ፈልግ

በአመጽ መቀስቀስ የተደናገጡ የካሜሩን ሴቶች እና ሕጻናት፣ በአመጽ መቀስቀስ የተደናገጡ የካሜሩን ሴቶች እና ሕጻናት፣  

አቡነ ቤርናዲቶ ሴቶችን በሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ ማሳተፍ ያስፈልጋል አሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ጥሪ ሴቶች በሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ መሳተፍ የሚችሉበት እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ ይህን ጥሪ ያቀረቡት ከ20 ዓመት በፊት የጸጥታው ምክር ቤት ያጸደቀውን ስምምነት ዋቢ በማድረግ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚቀሰቀሱት አመጾች እና ጦርነቶች ከፍተኛ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ የጸጥታው ምክር ቤት ሰላምን እና ጸጥታን በማስከበር አገልግሎት ሴቶች ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽዖ ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም ብለዋል። በመሆኑም ሴቶች ለሰላም እና ጸጥታ ማስከበር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ከቃላት አልፎ በተግባር የሚተረጎም ሂደት እንዲኖር በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ያወጣው ደንብ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ተረስቶ የቆየው የሴቶች ድምጽ፣

በሃያ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ብዙን ጊዜ የሚሰማው የሴቶች ድምጽ ተደማጭነት እንዲኖረው ጠይቀው ሴቶች ሰላምን እና እርቅን በማውረድ የሚያደርጉት እገዛ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው በዚህ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ላይ የሴቶች ሚና እንዲያድግ እድል መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ በማከልም ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ የተናገሩትን በማስታወስ በማህበራዊ እና ባህላዊ ዘርፎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

ሴቶች የአመጽ እና የጦርነት ተጠቂዎች ናቸው፣

አመጾች እና ጦርነቶች በሚቀሰቀሱባቸው አካባቢዎች በቅድሚያ ጉዳት የሚደርስባቸው ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በጦርነት ጊዜ ሴቶችን ከሚደርስባቸው ጉዳቶች መካከል አንዳንዶችን ጠቅሰው ከእነዚህም መካከል መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ፣ የጤና እና ማሕበራዊ ሕይወት መቃወስን ጠቅሰው የጾታ ጥቃትን እንደ ጦርነት ስልትም ይጠቀምባቸዋል ብለዋል። እነዚህ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች በየትም አካባቢ ቢሆን ሊወገዙ ይገባል ብለዋል። በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ጠንካራ አቋም እንዲኖር አሳስበው ጥቃቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል።

ሴቶች በሰላም ማስከበር ሂደት በስፋት እንዲሳተፉ አልተደርጉም፣

ሴቶች የጦርነት እና የአመጾች ተጠቂ ይሁኑ እንጂ ሰላምን በማምጣት እና እርቅን በማውረድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ በጦርነት እና በአመጽ የተጎዱ ቤተሰቦችን እና የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማረጋጋት ሴቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ ሴቶች አመጾችን እና ጦርነቶችን ለማስወገድ በሚደረጉ የመፍትሄ ፍለጋ ሂደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ አይደረግም ብለው በብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት አሳስበዋል። በሰላም እና እርቅ ማውረድ እንዲሁም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የደነገገው የአንቀጽ 1325 ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲት አውዛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታውን ምክር ቤት ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የእናቶች እና የልጃ ገረዶች ተሳትፎ መሠረታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የገዳማዊያት ሚና፣

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ የገዳማዊያት ማሕበርን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ ከ40 ዓመት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የነበሩትን ቅድስት ማዘር ተሬዛን አስታውሰው፣ ገዳማዊያት የሴቶችን ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደጉ ጠይቀዋል። በተለይም የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል እና የሌሎች ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ሴቶችን፣ ወንዶችን እና ልጃ ገረዶችን ወደ ቤታቸው ተቀብለው አስፈላጊውን የምክር እና ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኙ በርካታ ገዳማዊያት መኖራቸውን አስታውሰዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው ከ10 ዓመት በፊት የተመሠረተ “ታሊታ ኩም” የተባለ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት ሕብረትን አስታውሰው ማሕበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ጥቃት ለተፈጸመባቸው 15 ሺህ ሴቶች እርዳታ ማድረጉን፣ ለሌሎች 200 ሺህ ሴቶችም ራሳቸውን ከጥቃት የሚከላከሉበትን የምክር አገልግሎት መስጠቱን አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ ከዚህም ጋር አያይዘው ዓለም አቀፉ የገዳማዊያት ሕብረት በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መተጨማሪ በሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች ውስጥ የወደቁትን ሴቶች ከችግራቸው ለማውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በአድናቆት አስታውሰዋል።

ጥረቱ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ይገለጽ፣

በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረቡትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፣ የጸጥታው ምክር ቤት ሴቶችን በሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ተግባር ላይ በስፋት ለማሳተፍ የወጠነው እቅድ በቃል ወይም በጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲገለጽ ጠይቀው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሴቶችን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 November 2019, 15:09