ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙበት ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙበት ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ፣ 

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻውን ሰነድ ረቂቅ አቀረበ።

ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ሰኞ ጥቅምት 10/2012 ዓ. ም. ባካሄደው 14ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ የመጨረሻውን ሰነድ ረቂቅ ማቅረቡን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ትናንት ጠዋት ላይ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ የመጨረሻውን ሰነድ ረቂቅ ያቀረበው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መሆኑን የዜና አገልግሎቱ አስታውቆ በጉባኤው ላይ 184 የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች የተገኙበት መሆኑን ገልጿል። ከመስከረም 26/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት የሚጠናቀቀው መጭው እሑድ ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻውን ሰነድ ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀረቡት የጉባኤው አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ሂውምስ መሆናቸው ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደረጉት ውይቶች እና ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ የቀረቡትን ፍሬ ሃሳቦችን አንድ ላይ ሰብስቦ የያዘው ረቂቅ ሰነድ ለውይይት ወደ ትናንሽ ቡድኖች ዘንድ የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል።

የመጪዎቹ ቀናት ፕሮግራሞች፣

ከትናንሽ ቡድኖች በኩል የሚቀርቡ ሃሳቦችን በማጤን ማሻሻያዎች የተደረገበት የመጨረሻው ሰነድ በጉባኤው አስተባባሪ፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና በልዩ ባለሙያዎች የሚታይ መሆኑ ታውቋል። ይህ ሰነድ መጭው ዓርብ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሚደረግ 15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ፊት በንባብ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል። ቀጥሎም ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012 ዓ. ም. በሚደረገው 16ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ የሲኖዶሱ አባቶች ድምጽ የሚሰጡበት መሆኑ ታውቋል። 

የሊቀ ጳጳሳት ሄክቶር ካብሬዮስ አስተንትኖ፣

ሰኞ ጥቅምት 10/2012 ዓ. ም. የተካሄደው 14ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተጀመረው በጸሎት ስነ ስርዓት ሲሆን በዚህ ወቅት ስብከታቸውን ያቀረቡት የላቲን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚደንት እና የሜክስኮ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ካብሬዮስ እንደተናገሩት የጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የፍጥረታትን ውበት በማድነቅ ያቀረበውን የምስጋና መዝሙር እንዲያስታውሱ ጠይቀው “ለቅዱስ ፍራንችስኮስ ውበት ውጫዊ ገጽታ ሳይሆን ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና ጸጋ ነው” ብለዋል። የአሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ፍጥረታትን በሙሉ በፍቅር ይመለከታቸው እንደነበር፣ ከፍጥረታት ጋር በነበረው ፍቅር አማካይነት ይገናኝ እንደነበር፣ እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቀማቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ፍጥረታትን ማወቅ ፣ መገንዘብ እና መልሶ ማቋቋም፣

በሦስት ቃላት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት፣ የላቲን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚደንት እና የሜክስኮ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ካብሬዮስ፣ ፍጥረታትን ማወቅ ፣ መገንዘብ እና መልሶ ማቋቋም በሚሉት ቃላት ላይ በማስተንተን፣ የአሲዚው ቅዱስ ፍራንችስኮስ በመንፈሳዊ ጉዞው የፍጥረታትን የበላይነት በማወቅ፣ ለሰው ልጆች የሚሰጡትን ጥቅም በመገንዘብ ምስጋናን ያቀርብላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ለቅዱስ ፍራንችስኮስ ሐጢአት ማለት እግዚአብሔር በሰው ልጆች በኩል መልካምን መመኘት እና ማድረግ፣ ፍጥረታቱን በመመልከት ምስጋናውን ማቅረብ እንዳይችል የሚያደርግ፣ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጅ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲበላሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እግዚአብሔር የፍጥረታት ሁሉ አባት ነው፣

ቅዱስ ፍራንችስኮስ በመዝሙሩ እንደገለጸው፣ በዘወትር ምስጋና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ለፍጥረታት በሙሉ የተሰጠ ግዴታ እንደሆነ የተናገሩት የሜክስኮ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄክቶር፣ በሰው ልጅ ሐጢአት ምክንያት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ሳይቀርብ የቀረው ምስጋና በፍጥረታት አማካይነት የሚቀርብ መሆኑን አስረድተዋል። የፍጥረታትን ክብር ቅዱስ ፍራንችስኮስ የተገነዘበው በእግዚአብሔር ውስጥ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄክቶር፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ፍጥረታትን የወደደው እና የተንከባከበው የእግዚአብሔር አባትነት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታት በሙሉ መሆኑን ስለተገነዘበ ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

22 October 2019, 16:39