ፈልግ

ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ሥነ ምግባርን የተከተለ አመራር የሚያስፈልግ መሆኑ ተገለጸ።

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በማስመልከት ሴሚናር መካሄዱ ተገለጸ። “የአማዞን አካባቢ አገሮች ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ የተካሄደውን ሴሚናር ያስተባበረው በቫቲካን የሚገኝ የዮሴፍ ራትዚንገር - ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አድሪያና ማሶቲ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። የአማዞን አካባቢ ደናማ አካባቢን ከውድመት ለማትረፍ የሚደረግ ጥረት ሥነ ምግባርን የተከተለ መሆን እንዳለበት በሴሚናሩ ላይ የቀረቡ አስታያየቶች አመልክተዋል። ሴሚናሩን ያዘጋጀው የራትዚንገር ፋውንዴሽን እንዳስታወቀው ባሁኑ ጊዜ በአማዞን አካባቢ አገሮች ተሰማርተው ስነ ምሕዳራዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ሥነ ምግባርን የተከተለ አመራርን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መወያየታቸውን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ሴሚናር ላይ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ ሎዜርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ክፍል፣ በሮም ከተማ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅቶች፣ እንዲሁም አንዳንድ የግል ድርጅቶች የተሳተፉ መሆናቸው ታውቃል። የአማዞን አካባቢ አገሮችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መቋቋም እንዲቻል፣ ሥነ ምግባርን የተከተለ የአመራር ስልት የሚያስፈልግ መሆኑን የገለጹት የተለየያዩ ድርጅቶች በተጨማሪም እርስ በእርስ በመቀራረብ እና በመተባበር በአካባቢው አገሮች ውስጥ ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር በሕብረት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ 2022 ዓ. ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ከያዘው ዘላቂ የልማት እቅድ ጋር መዛመድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተዘጋጀውን ሴሚናር በጋራ ሆነው የከፈቱት የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሎሬንዞ ባልዲሴሪ እና የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን የሚመሩት ካርዲናል ፔድሮ ባሬቶ ይሜኖ መሆናቸው ታውቋል። የሰውን ልጅ የሚያጋጥሙ በርካታ ማሕበራዊ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ቢኖሩም የተለያዩ የማቃለያ መንገዶች መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፔድሮ ባሬቶ፣ ለጋራ መኖሪያ በሆነው ምድራችን ላይ ያለን ስጋት ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚላክልንን ደስታ እና ተስፋ ሊያስቀር አይችልም ብለዋል። ሴሚናሩን የተካፈሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በስነ ምህዳር ላይ ያላቸውን አቋም እና አስተያየቶችን የገለጹ መሆናቸው ታውቋል። ሴሚናሩን የመሩት የዮሴፍ ራትዚንገር - ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ እና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ መሆናቸው ታውቋል።

ሴሚናሩ እንዲካሄድ የተፈለገበት ምክንያት፣

የዮሴፍ ራትዚንገር - ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ሴሚናሩ እንዲካሄድ የተፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ከዚህ በፊት የምንኖርባትን የጋራ ምድራችን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ጥረቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያደርጉት ጥረት የሚያድግበትን መንገድ ለማመቻቸት መሆኑን አስረድተዋል። ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ ከዚህም ጋር አያይዘው እንደገለጹት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ለፍጥረት የሚገባውን እንክብካቤን እና ጥበቃን በማስመልከት የተናገሯቸው በርካታ ርዕሶች መኖራቸውን አስታውሰው ባሁኑ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ርዕሠ ጉዳዮች ያሳደጓቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለማችንን ከውድመት ለማዳን የሚያግዝ የፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አቶ ሬኔ ካስትሮ ሳላዛር ለሴሚናሩ ተካፋዮች  ባሰሙት ንግግር እንዳስታወቁት የዓለማችን መንግሥታት፣ ሕዝቦች እና ግለ ሰቦች ምድራችንን እየደረሰ ያለውን ጥፋት በመረዳት ከሚደርስባት አደጋ ለማዳን የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከሁሉም አቅጣጫ ሊደረግ የሚችል ጥረት እንዳለ የገለጹት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ በማከልም የሚገኙበትን አካካባቢ ከብክለት እና ከጥፋት ለማትርፍ በሁለት የላቲና አሜሪካ አገራት፣ በቺሊ እና በኮስታ ሪካ በኩል እየተደረገ ያለውን መልካም ጥረት እንደ ምሳሌ ጠቅሰው በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ጥረቶችን ለማድረግ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ፍላጎት ሊኖር ይገባል ብለዋል። ምክትል ዋና ጸሐፊው ይህን ከገለጹ በኋላ በተለያዩ አሕጉራት የሚገኙ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አሳስበው፣ ምድራችንን ከውድመት ለማዳን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሰው ልጅ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአማዞን አካባቢ አገሮች ነባር ነዋሪዎች፣

በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ የሚታየውን ድህነት ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ተወካይ የሆኑት ማቲያ ፕሬየር እንዳስገነዘቡት በላቲን አሜሪካ በገጠራማው አካባቢ በሚኖሩ ነባር ነዋሪዎች መካከል የሚታየውን ድህነት ለመቀነስ ድርጅታቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸው በዓለማን ውስጥ የድህነት ሕይወት ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል 75 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በላቲን አሜሪካ አገሮች የሚገኙ ነባር ነዋሪዎች መሆናቸውን አስረድተው። ድርጅታቸው በእነዚህ አካባቢዎች ሥራውን ከጀመረ 30 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው ባሁኑ ጊዜ በ32 አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ 6 ሚሊዮን ሰዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ለሚገኙ 63 ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅታቸው ለእነዚህ ሕዝቦች የሚያደርገውን ድጋፍ በሁለት መንገዶች እንደሚያካህድ፣ የመጀመሪያ በድህነት ደረጃ ላይ ከሚገኝ ማሕበረሰብ ጋር ቀጥታ ግንኙነትን በመፍጠር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ በሌላ ወገን በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ በድህነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ነባር ሕዝቦች ከአገራቸው መንግሥታት እና የፖለቲካ አመራር ጋር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ግልጽ ውይይቶችን በማድረግ ለአንዳንድ ጥቃቅን ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጎማን ማድረግ እንደሆነ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ተወካይ የሆኑት ማቲያ ፕሬየር አስረድተዋል።  

ለማሕበራዊ ጥቅም የጋራ ሃላፊነት እንዲኖር ያስፈልጋል፣

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ከሚገኙባቸው ጉዳዮች መካከል ሌላው ለአካባቢ የሚደረግ ጥበቃን እና እንክብካቤን የሚመለከት ሲሆን፣ የሴሚናሩ ተካፋዮች በጋራ የተስማሙበት ርዕሠ ጉዳይ በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች የሚኖሩ ነባር ሕዝቦች ከሚኖሩበት አካባቢ ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ በመሆኑ ለአካባቢያቸው የሚሰጡት እንክብካቤ እና ክብር ከሁሉም የላቀ መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ሕዝቦች ለጋራ ጥቅም እንዲሆን በማለት ለአካባቢያቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ እና ጥበቃ እውቅናን ሊያገኝ እንደሚገባም የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ተወካይ ማቲያ ፕሬየር ተናግረዋል። ሕዝቦች ለተፈጥሮ ለሚሰጡት እንክብካቤ እና ጥበቃ እውቅናን መስጠት የሚቻለው በመላው የሰው ልጆች መካከል ያለው ወዳጅነት እና ወንድማማችነት እውን ሲሆን ነው ካሉ በኋላ ይህም በአንድ አካባቢ የሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ ወይም ጦርነት ሌላውን የዓለማችን ክፍል የሚያጠቃ መሆኑን ስንረዳ ነው ብለዋል። የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ተወካይ የሆኑት ማቲያ ፕሬየር ንግግራቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት እንደተናገሩት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከአማዞን አካባቢ አገሮች ነዋሪዎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት በኩል በርካታ የባሕላቸውን እሴቶች ማግኘት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢ መሪዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፣

በሥነ ምግባር የታነጹ መሪዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት የስነ ማሕበረሰብ ጠበብት የሆኑት ክቡር አቶ ፍራንችስኮ ቶራልባ ለሴሚናሩ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግራቸው ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ከግለኝነት ወደ ብዝሃነት መሸጋገር አስፈላጊ እንደሆነ አስሳበው በሕብረት ለመኖር እና ለመሥራት በስነ ምግባር የታነጸ፣ ትህትናን የሚያሳይ፣ ቸርነትንም የሚያደርግ ህብረተሰብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የአንድ ጠንካራ መሪ መለያው የተፈጥሮ ስጦታውን እና ችሎታ የሚገነዘብ፣ በዚህም በመታገዝ ከሌሎች በተለየ መንገድ በግል ሊያበረክት የተጠራበትን አገልግሎት ለሌሎች ማበርከት ሲችል ነው ብለዋል። ከፍተኛ ለውጥ እየታየ በሚገኝበት ዘመን ላይ እንገኛለን ያሉት የስነ ማሕበረሰብ ጠበብት፣ አቶ ፍራንችስኮ ቶራልባ ንግግራቸውን ባጠቃለሉበት ጊዜ እንዳስገነዘቡት ዛሬ ያጋጠሙን እና ነገም ቢሆን የሚደርስብንን አደጋ ለመጋፈጥ የሚያግዙ አዳዲስ የፖለቲካ መንገዶችን መቀየስ እና መሪዎችንም ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዓለማችን መልካም ባህል ማሳደግ ያስፈልጋል፣

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ በሴሚናሩ ማጠቃለያ ላይ በአማዞን አካባቢ አገሮች ውስጥ የደረሱትን አካባቢያዊ እና ማሕበራዊ ቀውሶች አስታውሰው እነዚህ ቀውሶች ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች መሆናቸውን አስረድተው በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች በመተባበር ቅንነት ባለው አካሄድ ዓለም አቀፋዊ መፍትሄዎችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

       

21 October 2019, 16:07