ፈልግ

ከአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤዎች መካከል አንዱ፣ ከአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤዎች መካከል አንዱ፣  

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ ሰነዱን ለጠቅላላ ጉባኤው አቀረበ።

በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ትናንት ዓርብ ጥቅምት 15/2012 ዓ. ም. ባደረገው ጉባኤ   የመጨረሻውን ሰነድ ለጠቅላላ ጉባኤው ማቅረቡን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።  የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ጉባኤውን በሚያገባድድበት በመጨረሻው ሳምንት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። ትናንት ጥቅምት 15/2012 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተካሄደው 15ኛ የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙ መሆናቸው ታውቋል። ይህን ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ 182 የሲኖዶሱ አባቶች የተካፈሉበት መሆኑ ሲታወቅ በዕለቱ የቀረበውን የመጨረሻ ሰነድ ካዳመጡ በኋላ 13 የአስፈጻሚ ኮሚቴ ምክር ቤት አባላትን መምረጡን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት አክሎ አስታውቋል። ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ላይ በተደረገው ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ በቀረበው ሰነዱ አንዳንድ ተጨማሪ ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆናቸው ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በከፍተኛ ድምጽ የመረጧቸው እና የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮችን የሚወክሉ የምክር ቤት አባላት ስም ዝርዝር ይፋ መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሠረት አራት ከብራዚል፣ ሁለት ከቦሊቪያ፣ ሁለት ከኮሎምቢያ፣ ሁለት ከፔሩ፣ አንድ ከአንቲሌ፣ አንድ ከቨነዙዌላ፣ እና አንድ ከኤኳዶር መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህም በተጨማሪ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተመርጠው የሚቀርቡ ሦስት ተጨማሪ የምክር ቤት አባላት የሚኖሩ መሆናቸው ሲነገር የምክር ቤቱ ዋና ተግባርም የሲኖዶሱን ሰነድ ሃሳብ አፈፃጻም መከታተል መሆኑ ታውቋል።         

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶስ በኩል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሰነድ ለጉባኤው ያቀረቡት በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች የሚገኙ ቤተክርስቲያናት ፕሬዚደንት እና የሲኖዶሱ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ሂውምስ ከሲኖዶሱ በኩል የቀረበውን ሰነድ ለጉባኤው ማቅረባቸው ታውቋል። በዚህ ወቅት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ሂውምስ እንዳስታወቁት ምክር ቤቱ ከጉባኤው ተካፋዮች በኩል የቀረቡትን አስተያየቶች በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውቀዋል። ከሲኖዶሱ በኩል የቀረበው ሰነድ በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች የሚታየው የስነ ምሕዳር ቀውስ ጊዜ ሳይሰጠው አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የሚያሳስብ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ሂውምስ አስታውቀዋል። የአማዞን ደንን ከውድመት መታደግ እና መንከባከብ በዓለማችን ለሚገኙ የሰው ልጆች ጤንነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ቤተክርስቲያንም ብትሆን ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥን ማድረግ እነድሚያስፈልግ በሚገባ የተረዳች መሆኗን አስታውቀዋል። ቤተክርስቲያን በአማዞን አካባቢ አገሮች የሚገኙ ልጆቿን ጭንቀት እና የምድሪቱንም ስቃይ በሚገባ ተረድተዋለች ያሉት ካርዲናል ክላውዲዮ ከሁለቱም አቅጣጫዎች የሚደመጡ የስቃይ ድምጾች ምድራችን ከደረሰባት አደጋ የምትወጣበት የትልቅ ተስፋ ምልክቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች የሚገኙ ቤተክርስቲያናት ፕሬዚደንት እና የሲኖዶሱ አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ሂውምስ፣ የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና ከር. ሊ. ጳጳሳት ጋር ያላትን አንድነት የምትገልጽበት፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሪነት የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ለማጠናከር የሚያገለግል ነው ብለዋል።

ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 16/2019 ዓ. ም. በተካሄደው 16ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ ምክር ቤቱ በድጋሚ አይቶት ያቀረበውን ሰነድ የሲኖዶሱ አባቶች በጋራ ሆነው በማዳመጥ ድምጽ የሰጡበት መሆኑ ታውቋል። በመጨረሻም የብጹዓን ሲኖዶሱ የተለመደ አካሄድ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2012 ዓ. ም. የተካሄደውን የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ሲኖዶስ የሚያስታውስ ስጦታ ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተካፋዮች በሙሉ ማበርከታቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 October 2019, 16:49