ፈልግ

የሕንዱ እምነት ተከታይ ምዕመናን በጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ሆነው፣ የሕንዱ እምነት ተከታይ ምዕመናን በጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ሆነው፣ 

ቅድስት መንበር ወንድማማችነትን በጋራ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳሰበች።

በቅድስት መንበር፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ወንድማማችነትን በጋራ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቡን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ኤማኑኤላ ካምፓኒለ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ይህን የማሳሰቢያ መልዕክት የላከው፣ “ዲፓቫሊ” የተባለ ታላቅ ዓመታዊ በዓላቸውን ለሚያከብሩ የሕንዱ እምነት ተከታይ ምዕመናን መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ምክር ቤት በመልዕክቱ በሰዎች መካከል ወንድማማችነትን እና በመቻቻል አብሮ በሰላም መኖርን ማሳደግ እያንዳንዱን ሰው የሚመለከት እንደሆነ ገልጾ በተለይም የክርስቲያኖች እና የሕንዱ እምነት ተከታዮች ግዴታ ነው ብሏል። በሰላም አብሮ መኖርን አስፈላጊነት በመጥቀስ ጥሪን የሚያቀርብ መልዕክት ፈርመው ይፋ ያደረጉት በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ይህን መልዕክት የላኩት መጭው እሑድ ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. ዓመታዊ በዓላቸውን ለሚያከብሩ የመላው ዓለም የሂንዱ እምነት ተከታዮች መሆኑ ታውቋል። “ስለሆነም ዘላቂ ውይይቶችን በማድረግ በወንድማማችነት እና በወዳጅነት መንፈስ አብሮ መኖር የሐይማኖታዊ ሰው፣ የሕንዱ ወይም የክርስትና እምነት ተከታይ ተፈጥሯዊ ምኞት እና ፍላጎት ነው” በማለት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል በመልዕክታቸው አስረድተዋል።

የሚጋጭ ዓለም፣

እስካሁን ባልታዩ በርካታ ማሕበራዊ ዘርፎች ውስጥ እንደምንገኝ የሚገልጸው መልዕክት እንዳብራራው፣ በአንድ ወገን በተለያዩ ሃይማኖቶች እና ባሕሎች መካከል በርካታ ውይይቶች በሚደረጉበት፣ መተጋገዝ እና አንድነት እያደገ በመጣበት ዘመን ላይ ስንገኝ በሌላ ወገን ደግሞ በሰዎች መካከል ልዩነነቶች በሚንጸባረቁበት፣ በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ጥላቻ እያደገ በመጣበት ዘመን ላይ እንደምንገኝ የገለጸው መልዕክት ለዚህ ሁሉ ብዙን ጊዜ እንደ ምክንያት የሚቀርበው አንዱ ሌላውን እንደ ወንድም እና እንደ እህት ካለመመልከት የተንሳ መሆኑን መልዕክቱ አስረድቷል።   

የምንኖርበትን ዓለም መረዳት ያስፈልጋል፣

ሌላውን በመመልከት ድጋፍ እና ፍቅር ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ያለው በቅድስት መንበር የጳጳሳዊ ምክር ቤት መልዕክት በዓለማችን ሰላምን ለማንገሥ እና ተቻችሎ ለመኖር የሚያግዝ፣ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም አህመድ አል ጣይብ መካከል የተፈረመውን “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ እና የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ 25ኛውን ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ መልዕክት አስታውሷል።   

በርካታ መልካም እሴቶች አሉን፣

ከዘመናችን ጥረቶች መካከል ወንድማዊ ፍቅርን የሚያሳድጉ በርካታ የተደበቁ እሴቶች መናራቸውን የገለጸው የጳጳሳዊ ምክር ቤት መልዕክት ምንም እንኳን የምንሰማቸው አስደንጋጭ ዜናዎች በሐይማኖት ተቋማት እና በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ለማሳደግ ከሚደረግ ጥረት ወደ ኋላ ሊያስቀሩ እንደማይችሉ ገልጾ በመሆኑም የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች፣ በጎ ፈቃድ ያላቸው በሙሉ ሕብረት እና ሰላም የሚገኝበትን ዓለም ለመገንባት መተባበር እንደሚያስፈልግ መልዕክቱ አሳስቧል። በመሆኑም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የሰላም መልዕክተኞች” በማለት ለሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በወንድማማችነት መንፈስ በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያስችለንን የጋራ መኖሪያ መገንባት እንደሚያስፈልግ መልዕክቱ አሳስቧል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
22 October 2019, 17:00