለም ላይ ባለን አመለካከት ላይ አዲስ ግንዛቤን ያስጨብጠናል ያሉት ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ፣ እግዚአብሔር በክንዱ ብርታት በነገር ሁሉ ላይ ቅድስናውን በመግለጽ ዝቅተኛይቱ ማርያምን ወሰን ወደሌለው መንግሥቱ ከፍ በማድረግ የሃያላን፣ የነገሥታት ግዛት እና ስልጣን እንዲወድቅ ያደረገበት፣ ትሑታንን በኃይሉ ከፍ ያደረገበት፣ የተራቡትም በበጎ ነገር እንዲጠግቡ ያደረገበት፣ ሀብታሞች ግን ባዶአቸውን የተሰደዱበት መሆኑን ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ትሁታንን እና ዝቅተኞችን ከፍ የሚያደርገው አመጽን በመቀስቀስ ወይም ሰዎችን በማነሳሳት ሳይሆን እንደ ባለፀጋው ሰው ምሳሌ መሠረት ለሀብታሞች እና ለኃያላን ማስጠንቀቂያን በመስጠት መሆኑን ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ ገልጸዋል።

ገጽታው ከሚታየው እውኔታ የተለየ ነው፣

ከእግዚአብሔር ዘንድ ለተሰጠን ቃል ምስጋናቸውን ያቀረቡት ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ፣ በዓለማችን ውስጥ አሁን የሚታየው እውነታ ቤተክርስቲያን በተለየ ገጽታ የምትረዳው ከእግዚአብሔር ዘንድ በምታገኘው ቅዱስ ቃል በመታገዝ መሆኑን አስረድተው ቃሉን ሳትሰለች ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ፣ ለሌሎችም መመስከር እንዳለባት አሳስበው ዘለዓለማዊነቱን የሚያረጋግጠው በሰዎች አማካይነት መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም “ሰማይ እና ምድር ሲያልፍ በመጨረሻ ጸንቶ የሚቆየው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው” ብለዋል።

ማርያም የምስጋና መዝሙር መምህርት ናት፣

የዚህ ዓለም ሃብት እና ስልጣን ከንቱ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ገሃድ ያወጣችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ያሉት ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ፣ በማርያም የምስጋና መዝሙር የታወጀው የሃያላን እና የነገሥታት ውድቀት፣ የምስጋና መዝሙሯን በሚደግሙት እና ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በሚያቀርቡት ሰዎች አማካይነት እንደ ማስጠንቀቂያ ይነገራቸዋል ብለው እግዚአብሔር የሃያላንን እና የነገሥታትን ተግባር ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ሐሳብ ጭምር ከንቱ ያደርጋል ብለዋል።

እግዚአብሔር ሃያላንን በማራቅ ትሑታንን፣ ዝቅተኞችን እና የእርሱን እገዛ የሚሹትን በመልካም ነገር ሁሉ የሚያጠግብ መሆኑን የተናገሩት ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጣፋጭ እናታዊ ምክሯ እግዚአብሔርን እንድንመስል፣ የእርሷንም ምርጫ እንድንከተል ታሳስበናለች ብለዋል።       

የማርያም የምስጋና መዝሙር የቅዱስ ወንጌል ጥበብ የተሞላበት ነው በማለት ያስረዱት ክቡር አባ ካንታ ላ ሜሳ፣ የምስጋና መዝሙሯ ዘላቂ ለውጥን የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመዝሙሯ እግዚአብሔርን ከትውልድ እስከ ትውልድ ስታመሰግን የምትኖር መሆኗን ገልጸው ይህም ለቤተክርስቲያን የምስጋና ጸሎት ድጋፍ ይሆናል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 December 2019, 16:07