ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ 

አቡነ ቤርናዲቶ፥ “ዓለም አቀፍ አሸባሪነትን ለማስወገድ የጋራ ውይይቶች ሊደረጉ ይገባል”።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጠራው 74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቤርናርዲቶ አውዛ፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት የሚያስከትለውን አሰቃቂ ወንጀል ለመዋጋት የሲቪል እና የሃይማኖት ተቋማት በመተባበር የሚውስዱት እርምጃ እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንደሆነ ገልጸው ይህ አካሄድ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በውይይት የሚመጣ የመቻቻል ባሕሎችን ማዳበር እና ሁሉን የሚያሳትፍ ሰላማዊ ማሕበረሰብን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት በአሸባሪነት ተግባር በከንቱ ማጥፋት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ፣ በአሸባሪዎች በኩል የሚሰነዘሩ እነዚህ ጨካኝ ተግባራት በዝምታ የምናልፋቸው እና በቀላሉ ፍርድን መስጠት የምንችልባቸው ጉዳዮች አለመሆናቸውን አስረድተዋል። የጥቃቱ ሰለባዎችን ስቃይ ለማስታገስ ሃገራት በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በመዋጋት ይህን የመሰለ አስከፊ ክስተት  በአስቸኳይ ማስቆም እንደሚያስፈልግ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቤርናዲቶ በማከልም ሽብርተኝነት ለመዋጋት የሚያግዙ አራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሪያዎችን ጠቅሰው እነርሱም ሰላም እና የደህንነት ዋስትና ፣ ሰብዓዊ መብቶች ፣ የሕግ የበላይነት እና የሰው ልጆች እድገት እና ልማት የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዓለም ላይ ለደረሰው ጥቃት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ምላሽ፣

በመላው ዓለም ላይ ለተቃጣው የጥፋት ተግባር ዓለም አቀፋዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤርናዲቶ አውዛ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ባቀረቡት አስተያየታቸው በአሸባሪነት ወንጀሎች ለተሰማሩት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ መገታት እንዳለበት፣ በማሕበራዊ ሚዲያ አማካይነት ወጣቶች በአሸባሪነት ወንጀል እንዲሰማሩ የሚያበረታታ ቅስቀሳ መቆም እንዳለበት፣ አሸባሪነትን ለመታገል የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፣ ወንጀሎችን በሚከታተሉ ፖሊሶች እና በዳኝነት ሥልጣን ላይ በሚገኙ የሕግ ባለሞያዎች መካከል ያለው የጋራ መግባባት መሻሻል ይኖርበታል በማለት አስተያየታቸውን አካፍለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ በማከልም ፍርድ ቤቶች የአሸባሪ ቡድንን የሚደግፉ፣ የቡድኖችን አባላት ተቀብለው የሚስተንግዱ እና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ህጎችን የሚጥሱት ወደ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሰው ልጅ ክብርን እና መብትን ለማስጠበቅ ውጤታማ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ፣

አሸባሪነትን ለመግታት የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ በወንጀሉ ላይ በተሰማሩት ሰዎች ላይ የሚወሰዱ የሕግ እርምጃዎች ሰብዓዊ መብቶችን ያከበሩ እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መሆን የለባቸውም ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ በማከልም ሕዝቦች፣ መንግሥታት፣ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት እና መሪዎቻቸው አሸባሪነትን ለማስቆም የሚችሉባቸው መንገዶች ስላሏቸው አስተዋጽዖዋቸውን ማበርከት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጋራ ውይይትን ማሳደግ፣

በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ አቡዳቢ ከተማ ላይ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በአህመድ አል ጣይብ መካከል የተፈረመውን “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በመካከላቸው የጋራ ውይይቶችን፣ አንድነትን እና መቻቻልን ማሳደግ እንዳለባቸው አሳስበው ሽብርተኝነትን ለመግታት ምንም እንኳን የወንጀሉ አስከፊነት ከፍተኛ ቢሆንም የሚያስከትለውን አሰቃቂ ወንጀል ለመዋጋት የሲቪል እና የሃይማኖት ተቋማት በመተባበር የሚውስዱት እርምጃ እንዲሁም የሕግ የበላይነት እንደሆነ ገልጸው ይህ አካሄድ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በውይይት የሚመጣ የመቻቻል ባሕሎችን ማዳበር እና ሁሉን የሚያሳትፍ ሰላማዊ ማሕበረሰብን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 October 2019, 17:26