ፈልግ

ከፍልስጤም ስደተኛ ሕጻናት መካከል፣ ከፍልስጤም ስደተኛ ሕጻናት መካከል፣  

የፍልስጤም ስደተኞች ለ70 ዓመታት ያህል ሰላምን እየናፈቁ መቆየታቸው ተገለጸ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1949 ዓ. ም. የተቋቋመው ማዕከል በስደት ላይ ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን መጠለያን በመስጠት እና የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮችን ማገዙን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል። ለስደተኞቹ የሚቀርብ እገዛ ቀጣይነት ያለው እንደሚሆን ቅድስት መንበር ተስፋ ማድረጓን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ አውዛ ማስታወቃቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቤርታ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአረብ-እስራኤል ጦርነት ሳቢያ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ሶርያ እና በጋዛ አካባቢዎች ለሚሰደዱት ፍልስጤማውያን መጠለያን፣ ዕለታዊ ቀለብን፣ የሥራ ዕድልን እና የሕክምናን አገልግሎት ለማዳረስ በማሰብ ከ70 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው ማዕከል እስካሁን ባቀረበው እርዳታ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማዊያንን መርዳቱ ታውቋል። ከእነዚህ የፍልስጤም ተፈናቃዮች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑን በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በተዘጋጀላቸው 58 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በእንግድነት መስተናገዳቸው ታውቋል። ስደተኞቹ ከትውልድ አገራቸው ወጥተው የቆዩባቸው 70 ዓመታት ብዙ መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ በኒው ዮርክ ለተቀመጠው የመንግሥታቱ ድርጅት 74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አውዛ በዚህ ንግግራቸው ከእርዳታ ለጋሽ አገሮች ለእነዚህ ስደተኞች የሚደረግ የገንዘብ እገዛ መቀነሱን አስታውቀው፣ የገንዘብ እገዛ መቀነሱ ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይሆን ያላቸውን ስጋት ገልጸው በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ ስቃይ ላይ ለሚገኙት ስደተኞች የሚደረግ ስብዓዊ የእርዳታ አቅርቦት ምን ጊዜም ቢሆን መቋረጥ እንደሌለበት አሳስበዋል። ከእርዳታ ለጋሽ አገሮች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2014 ዓ. ም. ጀምሮ በጦርነት ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው የወደመባቸው ቤተሰቦች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የቀን ሰራተኞች እና ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር እያስከተለ የሚገኝ መሆኑን አቡነ ቤርናዲቶ ገልጸዋል።

ስደተኞችን ለሚያስተናግዱ አገሮች ምስጋና ቀርቦላቸዋል፣

የፍልስጤም ስደተኞች ከጎርጎሮሳዊያኑ 1948 ዓ. ም. ጀምሮ ከሚኖሩበት አካባቢዎች ተነስተው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዛወሩ የሚያደርግ እቅድ በፍልስጤም ስደተኞች ላይ የተቃጣ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ እቅዱ በስደተኞቹ መካከል ጭንቀትን እንደፈጠረባቸው እና ኑሮአቸውንም ይበልጥ የከፋ እንደሚያደርገው ለጠቅላላ ጉባኤው አስረድተዋል።

ዜግነትን ማግኘት ሰብዓዊ መብት ነው፣

ማንም ሰው አገር አልባ መሆን የለበትም ያሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ አውዛ የዜግነት መብት ማስከበር ከሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ ነው ብለው ዘላቂ የሰላም ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ለፍልስጤም ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የዜግነት መብታቸውን ማስጠበቅ ከሚደርስባቸው አደጋ ለመታደግ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተው ይህን ሰብዓዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ እርዳታ ለጋሽ አገሮች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያሳዩ ጠይቀው በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም የማያዳላ አንድነትን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።

ፍትሐዊ እና ዘላቂ የሰላም ተስፋ ሊኖር ይገባል፣

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በኒው ዮርክ ከተማ ለተቀመጠው የተባባሩት መንግሥታቱ ድርጅት 74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያሰሙትን ንግግር ከማጠቃለላቸው አስቀድመው እንደተናገሩት በፍልስጤም ስደተኞች ላይ የተጋረጠው ችግር ዘላቂ የሰላም መፍትሄን የሚያገኝ እንደሆነ ቅድስት መንበር ተስፋ ያላት መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል የቆየውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ ሁለት መንግሥታት፣ ሁለት አገሮች በሚለው አስታራቂ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ሁለቱም ወገኖች ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ቅድስት መንበር ተስፋ እንዳላት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 November 2019, 14:33