ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን  

“በእውነት ላይ የተመሠረተ ልግስና” በሚል ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ውይይት መካሄዱ ተገለጸ።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ የሚወያይ አውደ ጥናት ትናንት ህዳር 23/2012 ዓ. ም. መካሄዱን የቫቲካን ዜን አገልግሎት አስታውቋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ሐዋርያዊ መልዕክቱ በውስጡ የያዛቸውን የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች፣ ከእነዚህም መካከል ስነ ምሕዳርን እና የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገትን የተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች እና ያስገኟቸውን ውጤቶች መመልከታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ከአሥር አመት በፊት ሦስተኛውን እና የመጨረሻቸው የሆነውን “በእውነት ላይ የተመሠረተ ልግስና” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። የዚህ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አሥረኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ባወጡት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ የሚወያይ አውደ ጥናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው ማዘጋጀቱ ታውቋል።           

ትናንት ህዳር 23/2012 ዓ. ም. በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ማቅረባቸው ታውቋል። ብጹዕነታቸው በጽሑፋቸው በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ ሰብዓዊ ቤተሰብን ያጋጠመውን የአካባቢ አየር ለውጥ፣ ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮችን፣ ድሃ እና ሀብታም በማለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የኑሮ ልዩነት፣ ለሰው ልጅ ሊሰጥ የሚገባውን ክብር ወደ ጎን በማድረግ ትርፍን ብቻ ለማሳደግ የቆመ የኤኮኖሚ ሥርዓትን እና በሌሎችም ማሕበራዊ ሕይወት ላይ የሚደርሱትን ችግሮች በጽሑፋቸው የተመለከቷቸው ሲሆን እነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች “በእውነት ላይ የተመሠረተ ልግስና” በሚለው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ የተጠቀሱ መሆናቸው ታውቋል።     

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ “የሕዝቦች ልማት” በማለት ይፋ ባደረጉት የቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ውስጥ ስለ ተፈጥሮ ስነ ምሕዳር በስፋት መናገራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ቀጥሎም ይህን ርዕሠ ጉዳይ በማሳደግ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሰዎችን ሕይወት በተመለከተ አስተምህሮአቸው ሰብዓዊ ስነ ምሕዳርን የሚዳስስ ሰፋ ያለ ሃሳብ ማቅረባቸውን አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ፣ የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ የሰዎችን ቤተሰባዊ ሕይወትን እና ሰላምን የሚመለከቱ አስተምህሮችን ማቅረባቸው ይታወሳል። እነዚህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ሐዋርያዊ አስተምህሮች በቤተክርስቲያ ማሕበራዊ አስተምህሮ ውስጥ የተፈጥሮ ሥነ ምሕዳር፣ ሰብዓዊ ሥነ ምሕዳር፣ ማሕበራዊ ሥነ ምሕዳር እና የሰላም ሥነ ምሕዳር የሚሉትን ርዕሦችን የሚያጠቃልል መሆኑን ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ገልጸዋል።  

ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ለአውደ ጥናቱ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር በሰው ሕይወት እና በተፈጥሮ መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖሩ አስረድተው በሰው ሕይወት እና በተፈጥሮ መካከል ያለው ግንኙነት እግዚአብሔር በጥበቡ ለፍጥረታቱ በሙሉ ያለውን ፍቅር የገለጸበት ነው ብለዋል። ሰው ከሚኖርበት አካባቢ ጋር ያለው የጠበቀ ግንኙነት ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ሐዋርያዊ አስተምህሮ መንገድ መክፈቱን የገለጹት ካርዲናል ታርክሰን ይህ አስተምህሮአቸው የሰው ልጅ የሚኖርበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው፣ የቤተሰብን ሕይወት እና ማህበራዊ ሥነ ምግባርንም የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልዕክት ምዕ. 8:22-24 “እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል”? የሚለውን ጥቅስ በማስታወስ ባሰሙት ንግግር በተፈጥሮ እና በሰው ሕይወት መካከል የማይነጣጠል ግንኙነት መኖሩ አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 December 2019, 16:08