ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ 

ለወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አዲስ አስተባባሪ ተመረጡ።

በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ሆነው መመረጣቸውን የቫቲካን ዜና ማሰራጫ አገልግሎት አስታውቋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸደቀው የብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሹመት ይፋ የሆነው ኅዳር 28/2012 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። የማኒላው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ወደዚህ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ቦታ የመጡት ከእርሳቸው በፊት ጳጳስዊ ምክር ቤቱን ስያገለግሉ የቆዩትን ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ በመተካት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ሰኔ 21/1957 በማኒላ ከተማ ውስጥ ከካቶሊካዊ ቤተሰብ መወለዳቸው ሲነገር እናታቸው ከቻይናዊ ቤተሰብ የተወለዱ መሆናቸው ታውቋል። ማዕረገ ክህነታቸውን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1982 የተቀበሉት ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መሠረት ባደረገ የሥነ መለኮት ትምህታቸውን አጠናቅቀው ባቀረቡት የጥናት ጽሑፋቸው የዶክተርነት ማዕረግ ከሰሜን አሜሪካ መቀበላቸው ታውቋል። ቀጥለውም ወደ ሮም መጥተው ባደረጉት የሰባት ዓመታት ቆይታ ውስጥ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን በመቅሰም እውቀታቸውን ያሳደጉ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1997 ዓ. ም. የሥነ መለኮት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት አባል በመሆን አገልግለዋል።

ወደ አገራቸው ፊሊፒን ተመልሰው የኢሙስ ካቴድራል ቆመስ ሆነው ካገለገሉ በኋል በ44 ዓመት ዕድሜያቸው ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እጅ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በጥቅምት ወር 2001 ዓ. ም. የጵጵስና ማዕረግ መቀበላቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በፊሊፒን ውስጥ ባበረከቱት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው በተለይም ለወጣቶች በሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት ዙሪያ ያገለገሉ ሲሆን በፊሊፒን በሚገኝ የኢሙስ ሀገረ ስብከት የመጀመሪያ የሆነውን የእስያ አህጉር ወጣቶች መንፈሳዊ ፌስቲባልን ማዘጋጀታቸው ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 13/2011 ዓ. ም. በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በፊሊፒን የማኒላ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ሆነው መሾማቸው ታውቋል። በዚህ ቦታ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ለ13 ወራት ካበረከቱ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በኅዳር ወር 2012 ዓ. ም. ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እጅ የካርዲናልነት ማዕረግ መቀበላቸው ታውቋል። በሊቀ ጳጳስነት ማዕረግ የማኒላ ከተማ ጳጳስ ሆነው ከማገልገላቸው በተጨማሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የካሪታስ ኢንተርናሲዮናሊስ ወይም በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር ዓለም አቀፍ የቸርነት አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እና የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ለዚህ ሰፊ ሐዋርያዊ አገልግሎት መሾም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኅዳር 9-16/2012 ዓ.ም በሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ካደረጉ በኋላ ለእስያ አህጉር ያላቸውን ትኩረት እና ፍቅር የገለጹበት ነው ተብሏል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 December 2019, 15:39