ፈልግ

የስንዴ እርሻ፣ የስንዴ እርሻ፣ 

አቡነ ፌርናንዶ ኪካ ለዓለማችን ስነ ምግባርን የተከተሉ የፖለቲካ መሪዎች ማዘጋጀት የሚያስፈልግ መሆኑን ገለጹ።

“በስነ ምግባር የታነጸ አመራርን በማቅረብ ለመጭው ዘመን እንዘጋጅ” በሚል ርዕሥ በሮም ከተማ ዛሬ ህዳር 3/2012 ዓ. ም. አውደ ጥናት መካሄዱን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቤርታ ጂሶቲ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። በሮም ከተማ በሚገኝ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀውን አውደ ጥናት በጋራ ሆነው ያስተባበሩት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ጽሕፈት ቤት፣ ዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ እና በቫቲካን የሚገኝ የዮሴፍ ራትዚንገር - ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን መሆኑናቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘገባ አክሎ አስታውቋል። በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አሬላኖ ለአውደ ጥናቱ ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር ለዓለማችን ስነ ምግባርን የተከተሉ የፖለቲካ መሪዎች የሚያስፈልግ መሆኑን ገለጸዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውደ ጥናቱ ዓላማ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚመደብ የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ቢሆኑም በዓለማች የሚከሰተውን የምግብ እጥረት፣ የምግብ ምርት እንዳይጨምር የሚያደርጉ እንቅፋቶች መኖራቸውን በመገንዘብ ችግሩ የሚወገድበትን ሳይንሳዊ መንገድ ለማግኘት፣ በአካባቢ እና በሰው ጤና ላይ የሚደርሱትን ጉዳቶች በመከላከል መጭውን ዘመን የተሻለ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። አውደ ጥናቱ በተጨማሪም የምግብ ምርት እንዳይጨምር የሚያደርጉ እንቅፋቶችን በመለየት ትክክለኛ የመፍትሄ መንገዶችን ለማግኘት በሚያግዙ የስነ ምግባር አካሄዶች ትኩረት ለማድረግ መሆኑ ታውቋል።

ዘላቂ ልማት ፍትሃዊ የምግብ ስርዓት ይፈልጋል፣

በአውደ ጥናቱ ላይ ከቀረቡት የምርምር ሥራዎች መካከል አንዱ ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ፍትሃዊ የምግብ ስርዓት እንደሚያስፈል ውይይት የተደረገበት ሲሆን ዘላቂ ልማት የሚጀምረው የምግብ ምርት እና አቅርቦት ፍትሃዊ ስርዓትን ሲከተል መሆኑን ጥናቱ አስገንዝቧል። 

በሮም በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተካሄደውን አውደ ጥናት በንግግር የከፈቱት በቫቲካን የሚገኝ የዮሴፍ ራትዚንገር - ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ክቡር አባ ሎምባርዲ እና በተባበሩት መንግሥታ የምግብ እና ግብርና ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ማርያ ሔለና ሰሜዶ መሆናቸው ታውቋል። በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት በጳጳሳዊ አካዴሚ የስነ ማሕበረሰብ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ፣ በቅድስት መንበር በኩል የጣሊያን አምባሳደር ክቡር አቶ ፔትሮ ሰባስቲያኒ፣ ሮም ከተማ የሚገኝ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ቪንቼንሶ ቡዎኖሞ እና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አሬላኖ መሆናቸው ታውቋል።

ያለመታዘዝ ተቀባይነት ባሕል የለም

በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ክቡር አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ፣ በዘመናች የምግብ ምርት እንዳይጨምር ከሚያደርጉት እንቅፋቶች መካከል አንዱ ሳይንሳዊ የሆኑ በቂ መረጃዎችን፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን ያለመቀበል ባሕል እንደሆነ አስረድተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ. ም. የዓለም ሕዝብ ቁጥር አሁን ከሚገኝበት ከ7 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ወደ 10 ቢሊዮን እንደሚደርስ፣ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሠረትም የዓለም የምግብ ምርትም አሁን በሚታረሰው የእርሻ መሬት ላይ 30 ከመቶ በመጨመር ወደ 70 ከመቶ የሚያድግ መሆኑን አስታውቀዋል።                       

እየጨመረ የሚገኘውን የእርሻ ምርት እና የስጋ ፍጆታን መቆጣጠር፣

የስጋ ምርት ፍጆታ የሚወሰነው በተመጋቢው ገቢ መጠን ይሆናል ያሉት ክቡር አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ ባሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ የአንድ ሰው አማካይ የስጋ ምርት ፍጆታ በዓመት 83 ኪ. ግ.፣ በአውሮጳ ሕብረት አገሮች 62 ኪ. ግ.፣ በእስያ 28 ኪ. ግ.፣ በአፍሪካ 11 ኪ. ግ. መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ትንበያ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ. ም. የአንድ ሰው የዓመት ገቢን በማገናዘብ በእስያ እና በአፍሪካ የስጋ ምርት ፍጆታ መጠን በዓለም ደረጃ ወደ 76 ከመቶ ከፍ የሚል መሆኑን አስታውቋል።

በዚህ መሠረት የሌሎችም ዕለታዊ ፍጆታዎች መጠን የውሃ እና የጥራጥሬ ምግቦች ፍጆታም መጠንም የሚጨምር መሆኑን አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ ስታውቀው ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተገኘለት የደን መውደም እና የለም አፈር በዝናብ መሸርሸር  አሳዛኝ ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላል ብለዋል።

የምግብ መባከንን መቀነስ፣

በአውደ ጥናቱ ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል ሌላው የምግብ መባከን ሲሆን በዓለማች ከሚመረተው የምግብ ምርት መጠን 32 ከመቶ በዝግጅት ወቅት፣ 22 ከመቶ በምርት መሰብሰብ ወቅት፣ 13 ከመቶ በምርት ማከፋፈል፣ 22 ከመቶ ደግሞ በፍጆታ ደረጃ ላይ እያለ የሚባክን መሆኑ ተገልጿል። እንዲሁ ከሚባክን የምግብ መጠን 56 ከመቶ ባደጉት አገሮች፣ የተቀሩት 44 ከመቶ የሚሆን ምግብ የሚባክነው በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

ጥቂት ኩባንያዎች ገበያውን ተቆጣጥረውታል፣

በምግብ ምርት ላይ የሚታዩትን ሁለት ክስተቶች መመልከት እንደሚያስፈልግ ያሳስሰቡት፣ በጳጳሳዊ አካዴሚ የስነ ማሕበረሰብ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ፣ እነዚህም የገንዘብ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታዎች መሆናቸውን ገልጸው ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን የሚመረተው የምግብ ምርት ጥቂት ኩባንያዎች በተቆጣጠሩት የገበያ ስርዓት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል። ክቡር አቶ ስቴፋኖ ዛማኚ ከዚህ በማያያዝ በዓለማችን የምርት ገበያን የተቆጣጠሩ 10 ታላላቅ ኩባንያዎች መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ ኩባንያዎች በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ የሚያካሂደው የመሬት ቅርምት በምግብ ምርት እና በነዋሪው ሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።   

በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ጠንካራ ሥነ ምግባር ይጎድላል፣

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አሬላኖ ለአውደ ጥናቱ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ጠንካራ ሥነ ምግባር እንደሚጎድል አስታውቀው፣ ችግሮችን ለመቀነስ በሚያስችል ግብረ ገብ በመመራት ትክክለኛ እርምጃን የሚወስዱ፣ መልካም ስነ ምግባርን የሚከተሉ ማሕበራዊ የፖለቲካ መሪዎች ያስፈልጉናል ብለዋል። “ነገር ግን መልካም ስነ ምግባርን የሚከተሉ መሪዎች የትኞቹ ናቸው”? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አሬላኖ ከሁሉ አስቀድሞ በትህትና የተሞሉ አስተዋዮች፣ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ያላቸው እና በሚደርስባቸው ችግሮች እና ሥቃዮች አዘኔታ ያላቸው፣ ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት ፈቃደኛ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

የሁሉም ሰው የወደፊት ዕድል በሌሎች ላይ የተመካ ነው፣      

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ አሬላኖ ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት እንዳስገነዘቡት የሁሉም ሰው የወደፊት ዕድል በሌሎች ሰዎች ላይ የሚመካ መሆኑን ገልጸው በስነ ምግባር የታነጸ አመራር ማለት የሙያ ብቃት ወይም ባህላዊ ተሞክሮ ሳይሆን የሕይወት ምስክርነት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 November 2019, 16:37