ፈልግ

የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ  

የአማዞን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሦስተኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤ ርዕሦችን አስታወቀ።

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን አካባቢ አገሮች የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሃሳብ አስታወቀ። ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ልዩ ሲኖዶስ ትናንት ጠዋት ባካሄደው ሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች ሰብዓዊ መብቶች እና ስልጠና ላይ መወያየቱ ከጉባኤው ቀጥሎ የተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተገኙት 183 የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው ለጉባኤው የቀረቡትን የመወያያ ርዕሠ ጉዳዮችን አድምጠዋል።     

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሦስተኛ ዙር የጠቅላላ ጉባኤ ባካሄደው ውይይት በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች በሚኖሩ ሕዝቦች፣ በሕዝብ ተወካዮች፣ በሕዝባዊ ማሕበራት እና እንቅስቃሴዎች ሰብዓዊ መብት ላይ ሰፊ ውይይቶችን ማድረጉ ታውቋል። ጉባኤው በአማዞን ደናማው አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ድንበሮቻቸውን ለማስከበር ሲሉ ሕይወታቸውን የተሰው በቁጥር በርካታ ሰማዕታት መኖራቸውን አስታውሶ፣ ከ1995 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 2009 ዓ. ም. ድረስ ባሉት 14 ዓመታት ውስጥ 1119 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ጉባኤው በማከልም በደህንነት ዋስትና እጦትም በአካባቢው ማሕበረሰብ መሪዎችም ላይ ከባድ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ገልጿል። በዚህም መሠረት ነዋሪዎቹ የሚደርስባቸውን የሕይወት መጥፋት፣ መቁሰል እና የንብረት መውደምን ቤተክርስቲያን ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን ዘላቂ ማሕበራዊ ፍትህን ለማምጣት በርትታ መሥራት እንዳለባት ጥሪ አቅርቧል። በጉባኤው ላይ እና ከዚህም በፊት ብዙን ጊዜ እንደተወሳው የቤተክርስቲያን ዋና ተግባር የሚሆነው በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሕገ ወጥ የደኖች ጭፍጨፋ እና አካባቢን የሚያወድሙ ፕሮጄክቶች እንቅስቃሴ ለማስቆም ድምጿን እንድታሰማ የሚል መሆኑ ታውቋል። የሲኖዶሱ አባቶች በተጨማሪም የአካባቢውን ደሃ ማሕበረሰብ ወደ ጎን የሚያደርግ የኤኮኖሚ ሥርዓትን ከማራመድ ይልቅ ነዋሪዎች በጥቃቅን ማሕበራት ተደራጅተው ወደ ትላልቅ ኩባንያዎች ሳይሄዱ ምርቶቻቸውን በአካባቢ ገበያዎች ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ሕገ ወጥ የማዕድን ፍለጋ ሞዴሎችን መዋጋት፣

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በማቅረብ ሃሳብ የተለዋወጠበት ሌላው ርዕሠ ጉዳይ ሕገ ወጥ የማዕድናት ማውጫ ፕሮጄክቶች እና እነዚህ ፕሮጄክቶች በተፈጥሮ ላይ እያስከተሉ የሚገኙትን አደጋ የተመለከተ መሆኑ ታውቋል። ፕሮጄክቶቹ ማዕድናትን ለመፈልግ እና ለማውጣት በሚል ሰበብ የአካባቢውን ደን መጨፍጨፍ፣ የተፈጥሮ ሃብትን ደህንነት ለማስጠበቅ የተዋቀረ የመንግሥት አካል ባሳየው ደካማ የሕግ ማስከበር ስርዓትን ተከትሎ በአካባቢው የተሰማሩት የተለያዩ ኩባንያዎች አካባቢውን በማራቆት ላይ እንደሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ገልጿል። ቤተክርስቲያን በአካባቢ እና በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ማሕበራዊ ተግባራት እንዲገቱ ዓለም አቀፍ ደንቦችን ተከትላ፣ የስቃይ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ድምጽ ጉዳዩ ለሚመለከተው ክፍል እንድታሰማ ጥሪ አቅርቧል። ሲኖዶሱ በማከልም የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ሲጥሩ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ሚሲዮናዊያን መኖራቸውንም አስታውሷል።

አማዞን የስደተኞች ምድር ነው፣

የሲኖዶሱ አባቶች የተወያየበት ሌላው ርዕሰ ጉዳይ በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚኖሩ ነባር ነዋሪዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ትላልቅ ከተሞች የሚያደርጉትን ስደት የተመለከተ መሆኑ ታውቋል። የአማዞን አካባቢ አገሮች ነባር ነዋሪዎች መሰደድ በተመለከተ ቤተክርስቲያን በበኩሏ ማግኘት የምትችለው የምፍትሄ ሃሳብ ካለ በማለት የሲኖዶሱ አባቶች ተነጋግረውበታል። የነባር ነዋሪዎች መሰደድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ የመጣ ክስተት እንደሆነ ተገልጾ ለዚህ አዲስ ማሕበራዊ ክስተት ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት ቤተክርስቲያን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመሆን በሕብረት መሥራት እንዳለባት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በአማዞን አካባቢ አገሮች የታየው ስደት ወጣቶች የተወለዱበትን አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ አገር እንዲሰደዱ የተገደዱበትም ምክንያት ሲገልጽ በሥራ እጦት፣ በአካባቢያቸው በሚነሱ አመጾች፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ በሴተኛ አዳሪነት እና በጉልበት ብዝበዛ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። በአካባቢው አገሮች የምትገኝ ቤተክርስቲያን እነዚህን ማሕበራዊ ችግሮችን በትክክል በመገንዘብ ወጣቶች በተለያዩ ማሕበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ውስጥ በንቃት በማሳተፍ ተስፋን የሚሰጡ እንድታደርጋቸው በማለት የሲኖዶሱ አባቶች ጥሪያቸውን አቅርበውላታል።

የሥልጠና አስፈላጊነት፣

የሲኖዶሱ አባቶች በዚህ መሠረት ሁሉ አቀፍ የሆነች ቤተክርስቲያን ለሐዋርያዊ አገልግሎቷ ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከት የሚችሉ የምዕመናን ወገን ማሳተፍ ይኖርባታል በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል። ቤተክርስቲያን ምዕመናን ለቤተክርስቲያናቸው ሊያበረክት ለሚችሉት ወይም በማበርከት ላይ ለሚገኙት አገልግሎቶች እውቅናን እንድትሰጥ አሳስበው፣ ከምዕመናን ዘንድ የሚቀርቡትን አስተያየቶች ማዳመጥ እንዳለባት አሳስበዋል። በተለይም የአገልጋይ ካህን እጥረት በሚታዩባቸው አካባቢዎች ምዕመናን ሊያበረክቱ የሚችሉት አገልግሎቶች ላይ ቤተክርስቲያን እንድታስብበት አደራ ብለዋል። ይህን አስመልክተው የሲኖዶሱ አባቶች ባቀረቡት አስተያየት ምዕመናን ለቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደመሆናቸው መጠን በጋብቻ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን በክህነታዊ አገልግሎት ላይም መሳተፍ የሚችሉበትን ዕድል ቤተክርስቲያን እንድታስብበት ጥሪ አቅርበዋል።

አዳዲስ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች፣

በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ የሚታየውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማነስ ያስታወሱት የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት ቤተክርስቲያን ለመንፈሳዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ሕይወት ትኩረትን በመስጠት በአካባቢው ነባር ነዋሪዎች መካከል ጥሪን በማሳደግ ከምዕመናን መካከል ተመርጠው ለሚቀርቡት ባለ ትዳሮች እና ከቤተክርስቲያን እውቅናን ካገኙት አገልጋዮች ጋር የሚተባበሩ ቋሚ ዲያቆናትን በማዘጋጀት ቅዱሳት ምስጢራትን ለምዕመናን የሚያድሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ሃሳብ አቅርበዋል። የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ማዘጋጀት አስመልክቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ ዝግጅቱ ሦስት ደረጃ ኣንዲኖረው፣ የመጀመሪያው በቁምስና ደረጃ የአግልግሎት ዘርፍ የሚሰጣቸው፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚያስተነትኑ እና ለዕለቱ የተመደቡትን ንባባት ወደ ምዕመናን ዘንድ የሚያደርሱ፣ በሁለተኛ ደረጃ ሙሉ ጊዜያቸውን የምዕመናን ማሕበረሰብን በማስተዳደር አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱ እና በሦስተኛ ደረጃ የስነ መለኮት ትምህርቶችን ተከታትለው በክህነት አገልግሎት ተሰማርተው ምዕመናንን ማገልገል የሚፈልጉትን የምዕመናን ወገን ማዘጋጀት መሆኑን ገልጸዋል። በጉባኤው ከቀረቡት አስተያየቶች መካከል ሌላው ወደ ምዕመናኑ ቀርበው አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን ማበረታታት ሲሆን ሌላው ደግሞ ለሴት ምዕመናን የድቁና ማዕረግን በመስጠት ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ማብቃት መሆኑ ታውቋል።    

09 October 2019, 17:44