ፈልግ

የየመን ተፈናቃይ ሕጻን፣ የየመን ተፈናቃይ ሕጻን፣ 

ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ክርስቲያኖች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቀረቡ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በመንግሥታቱ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች ክርስቲያኖች ጠንካራ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በማለት ማሳሰባቸውን የቫቲካን የዜና ማሰራጫ አስታወቀ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሦስት አበይት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በማትኮር ንግግራቸውን ያደረጉት ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ በአካባቢው አገሮች ውስጥ በተከታታይ የሚነሱ አመጾች የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ሕዝቦች ሕይወትን አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል። በመሆኑም ነፍሳትን ከሞት አደጋ ማትረፍ፣ የአመጹ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን ማስጠበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ተከላካይ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች ጥበቃን ማቆም፣ ማሕበራዊ ተቋማትን በተለይም ሆስፒታሎችን፣ የትምሕርት ተቋማትን፣ የአምልኮ ሥፍራዎችን እና የጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ ጣቢያዎችን ከጥፋት መከላከል እንደሚያስፈልግ ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ አሳስበዋል።

የመን፣

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቅርቡ የመን የምትገኝበትን ሰብዓዊ ቀውስ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ በየመን በርካታ ሕጻናት እንደሚራቡ፣ ሕዝቡ በንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጦት እንደሚሰቃይ፣ ኤኮኖሚው ክፉኛ መጎዳቱን፣ በጦርነቱ ምክንያት የማምለጫ መንገድ የተዘጋባቸው በርካታ ሰዎች መሠረታዊ የዕለት ቀለብ ማግኘት ሳይችሉ መቅረታቸው እና የእርዳታ ሠራተኞችም በጦርነት ወደ ተጠቁ አካባቢዎች እንዳይደርሱ መከልከላቸው ችግሩን አባብሶታል ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሪፖርት መሠረት ያለፈው መስከረም ወር በየመን ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት፣ በቀን በአማካይ 13 ሰዎች በጦርነት አደጋ የሚሞቱበት ወር እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል። በየመን የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ያበቃ ዘንድ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርግ በማለት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች በኩል ተደጋጋሚ ጥሪ መደረጉ በጎ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ የየመን ሕዝብ መከራ እና ስቃይ ፍጻሜን ማግኘቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ አክለውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች በኩል በተደጋጋሚ የቀረበው የተኩስ አቁም ጥሪ በአካባቢው አገሮች የተስፋፋውን የጦር መሣሪያ ዝውውር ለማስቆም ሐቀኛ ፍላጎትን ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሶርያ፣

በቅርቡ በሰሜን ምሥራቅ ሶርያ የተቀሰቀሰው አመጽ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ፣ እሑድ ጥቅምት 2/2012 ዓ. ም.፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የመልአከ እግዚአብሔርን ጸሎት በመሩመት ወቅት ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፣ በሶርያ በመካሄድ ላይ በሚገኝ ጦርነት እጃቸው እንዳለበት የሚጠቀሱ አገሮች እና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም መፍትሄን ሊያስገኙ የሚችሉ ቅንነት ፣ ሐቀኝነት እና ግልጽነት ያለባቸውን ውይይቶችን እንዲያድርጉ ማሳሰባቸወን አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ንግግራቸውን በመቀጠል በጦርነት ምክንያት በመከራ ውስጥ ለወደቁት እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉት በተለይም በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ዘላቂ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታን ማቅረብ እና ከለላን መስጠት፣ መሠረታዊ የሆነው ሰብዓዊ መብታቸውን እና የማንነት ክብራቸውን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው ተጨማሪ አመጾች እንዳይቀሰቀሱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ፍልስጤም፣

የፍልስጤምን ጉዳይ አንስተው ንግግር ያደረጉት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር እንደራሴ እና ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቤርናዲቶ አውዛ ከሦስት ዓመት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአንቀጽ 2334 ያስተላለፈውን ውሳኔ በማስታወስ ባደረጉት ንግግር ከፍተኛ ጉዳትን የሚያስከትሉ አመጾች እና የሽብር ተግባራት መበራከታቸውን፣ ከጸጥታ አስከባሪዎች በኩል የሚሰነዘሩ የመከላከያ መንገዶች ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤርናዲቶ አውዛ ከዚህም ጋር አያይዘው በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ለራሳቸው እና ለልጆቻቸው ሰላም እና ደህንነት ሲሉ የሚኖሩበትን እና እምነታቸውን የሚያካሂዱበትን የትውልድ አገራቸውን ለቀው እንደሰደዱ መገደዳቸውን አስታውሰው ለክርስቲያን ማሕበረሰብ እና ለእምነታቸው ሕልውና መከበር በቂ ከለላ እንዲደረግላቸው ጠይቀው ለሌሎች ዜጎች እንደሚደረግ ሁሉ በእሥራኤል እና በፍልስጤም ለሚገኙ ዜጎች በሙሉ የተሟላ ሰብዓዊ እድገት ሊረጋገጥላቸው ይገባል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 October 2019, 14:56