ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ጋር፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ጋር፣ 

“የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት በፍቅር፣ በፍላጎት እና በመደማምጥ ሊከናወን ይገባል”።

በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሆነው መመረጣቸውን የቫቲካን ዜና ማሰራጫን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወቃል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ከተጠሩበት አገልግሎት ጀምረው ከዚህ በፊት የነበሩበትን ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ በማስታወስ ኦዜርቫቶረ ሮማኖ ከተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድረገዋል። በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ወቅት እንደገለጹት በወንጌል ምስክርነት የእግዚአብሔርን ቃል በፍቅር እና በፍላጎት ማዳመጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው ይህን በተግባር ለመግለጽ የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ የወንጌል ምስክርነትን አስመልክተው እንደተናገሩት የወንጌል ምስክነት እያንዳንዱ ክርስቲያን የተጠራበት የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን አስረድተው የኢየሱስን ርህራሄ እና ፍቅር በሕይወት ምስክርነት እንዲገልጽ ተጠርቷል ብለዋል። በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እንዲመሩ የተመረጡት የብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት አሁን የደረሰበትን ደረጃ አስታውሰው ይህን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዓለማችን የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ውጤቶችን መጠቀም አስፈላጊነት አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ማክሰኞ ኅዳር 30/2012 ዓ. ም. በፊሊፒን ዋና ከተማ ማኒላ በሚገኘው ቨሪታስ በሚል ስያሜ በሚታወቅ ካቶሊካዊ የማሕበራዊ መገናኛ ተቋም ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ በእስያ አህጉር በሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችን በማሕበራዊ መገናኛ ዘርፍ የሚያገለግል ጽሕፈትይ ቤት መመስረቱን ገልጸዋል። የብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ኦዜርቫቶሬ ሮማኖ ከተባለ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ውይይት       ኅዳር 28/2012 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላጸደቁት ሐዋርያዊ አገልግሎት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድጋፍ መማጸናቸውን ተናግረዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በማከልም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከላቸውን የአገልግሎት አደራ ለመጀመር ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት የመረጧቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስንም አመስግነዋል።  ከዓለም ዙሪያ ደስታቸውን የገለጹት ብዙ መሆናቸውን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው የምስራቅ አገሮች፣ ከእስያ አገሮች መካከልም ከጃፓን እና ካምቦዲያ እንዲሁም ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የደስታ መልዕክት መቀበላቸውን ተናግረው ይህም ምዕመናን ለወንጌል ምስክርነት ያላቸውን ተነሳሽነት ያመለክታል ብለዋል።       

በፊሊፒን ዋና ከተማ ማኒላ የተከፈተውን አዲስ የማሕበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤትን አስመልክተው እንደተናገሩት ጽሕፈት ቤቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰው የወንጌል ምስክርነት የሚጀምረው መንፈሳዊ የማዳመጥ ችሎታን በማሳደግ ነው ብለዋል። ከእኛ የሚጠበቀው የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ እና እርስ በእርስም መደማመጥ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ስናዳምጥም በትዕግስት፣ በፍላጎት እና በጥንቃቄ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ብዙን ጊዜ ሰዎች ሲያወሩ አንዱ ሌላውን በትዕግስት እና በፍቅር ሲያዳምጡ አይታይም ብለው በወንጌል ምስክርነት ማዳመጥ የመጀመሪያው እና አስፈላጊው መንገድ ነው ብለዋል።

የልጅነት ጊዜያቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በንግግራቸው እንደተናገሩት፣ ትምህርተ ክርስቶስን ሲከታተሉ እና የወንጌል መልዕክቶችን በሚሰሙበት ጊዜ በአዕምሮአቸው የሚቀረጸው የነበሩበት ሥፍራ እና ጊዜ ሳይሆን የወንጌል መልካም ዜናን የሚያበስር ሰው የሚያሳየው ልባዊ ፍቅር እና ሌሎችን የማዳመጥ ችሎታ ነው ብለዋል። የእርስ በእርስ መደማመጥ ባሕል እንዲያድግ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ መናገራቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል መልካም ዜና እንድናበስር ወደ ዓለም ዙሪያ ሲያሰማራን በሰዎች መካከል መደማመጥ እንዲኖር ያስፈልጋል ብለዋል።

በወንጌል አገልግሎት እና በማሕበራዊ መገናኛ አገልግሎት ወጣቶችን እና ሴት እህቶቻችንን ማሳተፍ አስፈላጊ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ፣ ወጣቶች የዘመናችንን ዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል የበለጠ ይችሉበታል ብለዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለሚቀርብ የወንጌል አገልግሎት ጠቃሚ ሃሳቦችን በማካፈል ሊረዱን ይችላሉ ብለዋል። ሴት እህቶቻችንም ቢሆኑ በሰዎች መካከል በሚደረግ የእርስ በእርስ ግንኙነት ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርጉበት የተፈጥሮ ስጦታ አላቸው ብለዋል።                       

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሆነው የተመረጡት፣ በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ለቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ለሆነው “ኦዜርቫቶሬ ሮማኖ” የሰጡትን አስተያየት ባጠቃለሉበት ወቅት እንደገለጹት በማኒላ ከተማ ያበረከቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ከከተማው ምዕመናን ጋር ሆነው በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት በመታገዝ አገልግሎቱ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ በፍቅር ያቀረቡት አገልግሎት እንደነበር አስታውሰው በፍቅር እና በፍላጎት የምናከናውናቸው ትናንሽ አገልግሎቶች በምድር ላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋፋት የሚረዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።   

የማኒላው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ወደዚህ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ቦታ የመጡት ከእርሳቸው በፊት ጳጳስዊ ምክር ቤቱን ስያገለግሉ የቆዩትን ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ በመተካት መሆኑ ታውቋል።

12 December 2019, 18:13