ፈልግ

ከኒዩክሌር የጦር መሣሪያ መታቀብ ሞራላዊ ግዴታ መሆኑ ተገለጸ።

በሁለት የጃፓን ከተሞች፣ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የተካሄዱት ጦርነቶች በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ያደረሱትን ጥፋቶች ቤተክርስቲያን ከልብ በመረዳት ይህ አስከፊ ጥፋት እንዳይደገም የሚል ጠንካራ አቋም በአስተምህሮቿ በኩል በማሳሰብ ላይ ትገኛለች። በእነዚህ ሁለት የጃፓን ከተሞች የተካሄዱትን ጦርነቶች እና ያስከተሉትን የሰው ሕይወት መጥፋት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በማዛመድ ይመለከቷቸዋል። ከሁሉ በላይ መገንዘብ የሚቻለው ጦርነት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋትን ማስከተሉን ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው እስካሁን የተመረቱ ከፍተኛ የአውዳሚነት አቅም ያላቸው የጦር መሣሪያዎች በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋን ከማስከተል ሌላ ከምድር ገጽ ሊያጠፉ የሚችሉ ሆነው አልተገኙም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካለፈ በኋላ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ በታሪካዊ የሬዲዮ መልእክታቸው፣ ሰላም ሲኖር ሁሉ ነገር የተሟላ እንደሆነ፣ ነገር ግን ከጦርነት ጥፋት እንጂ ምንም ትርፍ የማይገኝ መሆኑን በዘመኑ ማስተጋባታቸው ይታወሳል። የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በሂሮሺማ ከተማ ከጣለው እና መላውን ዓለም ካስደነገጠ የኒዩክሌር ጦር መሣሪያ ጥቃት ከተፈጸመ ስድስት ዓመት በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 6/1945 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የሬዲዮ መልዕክታቸው በድጋሚ በመታወስ ትልቅ ትርጉም ያለው ሆኖ ተገኝቷል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ካስተላለፉት ታሪካዊ የሬዲዮ መልዕክት በኋላ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በጥቅምት ወር 1962 ዓ. ም. ኩባ፣ ሞስኮ እና ዋሽንግተን የሚጠቀሟቸው ተወንጫፊ ሚሳይል የጦር መሣሪያ ላይ በደረሰው ቀውስ ምክንያት ወደ አቶሚክ ቦምብ መሸጋገራቸው ይታወሳል። ይህን ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል የጦር መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ 13 ቀናት የወሰደ ድርድር መካሄዱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የሁለቱ ተቀናቃኝ መንግሥታት መሪዎች የነበሩ፣ በአሜሪካ በኩል ፕሬዚደንት ኬነዲ እና ከሞስኮ በኩል አቻቸው የሆኑት ክሩሾቭ፣ አውዳሚውን የአቶሚክ ቦምብን ጥቅም ላይ ማዋል እንዲገታ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። ይህን ውሳኔ እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋጽዖን ያደረጉት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ መሆናቸው ስታወቅ ቅዱስነታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ በሁለት መንግሥታት መካከል የጋር ውይይቶችን እንዲደረጉ ለማድረግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችንም ማድረጋቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በቫቲካን ሬዲዮ አማካይነት የኒዩክሌር ጦር መሣሪያን መጠቀም የሚያስከትለውን አሰቃቂነት ጥፋት በማስመልከት ለመላው ዓለም ሕዝብ በተለይም ለሁለቱ ሃያላን መንግሥታት ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ መልዕክት በቤተክርስቲያን አስተምህሮ እይታ ውስጥ በመግባት፣ ከእርሳቸው በኋላ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለማገልገል በተሰየሙት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክቶች በመታገዝ ጦርነትን እና ሰላምን የሚመለከቱ አስተምህሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መጥተዋል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በግንቦት ወር 1963 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ “ሰላም በምድራችን” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ሐዋርያዊ መልዕክት የተላከው ለሚያምኑትም ሆነ ለማያምኑት፣ በጎ ፈቃድ ላላቸው የዓለማችን ሰዎች በሙሉ እንደ ነበር ይታወሳል።

ከርዕሠ  ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ቀጥለው የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልጋይ ሆነው የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፈልግ በመከተል ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤን መርተው እስከ ፍጻሜ ባደረሱበት ወቅትም ቢሆን በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ በተባሉት የጃፓን ከተሞች በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው ስቃይ በየትም የዓለማችን ክፍል እንዳይደገም በማለት የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል። “ደስታ እና ተስፋ” በሚለው ሐዋርያዊ ሰነድ ላይ የተጠቀሰው መልዕክትም አውዳሚ የሆነው የኒዩክሌር ጦር መሣሪያን ለጦርነት ማዋል ሕጋዊ የሆነውን እና ራስን የመከላል መብት የሚጥስ መሆኑን ያስገነዝባል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ጥቅምት 4/1965 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር “የሰው ልጅ በሳይንስ የደረሰበትን ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ በመጠቀም በመካከሉ ቅራኔን፣ ጥላቻን እና ልዩነት የሚያመጡ እንደዚሁም ለከፍተኛ ጥፋት የሚዳርጉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያን ለማምረት ችሏል” በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል። ይህ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀረቡት መልዕክት ጥሪ ብቻ ሳይሆን፣ ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ እንዳደርጉት ሁሉ በጸሎት በመታገዝ ሃያላን መንግሥታት ከቅድስት መንበር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ መልካም መንገድን የሚከፍት መልዕክት እና በኒዩክሌር የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ፍላጎት እንዲያስወግዱ የሚጠይቅ መሆኑ ይታወሳል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በመቀጠል መላዋን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያገለገሉ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛም ቢሆኑ ከእርሳቸው አስቀድመው የነበሩት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት የተራመዱበትን የሰላም ጎዳና በመራመድ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2/1980 ዓ. ም. በፓሪስ በተካሄደው የተባበሩትመንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ተግኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የሰው ልጅ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እድገት አስታውሰው እድገቱ የሰውን ልጅ የሚጠቅም እንጂ መልሶ የሚጎዳ መሆን የለበትም በማለት ጉባኤውን ለተካፈሉት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ተመራማሪዎች መናገራቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በመልዕክታቸው የሳይንስ ጠበብት ሞራላዊ ግዴታቸውን በመጠቀም የሰውን ልጅ በኒዩክሌር የጦር መሣሪያ በኩል ሊደርስ ከሚችል አደጋ መከላልከል እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ይህን መልዕክት በመያዝ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር የካቲት 25/1981 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የእስያ አገር ወደ ሆነችው ጃፓን በመሄድ በሂሮሺማ የሚገኘውን የሰላም መታሰቢያ ሥፍራን መጎብኘታቸው ይታወሳል። ከዚህ ጉብኝታቸው ተመልሰው ለሳይንስ ጠበብት በድጋሚ በላኩት መልዕክታቸው ሃያላን መንግሥታት በኒዩክሌር የጦር መሣሪያ ምርታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸው በሰው ሕይወት ላይ ስጋትን እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸው ሞራላዊ ግዴታዎች በተግባር ላይ ካልዋሉ አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች በሰው ሕይወት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት አደጋ ከፍተኛ ነው በማለት አሳስበዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛም በበኩላቸው አቶሚክ የጦር መሣሪያን መጠቀም በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል በተለያዩ አጋጣሚዎች ማሳሰባቸው የሚታወስ ሲሆን ከእነዚህ ማሳሰቢያዎች መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን  ምክንያት በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክታቸው “አንዳንድ መንግሥታት የአገሮቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ በኑክሌር መሣሪያዎች ላይ ይተማመናሉ” ብለው በኒዩክሌር የጦር መሣሪያ የታገዘ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች ጥፋት እንጂ ማንም አሸናፊ  ሊሆን እንደማይችል መግለጻቸው ይታወሳል። በቅድስት መንበር በኩል የጃፓን አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ኒዩክሌር የጦር መሣሪያን መጠቀም እንዲቆም በማለት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው አስከፊ የኒዩክሌር የጦር መሣሪያ ምርት በዓለማችን ሊያስከት የሚችለውን ጥፋት በመገንዘብ ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያስተላልፉ መቆየታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእርሳቸው አስቀድመው የነበሩት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት አቋም በመያዝ ኒዩክሌር የጦር መሣሪያን ለጦርነት ማዋል የሰው ልጅ ራሱን በራሱ የሚያጠፋበት መንገድ ነው በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይህን የጥፋት መንገድ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ኒዩክሌር የጦር መሣሪያ ምርትን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎችን በማበረታታትም ይታወቃሉ። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ 2017 ዓ. ም. በቫቲካን በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች እና ለሳይንስ ጠበብት ባስተላለፉት መልዕክት የኒዩክሌር የጦር መሣርያ ምርትም ሆነ አጥቃቀም ከግብረ ገብ ውጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሕገ ወጥ መሣሪያ መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሁለቱ የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች ባደረጉት 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ለጃፓን ሕዝብ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው ኒዩክሌር የጦር መሣርያን መጠቀም ከግብረ ገብ ወጭ የሆነ ተግባር ነው በማለትው ማሳሰባቸው ይታወሳል። ከዚህ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሌላ በባንግላዴሽ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የኑክሌር መሳሪያዎችን የመጠቀም ወይም ያለመጠቀም ሕግን መወሰን በምንችልበት ደረጃ ላይ ነን” ማለታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ጃፓን ባደረጉት 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ወደ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በመሄድ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ የጎበኟቸውን ሥፍራዎች ጎብኝተው መመለሳቸው ታውቋል። ሥፍራውን በጎበኙበት ወቅት በኒዩክሌር የጦር መሣሪያ የታገዘ ጦርነት ሊያስከትል የሚችለውን ጥፋት በግልጽ የሚያሳይ የፎቶግራፍ ምስል ማሳየታቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 November 2019, 15:39